Latest

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የጋራ ኮሚቴ አቋቋሙ


የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን እና የኢትዮጵያ ሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴን በተናጠልና በጋራ አወያይተዋል።

በውይይታቸውም የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ሰላማዊ በሆኑ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት መስማማታቸውን ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ያስታወቀው። ሁለቱ ወገኖች ችግሮችን በእስልምና አስተምህሮት መሰረት በጋራ ለመፍታትም ተስማምተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በዘላቂነትና ሰላማዊ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ ወኪሎችን ያካተተ መፍትሄ አፈላላጊ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል። አዲስ የተቋቋመው ኮሚቴ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን ሁለቱ ወገኖች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ በጋራ ከተወያዩ በኃላ መሆኑ ተገልጿል።

የኮሚቴዎቹ አባላት ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ፣ ከመጅሊስ፣ ከምሁራን እና ሽማግሌዎች የተውጣጡ ናቸው። ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተመረጡት ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ የታሪክ ምሑሩ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ናቸው።

ከመጅሊስ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር፣ የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሐጂ ሙሐመድ አሚን እና ሐጂ ከድር ሲሆኑ፥ ከምሁራን እና ሽማግሌዎች ዶ/ር ኢድሪስ ሙሐመድ፣ ዶ/ር ሙሐመድ ሀቢብ እና ሼኽ ሙሐመድ ጀማል አጎናፍር መሆናቸው ተገልጿል።

ሙፍቲ ሀጂ ኡመር በሁለቱ ወገኖች የተደረሰውን ስምምነት አስመልክተው "ማንም ሰው እስከተደማመጠ እና እስከ ተቀራረበ ድረስ የማይፈታው ችግር የለም ካሉ በኋላ ይህ ጅምር ፍሬ አፍርቶ ሙስሊም ክርስቲያኑ የሚደሰትበት ውጤት እንደሚያመጣ እምነቴ ነው" ብለዋል።

ሌሎቹ የጋራ የእርቅ ኮሚቴው አባላት የሆኑት ሀጂ መሀመድ አሚን፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል እና ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸዉ በጋራ ኮሚቴው ደስተኛ መሆናቸውን እና ውጤት እንደሚያመጣም ሙሉ እምነታቸውን ገልፀዋል።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድም ሰው ቢሆን ሰላም እስካልሆነ ድረስ ሁላችንም ሰላም ልንሆን አንችልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የለውጥ እና የመደመር ሂደት ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክሉት ሁለቱ ወገኖቻችን ከሚያራርቋቸው ነገሮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸውን የጋራ ግቦች በመመልከት አብሮነታቸውን እስካላጸኑ ድረስ የሙስሊሙ ወገንም ሆነ የሀገሪቱ ሰላም በፍጹም ሙሉ ሊሆን አይችልም ብለዋል።

ሙስሊሙን ማህበረሰብ አገለግላለው የሚል መሪም አርአያ መሆን እንዳለበት እና ይቅር መባባል የሀይማኖቱም መሰረት እንደሆነ በመጥቀስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ቢጠነክር አንድ ቢሆን ለሀገርም ጥቅም እንደሆነ አንስተዋል።
አያይዘውም ትልቅ አደራን የተቀበለው ኮሚቴው አደራውን እንደማይበላ አምናለው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር እና ይቅርታን በሚሰብክ እና የሰላም ቤት ነው በሚባል የእምነት ተቋም ውስጥ ደግሞ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ሰላም የግድ መኖር ያለበት ብቻ ሳይሆን ከሀይማኖታዊ ባህርይም በላይ የእምነት ተቋማት ተፈጥሮም ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የሁለቱ ወገኖች ለመነጋገርና ችግሮቻቸውንም በሰላም ለመፍታት መስማማት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም ብስራት ነው ማለታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments