ከታሪክ መድረክ ~ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትላንት እና ዛሬ። በኀይሌ ላሬቦ (ክፍል ፩)
ጽሑፌን የኢትዮጵያ ጠቅላይ መሪ የነበሩት አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው በፊት ከተናገሩት ልጀምር። “ይኸ መሥርያ ቤታችን ዐይነተኛ መረጃ አለን ወይ ውሳኔ ልንሰጥ የሚያስችል ወቅታዊ የሆነ መረጃ አለን ወይ። እኔ ርግጠኛ ነኝ። አሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ውስጥ [ውሳኔ ሊያሰጥ የሚያስችል መረጃ] አለን ብዬ ለመናገር የሚያስችል አፍ የለኝም። ሰዎች በተናገሩት ላይ ተመሥርቼ ነው እየወሰንሁት ያለሁት እንጂ በጣም ወቅታዊ የሆነ ታች ያለውን መረጃ አግኝቼ በዚያ ላይ ተመሥርቼ ውሳኔ እየሰጠሁ ነኝ ብዬ ለማለት አልችልም። እያንዳንዳችሁም እንደዚያ እንደሆናችሁ ርግጠኛ ሁኜ ለመናገር እችላለሁ።
በመሥርያ ቤቱ በምትሠሩት ሥራ በቂ መረጃ ወቅታዊ የሆነ መረጃ እንደዚሁም ደግሞ የመረጃ ሥርዐት የተዘረጋበት ሁናቴ የለም።” (ጠቅላይ አስተዳዳሪ ኀይለማርያም ደሳለኝ) ከሺስድሳዎቹ ዓ. ም. ጀምሮ በአገራችን የታየው ሁናቴ ይኸንን የጠቅላይ መሪውን ንግግር ያንጸባርቃል ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አብዛኞቻችን ምንም ሳንመረምርና ሳንጠይቅ እንደማያከራክር እውነት አድርገን የተቀበልናቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
የሺስድሳዎቹ ተማሪዎች ባልተጨበጠና በምርምር ባልተደገፈ፣ ብዙም ስለአገራችን በቂ ዕውቀት በሌላቸው ባንዳንድ ምዕራባውያን ምሁራን መረጃዎችና ከጥራዘነጠቅነት የማይሻሉ አወናባጅ ጥናቶችና ምርምሮች በመመርኰዝ፣ ወይንም ምንም ባልተረዱት በነማርክስና በነሌኒን ርእዮተ ዓለም ብቻ በመመሠረት፣ እጅግ ከሐቅ ወደራቀ ድምዳሜ ደርሰው፣ አገሪቷን እከፍተኛ ጥፋት ላይ ለመጣል በቅተዋል።፡
በግለሰብ ደረጃ በዚህ መልክ የሚሠራ ሥራ እጅግ ያስነውራል። በአገር ደረጃ ከሆነ ደግሞ፣ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ምስቅልቅልና ትርምስምስ ይፈጥራል። የሺስድሳዎቹ ተማሪዎች ወጣት ልጆች እንደመሆናቸው አእምሯቸው ብስለትና ሚዛን በተነፈገ፣ ከጫቅላነት ባልተላቀቀ የዕድሜ ጣራ ውስጥ ነበሩ። በጊዜያቸው ከፍተኛ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያለው፣ በየአቅጣጫው ይነፍስ የነበረው፣የግራዘመም ርእዮተ ዓለም ሰለባ መሆናቸው አይገርምም ይሆናል። ችግሩ በሽምግልና ዘመናቸውም ያንኑ የተዛባና የተጣመመ አስተሳሰባቸውን እንደማያከራክር እውነት አድርገው መውሰዳቸውና አለመታረማቸው ነው።
አሁንም እንደድሮው፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመቶ ዓመት በላይ እንዳላለፈ ይተርታሉ፤ የአገሪቷንም ማኅበራዊ አወቃቀር በበዝባዥና በተበዝባዥ፣ በጨቋኝና በተጨቋኝ መከፋፈላቸውን አልተውም። አገሪቷ ትተዳደር የነበረችውና የተመሠረተችው፣ አብዛኞቹን ብሔረሰቦች ጨቈኖ ይገዛ በነበረ ባንድ ብሔረሰብ ጉልበት ነው ብለው ማውራቱን እንደቀጠሉ ነው። ተማሪዎቹ፣ለጭቈናው መፍትሔ ብለው ያቀረቡት፣ ላገሪቷ ባዕድና ፋይዳቢስ የሆነ፣ የግራዘመም ርእዮተ ዓለም በግድ በሕዝቡ ላይ እንዲጫን በመስበክ ነበረ።
አጋጣሚም ሆነና፣ የዘውዱን ሥርዐት ገርስሶ የተተካው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ ጩኸታቸውን ቀምቶ ስብከታቸውን በዐዋጅ ኀይል በግብር ላይ ሊያውለው ሞከረ። ግን ምንም ሳይሠራለት ቀረ ብቻ ሳይሆን፣ ከልክ በላይ እየተፋጠነ ይሄድ የነበረውን የአገሪቷን ዕድገትና ልማት ወደመቶ ዓመት ወደኋላ ለመቀልበስ በቃ።
ደርግን ደምስሶ የመጣው፣ አሁን በሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሳዊ ግንባር [ኢሕአዴግ] በመባል የሚታወቀው በዳግማዊ ወያኔ የሚመራው አገዛዝ፤ የተማሪዎቹን ኮቴና ፈር በመከተል የመጡት የጐሣ ታሪክ አቀንቃኞች ጥርቅም መሆኑ መረሳት የለበትም። ይኸም አገዛዝ በበኩሉ፣ በተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ወቅት ይነዛ የነበረውን የጐሣ ሥርዐት አንግቦ ብቅ ያለው፣ እንደግራዘመሞቹ ተማሪዎች ምንም ዐይነት ጥናትና ምርምር ያልተደረገበት፣ በታሪክ ሳይሆን በተረትና በጥላቻ ላይ የተገነባ፣የጠላና የቡና ቤት ወሬ እንደማስረጃ አቅርቦ፣ በጦር ኀይል በማሳመን ነው።
የርሱም ርእዮተ ዓለም ልክ እንደደርጉ ከኢትዮጵያ ታሪክ የማይጣጣም የፈጠራ ተረት እንደመሆኑ፣ ሥርዐቱ በየቦታው እየተመታና ፍርስርሱ እየወጣ እንደሆነ፣አሁን ጊዜ ሁላችንም እያየን ያለነው ሐቅ ነው። ደርግ የኢትዮጵያን ዕድገት በመቶ ዓመት ወደኋላ ሲቀለብስ፣ ኢሕአዴግ ደግሞ አንድነቷን በመቦርቦርና በማዳከም፣ ወሰኗንና ልዑላዊነቷን በማስደፈር፣ ታሪኳን በማስነወር፣ ማንነቷን በመናድ፣ ከስድስት ሺ በላይ ዓመታት በጋብቻና በአምቻ በመተሳሰር፣ በባሕልና በቋንቋ በመወራረስ፣ በፍቅርና በመልካም ጉርብትና የኖረውን ሕዝብ፣ባሰኘው መልክ በፈጠረው ክልል አደራጅቶ፣ ርስበርስ በማጋጨትና በመከፋፈል፣ በማጣላትና በማጥላላት፣ ከወታደራዊ መንግሥት በከፋ ሁናቴ፣ ቢያንስ በሦስትና በዐራት መቶ ያህል ዓመታት፣ ወደኋላ መልሷታል ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ግፍና ወንጀል ፈጽሟል ማለት ይቻላል።
የዛሬው ጽሑፌ ዋና ትኩረት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምንድር ነው በሚለው ላይ ነው። አንድ ሕዝብ ማንነቱን ካላወቀ ነፍሱን እንደሳተ ግለሰብ ነው። የሁሉም መሣለቂያ፣ መዘባቻ ይሆናል። ከየት እንደመጣ፣ ለምንስ ባለበት እንዳለ፣ የትስ እንደሚሄድ ይጠፋበታል። ለኔ ታሪኩን የማያውቅ ሕዝብ የጉዞን መነሻና መድረሻ እንደማያውቅ በባሕር ላይ እንደተንሳፈፈ መርከብ ነው። በየጊዜው በሚነሣው ማዕበልና ነፋስ እየተመታ የመስጠም ወይንም የመዘረፍና የመጥፋት ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደአገርና ሕዝብ ማንና ምን እንደነበሩ ማወቅ አሁንም ያሉበትን ሁናቴ ለመገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ የወደፊቱንም የአገሪቷንም ሆነ፣ የመጪውን የታሪክ ተረካቢ ትውልድ ዕጣና ዕድል በትክክል ለመተለም ይረዳል። ከዚያም አልፎ ያላቸውን ብሔራዊ የተፈጥሮ ሀብትና የቅድመ አያቶች የኪነጥበብ ቅርስ፣ በደምብ አድርገው ተረድተው፣ የራሳቸው የታሪክ ድርሻ ምን መሆን እንደሚገባው፣ ከሌላውስ ምንና ምንስ ያህል መዋስና አለመዋስ እንዳለባቸው፣ ጥርት አድርገው እንዲያውቁ ያግዛል። ጽሑፌ አለቅጥ ረጅም ቢሆንም፣ ውድ አንባቢዬ በትዕግሥትና በርጋታ እስከመጨረሻው ከማንበብ እንደማይቦዝኑ ርግጠኛ ነኝ። ካልሆነም ተስፋ አደርጋለሁ።
ንግግሬ፣ በመጀመርያ ደረጃ የውጭ አገር ጸሓፊዎች ካላቸው ዕይታ በመነሣት፣እነሱ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያሉትን፣ አንዲሁም ኢዮጵያም ለውጭ አገሮች ያበረከተችውን አስተዋፅዖ ይቃኛል። ቀጥሎም የነዚህን ገለጻና አስተያየት፣በአገር ውስጥ ከነበሩት ሁናቴዎችና ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር በማነፃፀር ያገናዝባል። ከዚያም፣እንዴት አሁን ወዳለንበት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውነትን ወደመሸራረፍና ወደመሰርሰር ሁናቴ እንደመጣን በአጭሩ ተመልክቶ ይደመድማል።
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያን ታሪክ ማኳሰስ፣ መሬቷን ማንቋሸሽ፣ ምንነቷን መካድ እንደሙያቸው አድርገው በየቦታው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች እየተራቡና እየበረከቱ ነበሩ ሊባል ይቻላል። እነሱ የሚነጋገሩባትን ኢትዮጵያን የሚደግፉ መዛግብት ግን በየትም በኩል፣ በምንም መልክና ደረጃ እስካሁን ድረስ ብቅ አላሉም። ወደፊትም ይገኛሉ ብዬ ከቶውኑ አላምንም።
በውጭ አገር ጸሓፊዎች ስለኢትዮጵያ ብዙ ተብሏል። ግን ከጥንት ጀምሮ ተደጋግሞ የሚነሣ ነገር ቢኖር፣ አገሪቷ እጅግ በጣም ጥንታዊት፣ ነፃነቷንና ልዑልናዊነቷን ጠብቃ የኖረች፣ ረጅምና አስደናቂ ታሪክ ያላት፣ በመሬቷ አቀማመጥና ሀብት አስቀኚ መሆኗ ነው። ስለሕዝቧ ደግነትና ልበሰፊነት፣ ሕግ አክባሪነትና ጀብዱነት፣መንፈሳዊነትና ታታሪነት፣ ስለገዢዎቿ ፍትሕና ርትዕ ወዳድነት፣ እንዲሁም ነገሥታቱ በቅንነታቸው የሚደነቁ፣ ስለአገራቸው ጥበቃና ስለሕዝባቸው ደኅንንት ከማንም ጋር የማይደራደሩ ስለመሆናቸው በሰፊው ይነገራል።
ይቀጥላል
No comments