Latest

የህወሓት ቁልፍ ሰዎች አሜሪካ ሄደው ጠ/ሚ/ር ዓቢይን ለማውረድ ያቀረቡት ጥያቄ ድራማ


ነባርና ታዋቂ የህወሓት ቁልፍ ሰዎች አሜሪካ መታየታቸው በወፍ በረር ሲዘከር መሰንበቱ ይታወሳል። ከሶስት ሳምንት በፊት የህወሓት ሰዎች አሜሪካ ቤት ለመግዛትና ኑሯቸውን ለማደላደል እንደመጡ ተደርጎ ስም እየተጠቀሰ ሲነገርም ቆይቷል።

ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆነ የጎልጉል የዘወትር ታማኝ ዲፕሎማት መረጃ አቀባይ ግን ጉዳዩ ሌላ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። እንደ ዲፕሎማቱ መረጃ የህወሓት ቁልፍ ሰዎች አሜሪካ ድረስ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን ከሥልጣን ለማውረድ በሌላ አነጋገር መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የአሜሪካንን ይሁንታን ፍለጋ ነው።

ዶ/ር ዓቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑበት ዕለትም ሆነ ከዚያ በፊት በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ማዕበል ያልተመቻቸው የህወሓት ሰዎች ስሜታቸውን በተለያየ መልኩ ሲገልጹ ነበር። ሁሉም አልፎ ኢህአዴግ ካባ ውስጥ ባሉ የለውጥ ኃይሎች የተሸነፈው ህወሓት ሽንፈቱን ሳይወድ በግድ ለመቀበል ተገዷል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም የአሜሪካን ይሁንታ ማግኘታቸው “በቆሮቆር ላይ …” እንዲሉ የህወሓት ቁልፍ ሰዎች ሊደብቁት በማይችሉት ደረጃ አሳመማቸው። በዚሁ የህመም ስሜት የተተነፈሰውን ሁሉ ከማኅበራዊ ሚዲያ ጭፍራዎቻቸው ጋር በመሆን በጅምላ የትግራይ ህዝብ ቀለበት ውስጥ እንደገባ አስመስለው ያቀርቡ ጀመር።

“የቀን ጅቦች” በሚል ለሌቦች ሁሉ የተሰጠውን በተለይ ለአንድ የህብረተሰብ ክፍል ነዋሪዎች ሁሉ እንደተሰጠ በማስመሰል ራሳቸውን ህዝብ ጉያ ሥር በመክተት “የትግራይን ህዝብ ከመሪ ድርጅታቸው ህወሓት ነጥለው ሊያጠቁ ተነስተዋል” የሚል መግለጫ ያወጣው ህወሓት ወደ አሜሪካ ያቀናው ከከበበው ፍርሃት በመንሳት መልሶ የፖለቲካ ስልጣኑንን ለመረከብ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በዚሁ መሠረት አሜሪካ ያቀኑት የህወሃት ቁልፍ የተባሉ ሰዎች “ዶ/ር ዓቢይን በሰላማዊ መንገድ እንድናስወግድ ፍቀዱልን” ሲሉ ነው ጥያቄ ያቀረቡት። የመረጃው ምንጭ እንዳሉት “አገሪቱና ቀጣናው አሁን በመበታተን አደጋ ውስጥ ናት” በማለት የህወሓት ሰዎች “የማረጋጋትና ሰላም የማስፈን ልምድና ክህሎት ስላለን ይህንን ሥጋት ማስወግድ እንድንችል ይሁንታ ስጡን” ሲሉ ነው የተማጸኑት።

አንድ የህወሓት የማህበራዊ ገጽ ጭፍራ አገር ባይጠቅስም ይህንኑ ሃሳብ ሲያራግብ እንደነበር፣ የትግራይ ህዝብ አደጋ ላይ መኖሩን ለዓለም ሁሉ በማሳወቅ ራስን የመከላከል ሥራ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ የታዘቡና የህወሓት ክንፍ የድረገጽ ደብተራዎች “ማርም ሲበዛ ይመራል” ማለት ደረጃ መድረሳቸው የመፈንቅለ መንግሥት ጥያቄውን ለማጀብ የተወጠነ ስለመሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

በዶ/ር ዓቢይ ሕይወት ላይ ምንም ሳይደርስ “በሰላማዊ መንገድ ጉዳዩ ይከናወናል” ያሉት የህወሓት ሰዎች፤ የመፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ “የአሜሪካንን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ አዲስ አስተዳደር እናዋቅራለን፤ በቀጠናው የአሜሪካንን ፍላጎት ተግባራዊ እናደርጋለን” ሲሉም ከኩዴታው በኋላ የሚያከናውኑትን በዝርዝር አብራርተዋል።

ጥያቄው የቀረበላቸው የአሜሪካን ወሳኝ የፖሊሲ ሰዎች “አታስቡት” ሲሉ ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር እንደመለሷቸው፣ አሁን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት አጠናክረው እንደሚገፉበት፣ ሕዝብ በለውጡ መደሰቱንና ይህንን የሕዝብ ፍላጎት መከተል ግዴታቸው እንደሆነ አሳስበው በአጭር መልስ አሰናብተዋቸዋል።

መረጃ አቀባይ ዲፕሎማቱ እንዳሉት ከሆነ የህወሓት ሰዎች ዶ/ር አብይ አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ እያመሯት እንደሆነና ህወሓት በዚህ አካሄድ አገሪቱ ልትበታተን ትችላለች የሚል ስጋት እንደገባው መስሎ ላቀረበው “መንግስት ልገልብጥ” ጥያቄ ከአሜሪካ በኩል የተሰጣቸው መልስ “አርፋችሁ ተቀመጡ” የሚል እንደነበር ይናገራሉ።

ይህ ዶ/ር ዓቢይን ከሥልጣን ለማስወገድ የቀረበ ሃሳብ ተቀባይነት ካጣ በኋላ የቅዳሜው ሰኔ 16 ዓቢይን የመግደል ሙከራ እንደ ሁለተኛ ዕቅድ ተግባራዊ ስለመደረጉ የተጠየቁት መረጃ አቀባያችን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

No comments