ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በመጪው ሀምሌ ወር ወደ አሜሪካ ያቀናሉ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ በመጪው ሀምሌ ወር ወደ አሜሪካ በማቅናት በዚያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት መሰረት ያደረገ ሳይሆን በቀጥታ በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አግኝተው ማወያየትን ዋና ዓላማው ያደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩንም እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የሚያደርጉት ጉዞ በአጠቃላይ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆነው ለሀገራቸው ልማትና እድገት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተሳታፊ ሆነው ራሳቸውን ጠቅመው ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ በማለም የሚካሄድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀምሌ 21 በዋሽንግተን ዲሲ እና ሀምሌ 22 ሎስ አንጀለስ ከተማዎች ሁሉም ወገን የሚሳተፉባቸው ጉባኤዎች እንደሚደረጉ በመግለጫው ተጠቁማል።
ለውይይት እነዚህ ከተሞች የተመረጡትም በምስራቁና በምዕራቡ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አቅራቢያ ማዕከል ለማሰባሰብ እንዲመች ተብሎ መሆኑም ነው የተመለከተው።
በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን በየአከባቢያቸው ለመቀበል ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም ካለው ጊዜ አንፃር ግን ሁሉንም ለማዳረስ አዳጋች በመሆኑ ሁለቱ ከተሞች መመረጣቸው ተገልጿል።
በመሆኑም በመካከለኛው አሜሪካ የሚገኙ ወገኖች በሚያመቻቸው ሁኔታ እንዲሳተፉ ነው የተጋበዙት።
በእነዚህ ህዝባዊ ጉባኤዎች ላይ የፖለቲካ አመለካከት፣ የሀይማኖት፣ ብሄር፣ ወዘተ ሳይለያያቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል።
በሌላ በኩልም ከ25 ዓመታት በላይ ተለያይተው የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ለማስታረቅና ወደ አንድነት ለማምጣት በበጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን አስታራቂ ሽማግሌዎች በተቋቋመ ኮሚቴ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መግለጫው አንስቷል።
ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጉዞ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የእርቀ ሰላሙ ሂደት በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም አቡነ ሞርቆርዮስን አግኝተው የሚወያዩ ሲሆን፥ ለእርቀ ሰላሙ በቦታው በመገኘት ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ታውቋል።
No comments