Latest

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የሰላም ጥሪን ተከትሎ በብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሚያ አንድነትና ነፃነት ግንባር ልዑክ አዲስ አበባ ገባ

በብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ ሀገር ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግንባር ልዑክ ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑኩ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በዛሬው እለት አዲስ አበባ የገባው የኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግምባር ልኡክ የድርጅቱ አመራሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ዘጠኝ አባላትን የያዘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ ሀገር ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ፣ በሀገር ግንባታ ሂደቱም በጋራ እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግንባርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ተከትሎ ነው የትጥቅ ትግል በማቆም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር የገባው።

የኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግንባር ልዑክ መሪ አቶ ተማም ባቲ በሰጡት መግለጫ፥ ፓርቲው ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ከዚህ ቀደም ከመንግስት ጋር በተደረገ ውይይት በቀጣይ በሚያደርጉት የፖለቲካ ተሳትፎ መግባባት ላይ በመድረሳቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም በቀሪ ጉዳዮች ጋር ከመንግስት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች መኖራቸውንም የልዑኩ መሪ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግንባር በቀጣይ በህጋዊ መንገድ በመመዝገብ ሰላማዊ ትግል እንደሚያደርግ እና በሀገሪቱ የተጀመሩ ለውጦችን ለማስቀጠል ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የጀመራቸውን ስራዎች እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በይቅርታ መልቀቁንም አድንቀዋል።

አቶ ተማም ባቲ መንግስት ላደረገላቸው የሰላም ጥሪ እና ለህዝቡም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፥ የኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግንባር የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የትጥቅ ትግልን በመተው በህጋዊ መንገድ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ወደ ሀገር በመግባቱ አመስግነዋል።

መንግስት በቀጣይም ከኦሮሚያ አንድነት እና ነፃነት ግንባር ጋር በቀጣይ የተለያዩ ውይይቶችን የሚያደርግ መሆኑን ነው አቶ አህመድ የገለፁት።

ሌሎች በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ሀይሎችም በመንግስት የቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።

ከልዑኩ ጋር የግንባሩ መሪ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ እንዳልመጡ ለማወቅ ችለናል።
በፋሲካው ታደሰ

No comments