Latest

ያልተያዘ. . . ከሔዋን ሁለት ሺ


“እኔ ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት፣ አንተስ?” አልኩት፣ ከእንግሊዘኛው አልፎ የተሰማኝ ዘዬ (accent) የየትኛው አፍሪካ ሀገር እንደሆነ በሀሳቤ ለመገመት እየሞከርኩኝ።

“እናቴ ቦረና ነው የተወለደችው” አለኝ፣ “ነገሌ ቦረና?” አልኩኝ በትልቅ ፈገግታ፣ ፈገግታውን መልሶ “አዎ! አባቴ ደግሞ ሶማሊያ ውስጥ ሉቅ የሚባል ስፍራ ነው ተወልዶ ያደገው” አጠገቡ ከነበረው ውሀ ተጎነጭቶ “እኔ ደግሞ ኬንያ ውስጥ ጋሪሳ የሚባል ቦታ በUNHCR የሚደገፍ ዳዳብ የሚባል የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው ህይወቴን ያሳለፍኩት”።

ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ. . . “ታዲያ ኢትዮጵያዊም፣ ሶማሊያዊም፣ ኬንያዊም እንደሆንክ ይሰማሀል?” የመጀመሪያው ጥያቄዬን ጠየኩት። እጁን መዳፉ ላይ አስደግፎ ከፊል ፊቱን የሸፈነውን ጢሙን እያሻሸ ጥቂት ሰከንዶችን በዝምታ አሳለፍን።

“የሶስቱም ሀገር ዜጋ አይደለሁም. . . የምንም ሀገር ዜጋ አይደለሁም። እውነት ለመናገር ደሞ ከዜግነት እንኳን ባለፈ ሶስቱንም ቦታዎች ቤቴ ብዬ ለመጥራት ይከብደኛል። ነገሌ ቦረና ለእኔ በእናቴ ትውስታ ውስጥ የሚኖር ሩቅ ቦታ ነው። ልጅ እያለሁ አንዴ ሄጄ ነበር. . . ከእማዬ እና ከትልቋ እህቴ ጋር።

ታዲያ ያኔ እማዬ ጋራውን ሸንተረሩን ዛሮቹን እያየችና ትውስታዎቿን እየነገረችን አልቅሳለች። በእሷ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው ዛፎች፣ ጋራና ሽንተረሮች ግን ለእኔ ግኡዝ አካሎች ብቻ ነበሩ። አባቴ ሶማሊያ ውስጥ ስለነበረው ህይወቱ ብዙ አያወራንም፣ በኋላ ላይ ሞቃዲሾ ወታደር ሆኖ ይተዳደር እንደነበር አውቃለሁ።

ኬንያ ደግሞ ህይወቴን ሙሉ በብቸኝነት የማውቃት ሀገር ብትሆንም አልተቀበለችኝም፣ አልፈለገችኝም - ከካምፑ ውጪ የትም ቦታ የመገኘት መብት አልነበረኝምና። እንኳን እንደኔ ግልፅ ሶማሊያዊ መልክ የያዘ ግለሰብ ይቅርና፣ ፖሊሶች ማንኛውንም ሰው አስቁመው መታወቂያ ይጠይቃሉ። እኔ ደሞ ስደተኛ ነኝ፣ መታወቂያ የለኝም። በዚህም ኬንያ ውስጥ የማውቀው ዳዳብ ካምፕን ብቻ ነው፣ ምናልባትም በቤትነት ልይዘው የሚገባው እሱን ይሆናል።”

የድምፁ ፈርጣማነት ከእውነታው ጋር ሰላምን ፈጥሮ የሚተርክ እንጂ መባበልን የሚሻ እንዳልሆነ ያሳብቅበታል። ለእኔ ግን ከውልደት ጀምሮ ያለውን ህይወት በስደተኝነት ማሳለፍ ማለት የማይታሰብ ነገር ስለሆነብኝ የንግግራችንን ክብደት ለመቀነስ እና አቅጣጫ ለመቀየር “ታውቃለህ፣ አልበርት አነስታይንም እኮ የምንም ሀገር ዜግነት ያልነበረው ጊዜ ነበር? ራሱን ‘የአለም ዜጋ’ እያለ ይጠራ ነበር ይላሉ” አልኩት። 

ፈገግ አለና “እሱ በገዛ ፈቃዱ ነው፣ እኔ ግን ያው በምርጫ አይደለም” አለኝ። “እዚህ ከመምጣቴ በፊት. . . “ ቀጠለ “እዚህ ከመምጣቴ በፊት ወደመጣህበት እንደምትመለስ የሚያሳይ ማስረጃ ካላቀረብክ ቪዛ አንሰጥህም ብለውኝ ነበር። ምንም የግሌ የምለው ንብረት የሌለኝ ሰው ነኝ፣ የግል ንብረት ማፍራት ይቅርና መንገድ ላይ መታየት የማልችልበት ሀገር ውስጥ ተወልጄ ያደኩኝ. . . እንዴት እዛ እመለሳለሁ ብዬ ማስረጃ አቀርባለሁ?. . . ወደየት እመለሳለሁ? . . . እዛች ካምፕ ውስጥ ህይወትን እስከፍፃሜ ለመምራት?” 

መልስ አልነበረኝም። ከጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ በኋላ “ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ምን መሆን ትፈልጋለህ? ምን ማድረግ ትፈልጋለህ? የት መኖር?” ጥያቄዎችን አከታተልኩኝ፣ ካጎነበሰበት ቀና ብሎ “መፃፍ እወዳለሁ፣ መፃፍ በጣም እወዳለሁ። ብዙ ከባድ ነገሮችን በመፃፍ ውስጥ አሳልፌያለሁ. . . ወደፊትም የእኔንና የሌሎችን ታሪክ በፅሁፍ ማውሳት ብችል ደስ ይለኛል” አለ፣ ስለመፃፍ ማውራት ሲጀምር ፊቱ ከቀድሞው በራ። 

“እስከዛሬ የፃፍኳቸው መጣጥፎችና የተወሰኑ አጭር ልብወለዶች አሉኝ፣ ጊዜ ካለሽ ልክልሽና ታነቢያቸዋለሽ” ሲለኝ “ደስ እያለኝ!” አልኩት ከእሱ ፊት መፍካት ጋር የእኔም አብሮ ፈክቶ። “አሁን ትንሽም ቢሆን ነፃነት ይሰማኛል. . . ምንም ነገር እንዳልያዘኝ. . . መውጣት እና መንገድ ላይ መታየት ወንጀል እንዳልሆነ. . . ከእዛኛው ካቴና ለጊዜውም ቢሆን እንደተላቀቅኩኝ . . . ” አለ፣ ፈገግታው ሳይጠፋ። ፊቱ ላይ የሰው ልጅን የውበት ዳርቻ በጥንካሬና በተስፈኝነት ተሞልቶ ያየሁ መሰለኝ . . .

No comments