Latest

ዶክተር አብይ ቃሉን በልቷል ~ ጌታቸው ሺፈራው ~ክፍል 1


ዶክተር አብር አህመድ መቀሌ ላይ ስለ ወልቃይት በተናገረው ያልተገባ ነገር ተቃውሞ ሲሰማበት ሚያዝያ ወር መጀመርያ ወደ ጎንደር መጥቷል። ጎንደር ጎሃ ሆቴል በነበረው ስብሰብ ከተነሱለት ጥያቄዎች አንዱ ለሱዳን ስለ ኢትዮ_ሱዳን ድንበር ነበር። በወቅቱ የሰጠው መልስም "ነገ አልበሽርን አገኘዋለሁ። ተገናኝተን እናወራለን።… …በቅርቡ የሕዝቦች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይገታ እናደርጋለን" የሚል ቃል ገባ። ሕዝብም ችግሩን ያውቀዋልና አጨበጨበ።

ዶክተር አብይ አልበሽርን ባህርዳር በነበረው የጣና ፎረም አገኘው። በጥቂት ቀን ውስጥ "መፍትሄ እንሰጥበታለን፣ ሕዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ይሆናል" ካለ ከሶስት ወር በኋላም የሱዳን ሰራዊት የአማራ ገበሬዎች ላይ ከባድ መሳርያ እየተኮሰ፣ ድንበር ጥሶ እየገባ ነው።

ሰኔ 4/2010 ዓም በተጠናከረ ሁኔታ የጀመረው የሱዳን ወረራ የእነ ዶክተር አብይን ትኩረት አላገኘም። ከሰኔ 4/2010 ዓም ጀምሮ ገበሬዎች ታፍነው ወደ ሱዳን ተወስደዋል፣ አራት ሰራተኞችና አንድ ባለሀብት እርሻቸው ላይ እያሉ ተገድለዋል። የገበሬዎች ማሳ በሱዳን ሰራዊት ወድሟል። ካምፓቸው ተቃጥሏል።

ከአስር ቀን በፊት በተደረገ ወረራ ከ7 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በሁለተኛው ቀን መከላከያ ሰራዊቱ ወደ ቦታው ቢያቀናም "ከቻላችሁ ገበሬውን አረጋጉ፣ ካልሆነ ተመለሱ" የሚል ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ገበሬውን ያገዙት ከትዕዛዝ ያፈነገጡ የተወሰኑ አባላቱ ብቻ ነበሩ።

የሱዳን ሰራዊት በከባድ መሳርያ፣ የአማራ ገበሬ በነፍስ ወከፍ መሳርያ ጦርነት ሲገጥሙ ዳር ድንበርን ለማስጠበቅ ግዴታ ያለበት፣ ከሶስት ወር በፊት " በቅርብ ቀን ሕዝብ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር እናደርጋለን" ያለው አብይ መንግስት ያደረገው ነገር አልነበረም።

ገበሬው በሱዳን ጦር እየተገደለ፣ ሰራዊቱ ቆሞ እያየ፣ የፌደራል መንግስቱ በወርቅነህ ገበየሁ በኩል የሚገደለውን የአማራ ገበሬ በሰማይ አልፎ ሱዳን ካርቱም ሄዶ እንደነበር ቢነገርም፣ የገበሬዎቹን ሞት፣ የዳር ድንበሩንና ሉአላዊነቱን መደፈር ላይ ግን ምንም አይነት መልስ አልሰጠም። መግለጫ እንኳ አልተሰጠም!

ዛሬም የሱዳን ጦር በአማራ ገበሬዎች ላይ እየዘመተ ነው። የሰው ህይወት እየጠፋ ነው። የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ግን "በቅርብ ቀን" ብሎ የገባውን ቃል በሶስት ወር እውን አላደረገም። ትኩረትም አልሰጠም። ይህ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። የሉአላዊነት ጉዳይ ነው፣ የውጭ ወረራ ነው!

በቅርቡ ዶክተር አብይ አህመድ ችግር ያለባቸው ቦታዎች ላይ መከላከያ ሰራዊቱ እንዲገባ ሲያደርግ በሱዳን ድንበር ግን ገበሬው እንዲያልቅ ተፈርዶበታል። ቃል ተገባም አልተገባም የፌደራል መንግስት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ትልቁ ስራ ከሆነው መካከል ሉአላዊነት ማስከበር የመጀመርያው ነው። የመከላከያ ሰራዊት ዋነኛ ስራ ዳር ድንበር ማስከበር ነው። በውስጥ ጉዳይ እንዲገባ ሲወሰን የሉአላዊነቱ ጉዳይ ግን ገበሬዎች እንዲሞቱበት እዳ ሆኖባቸዋል።

የሱዳን ሰራዊት በማን አዝማችነት እንደሚመጣ እነ ዶክተር አብይ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም። ሀገር ውስጥ "የቀን ጅቦችን ለመከላከል" ተብሎ ሰራዊት ሲሰማራ በ"ቅርብ ቀን" ብሎ ቃል የገባበትን የሱዳን ወረራ ጉዳይ ከሶስት ወር በኋላ ምንም አይነት ትኩረት አልሰጠውም። እየደረሰ እንዳለው ጉዳይ ሆን ብሎ ያለፈውም ይመስላል።

ገበሬዎች በውጭ ሰራዊት ከባድ መሳርያ ሲደበደቡ ስራው ዳር ድንበር መጠበቅ የሆነውንና በዶክተር አብይ የሚመራው ሰራዊት "ተመለስ" የሚል ትዕዛዝ ነው የተሰጠው። የዚህ ሰራዊት አዛዥ ከሶስት ወር በፊት ሱዳን የምትወረው ገበሬ በሰላም እንዲኖር እሰራለን ያለው ዶክተር አብይ አህመድ ነው። 

ሰራዊቱ የገበሬውን ሞት እያየም እንዲመለስ ትዕዛዝ ከተሰጠ "ተውት ይሙት" ባዩ ዶክተር አብይ መሆን አለበት። በውስጥ ጉዳይ መከላከያ ሰራዊት ሲያሰማራ፣ ከተማ ውስጥ መከላከያ ሰራዊት ሲልክ የውጭ ጦር በየቀኑ በሚወረው ሕዝብ ግን ዶክተር አብይ የሚመራው ሰራዊት እንዳይደርስ ተደርጓል። ተገቢው የሰራዊቱ ምላሽ ብቻ ሳይሆን መግለጫ እንኳ ተሰጥቶ አያውቅም።

ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ ቃል አባይ ከሆነበት የመጀመርያው ጉዳይ በአማራ ገበሬ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ነው። ጉዳዩ ካለው አሳሳቢነት አኳያ ዝምታውን እንመዝነው ከተባለ ደግሞ ክህደትም ጭምር ነው። ዶክተር አብይ ስልጣኑን በተረከበ ቀን በፓርላማ ባደረገው ንግግር መተማ ላይ ስለወደቁ ኢትየጵያውያን ተናግሯል። 

መልካም ነበር። ለቀደሙት ታሪካቸውን ማስታወስ እንጅ ጦር መላክ አይችልም። ታሪክ ከማስታወስ በላይ ግን ዛሬ ያን ዳር ድንበር የማስጠበቅ ታሪካዊ አደራ ዶክተር አብይ ላይ ወድቋል። ስለ ታሪኩ ከማውራት ውጭ ዛሬ ያን አደራ መውጣት ግን አልቻለም። በአሁኑ ወቅት፣ ራሱ የሚመራው ሰራዊት ያን አደራ መወጣት አልቻለም። ከሶስት ቀን በፊት ጎንደር ጎሃ ሆቴል የገባውን ቃልም በልቷል!

No comments