Latest

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነትን ተፈራረሙ


የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የተለያዩ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን ተፈራረሙ።

በዚህ ስምምነት ሀገራቱ የነበሩበት ጦርነት ማብቃቱን በይፋ አውጀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረሱ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነቶችን በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

በዚህም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ጦርነት በይፋ ማስቆምና ወደ አዲስ የግንኙነትና ወዳጅነት ምዕራፍ ለመሸጋገር ስምምነት ፈጽመዋል።

በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራትም ሁለቱ መሪዎች በዛሬው እለት በፊርማቸው አረጋግጠዋል።

የአየርና የየብስ ትራንስፖርትን ማስጀመር፣ የተቋረጠውን የመደበኛ ስልክ አገልግሎት እንዲሁም የንግድ ግንኙነታቸውን ማስጀመርም የመሪዎቹ የስምምነት ፊርማ አካል ነው።

ከዚህ ባለፈም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማስጀመር በመስኩ ያቋረጡትን እንቅስቃሴ ለማስቀጠልም ተስማምተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአስመራ የኤርትራ ኤምባሲ ደግሞ በአዲስ አበባ አበባ የሚከፈት ይሆናል።

ሃገራቱ በአልጀርሱ ስምምነት የገቧቸው የድንበር ስምምነቶች ገቢራዊ እንዲሆኑና፥ ሁለቱ ሃገራት በቀጠናው ሰላም፣ ልማትና ትብብርን ለማምጣት በጋራ እንደሚሰሩም በስምምነታቸው ወቅት ገልጸዋል።

የስምምነቶች መፈረምም በሃገራቱ መካከል የጥላቻን በር በመዝጋት አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ታሪካዊ የተባለውን ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አስመራ መግባታቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና እና የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት ለክብራቸው የእራት ግብዣ አዘጋጅተው ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሠላምና ልማት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ድንበር በፍቅር ፈርሷል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የሁለት ቀናት የኤርትራ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል።

ምንጭ ~ ፋና

No comments