የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው
በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል በኢኮኖሚ ልማት፣ በማህበራዊ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ላይ ያተኮረው ምክክር ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ምክክሩ በኢትዮጵያና እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያና በህብረቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።
አያይዘውም ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ከታዳጊ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሃገራት ጋር የተፈራረመው የኣጋርነት ስምምነት ተጠቃሚ መሆኗንም አንስተዋል።
ለ20 አመታት የሚቆየው ስምምነት በፈረንጆቹ 2000 የተፈረመ ሲሆን፥ በስምምነቱ የተካተቱ ሃገራትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ይነገራል።
አሁን ላይ ስምምነቱ እየተጠናቀቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ህብረትና ሃገራቱ በቀጣይ ዘላቂ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ምክክር በኢኮኖሚ ልማት፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በስፋት እንደሚመክር ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈም በህብረቱና በአባል ሃገራቱ መካከል የተለያዩ ስምምነቶች የሚፈረሙ ሲሆን፥ ቀጠናዊ ውህደትን ማምጣት የሚያስችል ውይይት እንደሚደረግም ነው የሚጠበቀው።
ማህበራዊ ልማትን ለዘላቂና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዴት ማዋል እንደሚቻል የሚጠቁም ውይይትም የምክክር መድረኩ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል።
ምክክሩ በኢትዮጵያና እና በአውሮፓ ህብረት መካከል በፈረንጆቹ 2016 የተፈረመው የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት አካል መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
No comments