Latest

የብሽሽቅ ፖለቲካን እናቁም አልተባለም እንዴ ! – ዩሱፍ ያሲን / ኦስሎ


በኢትዮጵያ የሚካሄደው የለውጥ ሂደት በጣም እየፈጠነ፣ ምድረ ታዛቢውን፥ ተንታኙን፥ የምንይዘውንና የምንጨብጠውን እያሳጣን ነው፡፡ ምኑ ይጻፍ? ምኑ ይቅደም ? ምኑ ይከተል ? የሚለው ራሱ እያስቸገረ ነው፡፡ በቅድሚያ አንባቢዎቼን ለሳስብ የምፈልገው የአሁኑ የጦቢያ መጣጥፍ ሳይሆን የአጭር የፌስቡክ ጦማር መሆኑን ልብ እንድትሉልኝ ነው፡፡

በሌላ ርዕስ የጀመርኩትን መጣጥፍ ትቼ ወደ ኤርትራ ልዑካን የአዲስ አበባ ጉብኝትና እሱን ተከትሎ ሀገሩን የቀወጠው ‘’ የተዘወሪ መኪና ጓይላና የኤርትራ መንግስት መግለጫ ተብሎ በቴሌቪዥን ቀረበ የተባለው የዕብለት የፉገራ አዋጅ ነው ትኩረቴን ያስቀየረኝ ፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ የለውጥ ባቡርም ልክ እንደ ደርጉ ባቡር ፈጣን ነው፡፡ ልዩነቱ የደርጉ እየገፈተረ ነበር የሚጓዘው ፡፡ የዓቢይ ግን እየደመረና አንደ አዲስ አበባ ታክሲ የሞላ፥ የሞላ እያለ እየጫነ ነው የእስካሁኑ ጉዞው የቀጠለው ፡፡ የእስካሁኑ የምትለውን ያዙልኝ !!

ጠቅላይ ሚንስትሩ የኤርትራን ልዑካን በተቀበሉበት ጊዜ ‘’የብሽሽቅ ፖለቲካ’’ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን እርግፍ አድርገን እንተወው ያሉ መሰለኝ፡፡ ትክክለኛውን አባባላቸውን ባላስታውሰውም ቅሉ፣ መንፈሱ ይህ ነው ፡፡ ድንቅ ሃሳብ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ግን አሁንም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው የሆኑትን ህወሀቶችንም ሆነ የእናት አባት ዘመዶቻቸው የሆኑትን “ዓጋሜዎች” ከማብሸቅ አልተቆጠቡም ፡፡ The game is over ! Woyane እያሉ እየተሳለቁባቸው ነው ፡፡ ይህ የብሽሽቅ ፖለቲካ ካልተባለ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል ?

የኤርትራው (አባትና መስራች) የተሰኙት ፕሬዚዴንት ሃገራቸውን ከነስሟ ሃገረ ኤርትራ /State of Ertrea/ ተብላ አንድትሰየም የፈለጉበት ምክንያት “ሃገራዊነቷ” እንዲደላደልና እውቅና ተጎናጽፎ አንዲቀጥል ነው፡፡ ፕሬዚዴንቱ ግን ስለበይነ መንግስታት ግንኙነት ሳይሆን በአወቅሁሽ ናቅሁሽ ወያኔ ጋር አተካራ ለመግጠም የመረጡ ይመስላል፡፡

በሰመራ ከተማ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የተሰበሰቡት የአፋር ሽማግሌዎች በኤርትራ አፋሮችና በአሰብ ወደብ ጉዳይ እኛም እንካተት የሚል ማሳሰቢያ ነበር እንጂ የመሬት ጥያቄ አላነሱም፣ እንዲያውም የመሬት ጥያቄ የላቸውም፡፡ ለምን ቢባል መልሱ ድንበር ዘለል የሆኑት አፋሮች ከኤርትራ ውስጥ ከተካለሉት ዘመዶቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትና ትሥሥር፥ ዝምድና አንድ ነን ባይነት ፣ ‘’ትግርኛ ተናጋሪዎች’’ እርስ በርስ ካላቸው ዝምድና ከስር መሠረቱ ይለያል፡፡ 

ትግርኛ ተናጋሪዎች ያልኳቸው በአንድነት እንደ አፋሮቹ፥ ኩናማዎቹ ፥ ሳሆዎቹ ፥(ኢሮብ) የወል መጠሪያ ወይም መታወቂያ ስያሜ የለንም ባዮች ስለሆኑ ነው፡፡ አንዱ የችግሩ ምንጭ እዚህ ላይ ነው፡፡ ወደ ታሪካዊው ዳራው የኋሊት መፍሰስ ያስፈለገውም ስለዚህ ነው፡፡
 

በአጭሩ የሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪዎች (ተዛረብቲ ትግርኛ) ውዝግብ መንስዔው ገሚሱ ታሪካዊ ተበደልኩ ባይነት ሲሆን ገሚሱ ደግሞ አንዲያው የስነ ልቡና ቁጥርጥር (Complex) ውጤት ነው፡፡ ለዚህም ነው አሁንም ጥንቃቀቄ ያስፈልጋል የምንለው፡፡ መቼም ከ1983-1990 ወደ ነበረው ህንፍሽፍሽ (ምስቅልቅል) እንደማንመለስ ተስፋችን የጸና ነው፡፡

ፈረንጆች የሁለቱ ጦርነት sensless war (ትርጉም አልባ)፥ ትሥሥሩ ደግሞ የወንድማማቾች አምባጓሮ/ brothers at war እያሉ ለመረዳት ያስቸገራቸውና ምስቅልቅሉን ለማስረዳት ብዙ የባጁት፡ የተባበሩት መንግሥታት ድንበር አካላዩ ኮሚሽን ድንበሩን ሲያካልል ወደ አፋር ክልል (ኢትዮጵያ) ያካተተው ሰፊ መሬት አለ፡፡
 

ለምሳሌ የቢሩ ሱልጣኔት የተሰጠው መሬትና አዩማን የተባሉት አካባቢዎች ሁለት ወረዳዎች ሊወጣቸው የሚችል ሰፊ የኢትዮጵያ የአፋር መሬት ነው፡፡ ስለዚህ መሬት ወያኔ አልተቸገረም አውርቶም አያውቅም፡፡ አፋሮችም አልተወዛገቡም፡፡ መሬቱ የአፋር ጎሳዎች መሬት እስከሆነ ድረስ ለነሱ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለባለቤትነት መወዛገባቸው ከቁባቸው አልገባም፡፡ ድንበሩም ለነርሱ ‘’ትርጉም’’ የለውም ማለት ማጋነን አይደለም፡፡

No comments