Latest

Video: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለኤርትራ መንግሥት ከፋተኛ የልኡካን ቡድን አቀባበል አደረጉ


የኤርትራ መንግሥት ከፋተኛ የልኡካን ቡድን በዛሬው እለት አዲስ አበባ ገብቷል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።


በተጨማሪም የሀይማኖት አባቶች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች የህብረተሰብ ተወካዮችም ለልኡኩ አቀባበል አድርገዋል።

ወደ አዲስ አበባ የመጣው የኤርትራ ልኡክም የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህ ናቸው።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባሳለፍነው ሳምንት በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የሀገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ማሰባቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ነው የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኩን በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ የላከው።

ልኡኩ በአዲስ አበባ ቆይታውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የሚወያይ መሆኑንም ለማወቅ ችለናል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን መግለጹ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

No comments