Latest

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሀዋሳ ያደረጉት ሙሉ ንግግር


የተከበራችሁ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፤ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፤ የሀዋሳ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ክቡራትና ክቡራን።

ታቦር ተራራን ከራስጌ፣ የሀዋሳ ሀይቅን በግርጌ አድርጋ ከዕድሜዋ በላይ በፈጣን የእድገት ግስጋሴ ላይ በምትገኘው የክልሉ መዲና በሆነችው በውቢቷና የፍቅር ከተማ ሀዋሳ እና በእንግዳ ተቀባይ ሕዝቦቿ መሀል በመገኘቴ የተሰማኝን ልባዊ ደስታና ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ኢትዮጵያዊነት በህብረ ብሔራዊ ቀለማት ያጌጡ የአንድነትና የአብሮነት ረቂቅ ሸማ ድርና ማግ ሆኖ የተወዳጀበት የታላቋ የኢትዮጵያ ነጸብራቅ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የዚህ ክልል ህዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ የረጅም ዘመን ታሪክ እና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ነው፡፡ ከአራት ሺህ አመታት በላይ የዘለቀ እንሰትን ጨምሮ የሠብል ልማት እርሻ፣ የሥነ ጥበብና እደጥበብ ሙያ፣ የተለየ የዘመን አቆጣጠር፣ የተደራጀ ጥንታዊ አስተዳደርና ፖለቲካ ሥርዓት ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ያሉበት ክልል ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን
የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትናንትም፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር ከተቀረው የሀገራችን ሕዝብ ጋር በአብሮነት በመሰለፍ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ታላቅ ጀግንነት የፈፀም ህዝብ ነው፡፡ የክልሉ ሕዝብ በቀጣይነትም ኢትዮጵያ ሉላዊንቷን ጠብቃ እንድትቀጥል በከፍተኛ የአርበኝነትና የሀገር ፍቅር ስሜት የድርሻውን በመወጣት ለሀገራችን ህልውና አለኝታ እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለኝ፡፡

ይህ ህዝብ በሠላም ለመጡበት ሁሉ እጁን ዘርግቶ ፣ያለውን አካፍሎ፣ መኝታውን ለቆ በአብሮነት ለመኖር ከፊት ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ በሀገር ባለቤትና በማንነታቸው ኮርተው ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በወንድማማችነት በጋራ ለመኖር ለዘመናት ያካሄዱት የአርበኝነት ተጋድሎ እና የተከፈለው መስዋዕትነት የምንዘክረው ብቻ ሳይሆን ዘብ የምንቆምለት አላማ ነው፡፡ የሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ቀቤና፣ ሀዲያ፣ ማረቆ፣ ስልጤ፣ ጌዴኦ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ፣ጎፋ ፣ የም፣ አይዳ፣ ባስኬቶ፣ ከምባታ፣ ሀላባ፣ ጠምባሮ፣ ዶንጋ፣ ቡርጂ፣ ኮንሶ፣ ደራሼ እና ኮሬ ህዝቦች ያደረጉትን የሞት ሽረት ትግልን በማስታወስ የሚያበቃ ሳይሆን የካፋ፣ ቤንች፣ ሸካ ፣መኢኒት እና የደቡብ ኦሞ ህዝቦች እስከ አድዋ ጦርነት መባቻ ድረስ ገባርነትን መከላከል ችለው እንደነበር ታሪክ የሚዘከረው ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን
ይህ ክልል በልዩነት ውስጥ አብሮ መኖር አንደሚቻል ያስመሰከረና አርዓያ መሆን የሚችል ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ ጠንካራና ፅኑ የሆነ አንድነትና ያለው፣ አንዲሁም ግሩም የሆኑ የጋራ እሴቶች ባለቤት የሆነ ህዝብ መኖሪያ ክልል ነው፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአብነት ያክል በባህላዊ የቤት አሰራር፣ የእንሰት አመራረትና ዝግጅት ፣ በህዝባዊ በዓላት አከባበር እንዲሁም በሀገር በቀል እውቀቶች አጠቃቀም እና በመሳሰሉት ለበርካታ ዘመናት የዘለቀው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶች የክልሉን ህዝብ የሚያስተሳስሩ የጋራ እሴቶች ፈጥረዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ለረጅም ዘመናት ሲተዳደርባቸዉ የነበሩ የየራሱ የተደራጀ ጥንታዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ስርዓት ያላዉ ብቻ ሳይሆን የራሱን መሪ የሚሰየምበት የስልጣን ርክክብ የሚያከናወንበት፣ የሀሳብ ልዩነቶችን የሚያስተናግድበት ፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት፣ በቋንቋው የሚዳኝበት፣ ማንነቱን የሚገልጽበት፣ የጀግንነት ተግባር የፈጸሙትን የሚበረታታበትና የሚሸልምበት የዳበረ ጥንታዊ ባህላዊ የአስተዳዳር ስርኣት ባለቤት መሆኑን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም የሚታይ እውነታ ነው፡፡

በመሆኑም አልፎ አልፎ በራሱ ዉስጥም ሆነ ከአጎራባች ወንድሞቹ ጋር የሚከሰቱ ለህይወትና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በማስወገድ፣ ጥንታዊ ባሕላዊ ስርዓቱን በማጠናከርና በመጠቀም ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለማስቀጠል የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም፡፡ በዚህም ረገድ የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን አበክሮ የሚሰራ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልገልፅላችሁ እወዳለሁ፡፡

ክቡራንና ክቡራን
ክልሉ በአመዛኙ የመሬት ጥበትና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር መጨመር ከሚስተዋልባቸው የሀገራችን ክፍሎች መካከል አንዱ በመሆኑ በክልሉ የተመዘገበው ፈጣን እድገት የሁሉንም የክልሉን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳላስቻለ ከህዝቡ የዕለት ተለት ኑሮ የምንረዳው ነው፡፡ በጤና ፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በመብራት፣ በውሃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለማደረስ የተደረገው እንቅስቃሴ ረጅም ርቀት መጓዙ የሚካድ ባይሆንም ከህዝቡ ፍላጎት አንፃር ግን ገና ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ሠፊ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ሀቅ ነው፡፡


ይህን እውነታ ለመለወጥ የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በየትኛውም ደረጃ ስራ ሳይንቁ ሰርተው ለመለወጥ ደፋ ቀና የሚሉ የክልሉን ሕዝቦች ከጎናችን በማሰለፍ በአጠቃላይ የክልሉን ሕዝብ ሕይወት በተለይም የወጣቱን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ በትጋት እንሰራለን፡፡

እዚህ ላይ ግን ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ “ወንዝ ዳር ቆማ የምትጠጣው ውሃ ከሠማይ እስኪዘንብ እንደምትጠብቅ ወፍ” እግርና እጃችንን አሳስረን መቀመጥ አይኖርብንም፡፡ የደቡብ ክልል ሕዝቦች ታታሪ ሠራተኛነት እና ድንቅ የመቆጠብና የመሻሻል መንፈስ ከራሳቸው አልፎ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን አብነታዊ ተምሳሌት ናቸው፡፡
 

ይህ ሕዝብ ጠንክሮ የመስራትን ብቻ ሳይሆን የመተባበርና መደጋገፍን ዋጋ አስቀድሞ በመረዳት ባንክ ሳይፈጠር፣ አክሲዮን ሳይመጣ ፣ሴፍቲ ኔት ሳይቋቋም በፊት ባህላዊ የእቁብና የእድር ስርዓትን የመሰረተ ለተቀረው የሀገራችን ሕዝቦችም ያሸጋገረ ሕዝብ ነው፡፡ 

በዚሁ ባህላዊ ሥርኣት ትናንት አያሌ የክልሉ እና የሀገራችን ሕዝቦች ችግርን ማሸነፍ እንደቻሉት ሁሉ የዛሬውም ትውልድ የአባት አያቶቹን ታታሪ ሠራተኛነት እና ድንቅ የመቆጠብና የመሻሻል መንፈስ ከመተባበርና መደጋገፍ ስርዓቱ ጋር በማስተሳሰር ለራስ፣ለቤተሰብ፣ለክልልና ሀገራዊ እድገት የልማት አርበኛ እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ከዚህ ቀደም በውጭ ሀገር ሰዎች የተያዙ የንግድ ስራዎችን በሀገር ዜጎች መተካት ሀገርን ፣ ከእጅ መጠምዘዝ የታደጉ በቤተሰብ የሚመራ ንግድ በኢትዮጵያ ያስተዋወቁ ቀደምት የልማት አርበኞች እንደነበሩ ፣ የዛሬዎቹ የእዚህ ክልል ህዝቦች በመረዳት መታወቂያችሁ የሆነውን ታታሪ ሠራተኝነትና ሀገር ወዳድነት በውስጣችሁ ሕያው መንፈስና የጉዞ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓስ በማድረግ ለሀገራችሁ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ዘብ በመቆም ታሪክ ትሰሩ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

ውድ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች
ይህ ክልል በመንደር፣ በአካባቢ ያልታጠረ አድማስ ተሻጋሪ አብሮ የመኖር ባህል ያለዉ ብቻ ሳይሆን ፣በግለሰብና ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሯዊ ሚዛን ተጠብቆ የሚኖርበትን ሀገር በቀል የግብርና፣ የተፈጥሮ ጥበቃ የህግና የአስተዳደር ሥርዓት ዛሬም ድረስ ማዝለቅ የቻለ ነዉ፡፡

በዚሁ ክልል የስምጥ ሸለቆ ትሩፋት የሆኑ የተለያዩ የውሀ ሀብቶች ለአብነት ያህል አባያ፣ ጫሞ፣ ሐዋሳ፣ የሩዶልፍ ሀይቆች፣ ኦሞ ወንዝ እና ሌሎችም የሚገኙበት ከመሆኑ በተጨማሪ ክልሉ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ለአብነት ያህልም የኮንሶ እርከን ስራ፣ ጢያ ትክል ድንጋይ፣ የካፋ የጫካ ቡና፣ የሲዳማ ፍቼ ዘመን መለወጫ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስ፣ የጌዴኦ ጥምር ግብርና ተጠቃሽ ሀብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው ሀብቶች የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚነት ማሳደግ ለሚችል ልማት መነሻ ብቻ ሳይሆኑ ደቡብንም የኢትዮጵያ እስትንፋስ የማድረግ አቅም የታደሉ ናቸዉ፡፡

በመጨረሻም በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉ ፣ ዳኤ ቡሾ፣ በላለዲ ይምጣ ፣በአፈር ንተን፣አሻም. . . በማለት በፍፁም ፍቅር እጆቹን ዘርግቶ ለተቀበለን ሕዝብና ለክልሉ አመራሮች እኔም ከወገቤ ዝቅ በማለት ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆችዋ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልፅጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ
አመሰግናለሁ!

No comments