የፀረ ሽብር ህግን ጨምሮ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ እንደ ችግር ለሚነሱ ህጎች የማሻሻያ ሀሳብ የሚያቀርብ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ ተቋቋመ
የፀረ ሽብር ህጉን ጨምሮ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ እንደ ችግር ለሚነሱ ህጎች የማሻሻያ ሀሳብ የሚያቀርብ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ ተቋቋመ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የተቋቋመው አማካሪ ጉባዔ 13 አባላት ያሉት መሆኑን አስታውቀዋል።
የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጆች በህዝቡ ዘንድ ሮሮ የሚነሳባቸው እና በግልፅ ባይሆንም ከህገ መንግስቱ ጋር ሲጋጩ ይስተዋያል ብለዋል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ።
በአማካሪ ጉባዔው ከላይ የተጠቀሱትን ህጎች ጨምሮ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማሻሻል የፖሊሲ አቅጣጫ ለመንግስት የሚጠቁም መሆኑንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል።
የፀረ ሽብር አዋጁን አስመልክቶም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ እንዳሉት፥ በጉባዔው ማሻሻያ የሚያስፈልገው ከሆነ እንዲሻሻል ካልሆነም የፀረ ሽብር ህጉ በሌሎች ህጎች የሚሸፈን ከሆነ አዋጁ የሚቀርበትን መንገድ ሊፈጥር ይችላል ብለዋል።
አማካሪ ጉባኤው ከህግና ፍትህ ስራዎች ጋር ለተያያዙ ስራዎች ሙሉ ነጻነቱ እንደሚጠበቁለት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ብርሀኑ ጸጋዬ ተናግረዋል።
መንግስት ከጉባኤው ለሚመጡ ሀሳቦች ተግባራዊነት ቁርጠኝነት እንዳለው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ተናግረዋል።
13 አባላት ያሉት ያሉት አማካሪ ጉባዔው በስሩ አምስት ቡድኖች እንዳሉትም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ፀጋዬ ብርሃኑ አስታውቀዋል።
የጉባዔው አባላት የተመረጡት በትምህርት ዝግጅት፣ በስራ ልምድና በሀይወት ተሞክሮ ተመዝነው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ ከአባላቱ መካከል ዶክተር በላቸው መኩሪያ፣ ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፣ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ አቶ ታምሩ ወንድማአገኝ እና አቶ አሊ መሃመድ እንደሚገኙበት አንስተዋል ።
በአማካሪ ጉባዔው በሚያደርገው ስብሰባም ደንቡንና በብሳቢውን መርጦ ወደ ስራ እንደሚገባም ገልጸወዋል ።
አማካሪ ጉባዔው የሶስት ዓመት ቆይታ ያለው ሲሆን፥ እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ የቆይታው ጊዜ የሚራዘም መሆኑንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል።
አማካሪ ጉባዔው መንግስትን የሚያማክር አንደመሆኑ በጀቱ በመንግስት የሚመደብለት ይሆናል ብለዋል።
በካሳዬ ወልዴና ባህሩ ይድነቃቸው
No comments