Latest

እ ገ ዛ ላ ታ ለ ሁ..........!! (አሌክስ አብርሃም)


ቆንጆ ማለት ለአይን የሚማርክ ፣የሚያምር፣ የሚያስደስት. የሚያማልል፣ ፣ ሰው፣ እንስሳ ፣ሳር ፣ቅጠል፣ አየር ፣ ውሃ፣ ቃል፣ ሁኔታ፣ ድርጊት፣ ሌላም መአት ትርጉም ይኖረዋል ...አሻሚ ነው ቃሉ......

‹ውብ› የሚለው ቃል ግን አያሻማም አያደናግርም ‹‹ውብ ›› ማለት ‹‹እናቴ›› ማለት ናት! የእኔ እማማ ብቻ( !! )

አዎ እናቴ ውብ ናት !! ...በችግር የማይፈታ ውበት ... ማንም በአድናቆት ቃል በእንቶፈንቶ ድለላ ውሉን እጁ አስገብቶ የማይተረትረው ነጭ ቱባ!! ፈገግ ስትል ከጥርሶቿ ድል ማድረግ ይነዛል !!... እንደናቴ ፈገግታ ልብ የሚሰነጥቅ ሳቅ አላየሁም ..... የእናቴ ፈገግታ ብርታቴ ነው ሰውነቴ በፈገግታዋ ይታደሳል ...የተፈጥሮ ፍልውሃ !!

ሂወት ወገቧን አስራ ልታስለቅሳት ድንጋይ ስትፈነቅል እናቴ ...እማምየ ....የኔ ፀሃይ.... በአንዲት የአሽሙር ፈገግታ ትደቁሳታለች (ሃሌ ሉያ) !! ሂወት የጨለማ አረሟን በቤታችን ላይ ስትዘራ እናቴ በፈገግታዋ ትመነጋግለውና የደስታ እና የሃሴት አዝመራ ቤታችን ይዘናፈላል... እኔ እዛ ማሳ ውስጥ እቦርቃለሁ፡፡ ... አውቆም ይሁን ሳያውቅ አባቴ ቤታችንን የምድር ዋልታ ላይ በበረዶ ሰራው...እናቴ በፈገግታ ገመድ ጎትታ መሃል አዲስ አበባ ..አራት ኪሎ... ፀሃይ የሞላበት አመጣችው ቤቱን ከነግቢው ከነዛፉ !!! እንደዛ ነው የሚሰማኝ !

አባቴ በውትድርና ኤርትራ ሄደ..... ‹‹ እነከሌ አገር ሊገነጥሉ መሬት ሊሸርፉ ነውና ና ሂድህ ልክ አግባቸው ›› በሚል ትዛዝ.... ከእኔ ከልጁና ከሚወዳት ሚስቱ ተነጥሎ ሄደ!! ‹‹....አቤት ቁመና አቤት የትጥቅ ማማር እያለ ጎረቤቱ ሸኘው... (አምሮ ሊገድል አምሮ ሊሞት) ህፃን ነበርኩ ብዥ ያለ ነው ትዝታየ !! አባቴ ሄደ (ዘመተ ይሉታል) ስልክ የለም ደብዳቤ የለም ! ሄደና ጠፋ!!

እናቴ ታዲያ በፍፁም ንፅህና ስድስት አመት ጠበቀችው .... ያውም በደጃችን በእናቴ ውበት... መቶ ጀኔራል እየሸለለ ሽ ካድሬ እየቋመጠ ሚሊየን አብዮት ጠባቂ ምራቁን እየዋጠ !! (ንፅህናዋን በምን አወክ ?)... ስድስት አመት ሙሉ ማታማታ አንዲት ቀን ሳታቋርጥ ፎቶው ፊት ተንበርክካ ምን እያለች ትፀልይ እንደነበር እናተ ታውቃላችሁ ...? የአባቴን ፎቶ አቧራ ዝር እንዳይልበት በቀን ስንት ጊዜ ትወለውለው እንደነበርስ .... ? ከቤታችን እቃወች ውድ የተባለው መደርደሪያ ላይ ምን ይቀመጥ ነበር ?...የአባቴ ፎቶ ...!!

ተሳስቸ ደብተሬን ባስቀምጥ ሳታስደነግጠኝ ቀስ ብላ ታነሳዋለች !!... ቤት ለማዘጋጀት እንዳይመስላችሁ አባቴ ፎቶ አጠገብ ምንም እንዳይቀመጥ !! የቃል ኪዳን ቀለበቷን ሽጣ ምን ገዛች...? ለኔ ቆንጆ ጫማና ልብስ ..ምድረ የትምህርት ቤት ማቲ የቀናበት የደብተር መያዣ ቦርሳ ....ላባቴ ፎቶ ወርቃማ ክፈፍ ያለው የብረት ‹ፍሬም› ...በተረፈችው የቃል ኪዳን ቀለበቷን የምትመስል አርቲፊሻል ቀለበት ! በእንቁ ልብና በአርቲፊሻል ቀለበት ቃልኪዳኗን አጠረች (ከእኔ በስተቀር ይሄንን ማንም አያውቅም ) ለእራሷስ ምን ገዛች ?....ምንም !! እች ናት እናቴ!!

ስድስት አመት አባቴን ጠበቀች...(ይሄ...‹ ሊመጣ ይችላል› ተብሎ እዛም እዚህም እየተባለ የሚጠበቀው አይነት ጥበቃ ሳይሆን ‹መቸ ሄደና› ብሎ ክችች አይነት የመንፈስ አብሮነት! በሌሉበት ማክበር!! ...ይሄ የመጀመሪያው አመት ላይ ሄደብኝ የኔ ጌታ የልቤ ቁራሽ የደሜ ጭላፊ...እያሉ ጎረቤት እንዲያባብል ድራማ መስራት አመት በጨመረ ቁጥር ‹አሁን ተፅናናች ሰው መቅረብ ጀመረች› የሚባለው አይነት መጠበቅ ሳይሆን ትላንትም ዛሬም አመታት ጉልበቱን በማይሰልቡት ጥልቅ መሻት ጠበቀችው) እች ናት እናቴ!!

ስለኤርትራ በተወራ ቁጥር እንደኤርትራ ኪሎ ስጋ ከአካሏ እየተገነጠለ ጠበቀች!!...‹‹ከኤርትራ የመጣ ሰው በኮተቤ አለፈ›› ቢሏት ነጠላዋን አንጠልጥላ ኮተቤ ትገኛለች ...አንዲት ኤርትራዊት ተፈናቃይ አቃቂ ኪወስክ ከፈተች ቢባል ከአራት ኪሎ እየተመላለሰች የስሙኒ ሻይቅጠል ለመግዛት ደንበኛ የምትሆን ሴት ካለች .... እናቴ ብቻ ናት !!

እርጋታዋ..... የእኔ እማማ በ ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ›› ተረት እልፍኛቸው ውስጥ ተላላፊ እንደሚያበዙ ሴቶች አይደለችም! ማንም የቃል ኪዳን መስመሯን አያልፍም... አገር ያውቃል .... ቤታችን ቤተ መቅደስ ነው ...የፍቅር ፅላት በቅዱሰ ቅዱሳን እማማ ልብ ውስጥ አለ! እርጋታዋ ታማኝነቷን ይነግረኛል ...አይኗ ከአባቴ ፎቶ ላይ ከተነቀለ ቀጥሎ ማረፊያው እኔ ላይ ነው ....ጆሮዋ ወደውጭ አይቀሰርም የኔን አርቲ ቡቲ ወሬ እንደወንጌል በጥሞና መስማት ...የነፍሷ እርካታ ነው ...አባቴ መፅሃፍ ቅዱስ እኔ ይኋንስ ራእይዋ .... ታነበኛለች ሰባት ቀንድ አስራ ስድስት ምላስ ምንም ጆሮ የሌላቸው ልዩ ፍጥረቶች መሃል እናቴ ጆሮ ብቻ ሁና ትሰማኛለች....!!

ጥቁር ፀጉሯ ሲዘናፈል...እንደማር የለሰለሰ ቆዳዋ አላፊ አግዳሚ ሲጠራ..እረጋ ባለ እርምጃ እንደደመና ስትንሳፈፍ ....‹‹ፈዛዛ ... ውበቷን አቀለጠችው›› ይሏታል ....‹‹ጎታታ ... እንደኤሊ ስትንቀረፈፍ እድሜዋን ፈጀች›› ይሏታል.... በሌጣ ልባቸው ሩጠው ምናምንቴ ስለቃረሙ የፈጠኑ እየመሰላቸው!! የፍቅር መስቀል ተሸክማ ዳገት የምትወጣ እናቴን .... ኤሊ ይሏታል ...አፍ አውጥተው ... ኤሊ ይሏታል ... የድንጋይ ልባሷ አንደነሱ ቀሚስ የትም ለማንም አለመገለቡ እያበገናቸው ...ተኳኩለው የሚጠብቋቸው ወታደር ውሽሞቻቸው ያልተኳኳለች እናቴን እያዩ ‹‹ማናት እች ቆንጆ?›› ሲሏቸው እየበሸቁ....

ስድስት አመት ጠበቀችው አባቴን ......‹‹እስካሁን ባሏ ከአስመራ ቆንጆወች ጋር አሸሼ እያለ ነው.... እሷ እዚህ ትጠራሞታለች ›› እያሏት ጎረቤቶቻችን!! (አስመራ አድረው ጧት አዲስ አበባ የገቡ ይመስል) ...‹‹ለታመነልህ ታመን ›› የቆሸሸ ዲስኩራቸው ‹‹በአልታመኑልንም›› ሰበብ ባሎቻቸውን እንዲክዱ ፍቅረኞቻቸውን እንዲቀጥፉ መንገድ እየጠረገላቸው ....ለውስጣቸው ግልሙትና ጥቅስ...እየሆነላቸው.... የአስመራን ግልሙትና በአዲስ አበባ ግልሙትና መበቀል ፅድቅ ነው የተባለ ይመስል... እማምየን (ባልሽ ወንድ ነው አትመኝው) ይሏታል

አንድ ማለዳ በራችን ተንኳኳ ከፈተች ጎረቤቶቻችን የተበሳቆለ ወታደር አስከትለው ‹‹ ባልሽ ሙቷል›› አሏት !! ‹‹ በዛ ሂዶ በዚህ ወርዶ መድፍ ተኩሶ ታንክ ማርኮ በጀግንነት ሞተ›› አሏት!! ዝም ብላ ሰማቻቸው ...ሰው ቀጥ ብሎ የማያይ ጨዋ ለትዳሩ ታማኝ ወታደሩ ሁሉ ሲልከሰከስ እሱ የአንችን ፎቶ ከደረት ኪሱ ሳይለይ በየበረሃው ለአገሩ ሲፋለም ኑሮ ሞተ አሏት ....ዝም ብላ ሰማቻቸው

አባቴ ሲሞት ‹‹ከጎኑ ነበርኩ›› ያለው በስቋላ ወታደር ከአባቴ ሬሳ ኪስ ውስጥ አገኘነው ያለውን ፎቶ ሰጣት .... እናቴና አባቴ ጎን ለጎን ሁነው የተነሱት ጉርፍ ፎቶ ግራፍ ነበር!! ልክ መሃላቸው ላይ በጥይት የተቦደሰ ፎቶ!!! እን...ዴ ! በመድፍ ጥይት ነው እንዴ ፎቶውን የበሱት ? እና እንዴት አንዲት ጥይት በቤተሰብ መካከል ይሄን የሚያህል በደም ነጠብጣብም የተከበበ ሽንቁር ትፈጥራለች ?

‹‹ባለቤትሽ ደረቱ ኪስ ነበር ፎቶውን የያዘው... ከጠላት የተተኮሰ ጥይት ፎቶ ባስቀመጠበት ኪሱ በኩል ደረቱን መታችው›› ፎቶውን በትኩረት አየችው .... አላለቀሰችም... ፊቷም ላይ ምንም ለውጥ አልታየም ከፎቶው ይልቅ ሽንቁሩን የምታይ መሰለኝ ....ዝም አለች !!

አሁን.... ውሻ ሞት በከፈተው ቀዳዳ ጅብ ወንዶች ዘው ሊሉ አሰፈሰፉ!! ‹‹አይዞሽ ሰው መቸስ ዘላለም አይኖር ...››ምናምን ብለው በማስተዛዘን ስም ወደ ቤተመቅደሳችን ዘው ሊሉ..... እናቴ ‹‹ ማንም ለቅሶ እንዳይደርሰኝ›› አለች!! መንደሩ ‹‹ለየላት አበደች›› ብሎ አወራ!

እማማ የእኔ መለአክ እኔንም ግራ አጋባችኝ !! አባቴ ሙቷል አልሞተም ? ....ቢሞትም አማማ አልሞተም ካለች አልሞተም!! ሰኞ ነበር ቀኑ የአባባ መርዶ የመጣበት ... እረጋ ብላ ቁርስ ሰራችልኝ የሚጣፍጥ ጨጨብሳ ...ስኳሩ በዛ ካለ ሻይ ጋር ! እሷ አልበላችም .....በእጇ የያዘቻትን የሻይ ማንኪያ እየነቀነቀች በጥልቀት ታየኛለች ... አይን አይኔን እያየችኝ ጥርግ አድርጌ በላሁ! ጉንጨኝ ስማኝ ወደትምህርት ቤት ላከችኝ.... ጉንጨን ነው ያልኩት ? በልምድ ብዙ ወላጆች ‹‹የልጆቻቸውን ጉንጭ ይስማሉ›› እንላለን እንጅ እንደእኔ እናት ከሆነ ግን ወላጆች የልጆቻቸውን ነብስ ነው የሚስሙት ! አዎ እማምየ ነብሴን ስማ ነው የምትሸኘኝ!! ብዙ ከሄድኩ በኋላ .... ወደቤታችን ዞር ስል አርንጓዴ ቢጃማዋን ለብሳ የበሩን ጣውላ ተደግፋ ቁማ እያየችኝ ነበር የደከማት ትመስላለች.... !!!!!!!!

አይኖቿ ብርታቶቸ ናቸው ...ከኋላየ ስትቆም እልፍ አእላፍ መላእክት ከነሰይፋቸው...ከነ እሳት ሰረገላቸው እኔን ሊጠብቁ የቆሙ ይመስለኛል ....በምድር ላይ ያለ የጦር ሰራዊት ከነመሳሪያው ያጀበኝ....!! እናትየ ከኋላየ ስትቆም.... ሰማይ ይቀርበኛል ደመና ባጭር የተቆረጠ ፀጉሬን ሲዳስሰኝ ይሰማኛል የእግዜር እግር ስር የቆምኩ ይመስለኛል ... የምረገጠው ምድር በእግሮቸ ብርታት የሚናጥ ድንጋዮቹ የሚፈነቃቀሉ ይመስለኛል... የእማማን የእይታ ጡሩር ከለበስኩ ማንንም አልፈራም!! ተራሮች ምንድናቸው? በእግሬ እንደማንከባልለው የጨርቅ ኳስ ናቸዋ!! ጨጨብሳ ባልበላም በጠረኗ ሽ አመት እኖራለሁ በፈገግታዋ ዘላለም!!

እማምየ የፍቅር ጥግ የእናትነት አልፋና ኦሜጋየ .....እናንተ ‹‹ ሴት እናት ናት ...ሴት እህት ናት›› የምትሉ ‹በደፈናወች› ሃይማኖተኛ ሁሉ መነኩሴ ነው እያላችሁ ነውና ይቅር ይበላችሁ.....ሴትነት እናትነት አይደለም!! ‹‹‹‹ሴት ከውስጧ የወጣ ገዳም ውስጥ ስትመንን እናት ትሆናለች››››› ...... ‹‹‹‹‹‹የልጅ መስቀል ተሸክማ የሂወትን ቀራንየ ስትወጣ....እናት ትባላለች !!!!!!››››››......

ዙሬ አየኋት እማማን የምትወደው ባሏን መርዶ ቅድም የሰማች ሴት በር ላይ ቁማለች ....አይገርምም ? እናት የላትም ...አባት የላትም ...ዘመድ የላትም እኔ ብቻ ነኝ ያለኋት....የማላውቀው ስሜት ወረረኝ....በአንድ ጊዜ ጀግናም ፈሪም ሆንኩ እኩል! ማንም የላት እና እኔ አለሁላት የሚሉ ሃሳቦች ተጋጩብኝ............

ትምህርት ቤቴ እስከምደርስ እንባየ ጉንጮቸ ላይ እየፈሰሰ እንዲህ እያልኩ ለብቻየ አነበንብ ነበር....

‹‹ሳድግ ለእማማ አዲስ አበባ ሱቆች ውስጥ ያሉትን ቀሚሶች ሁሉ እገዛላታለሁ.......ፒያሳ ወርቅ ቤቶች ውስጥ የተደረደሩትን ያልተደረደሩትንም የወርቅ ቀለበቶች ፣ሃብሎች፣ ጉትቻወች...ሁሉንም ለእማምየ እገዛላታለሁ ....ለእናትየ ትልቅ ቤት እገዛላታለሁ ....ትልቅ ግቢ እገዛላታለሁ....

ባለ ሚሊየን ፎቅ ጫፉ ጨረቃን የሚነካ ህንፃ እገዛላታለሁ ...በመጨረሻው መስኮት ብቅ ብላ የአባቴን ፎቶ ከነ ወርቃማ ‹ፍሬሙ› ጨረቃ ላይ ታስቀምጠዋለች ማንም እንዳይደርስበት!!!! ... ሳድግ ለእማምየ ሰፈራችንን አራት ኪሎን እንዳለ እገዛላታለሁ ከነሃውልቱ ...ከነ ዩኒቨርስቲው ...ከነቤተ መንግስቱ .......!!

ሳድግ ለእማማ ለእኔ ደግ ለእኔ ሩህሩህ .... አዲስ አበባን እገዛላታለሁ .....ሳድግ... ለኔ ትሁት ለኔ ቃልኪዳን አክባሪ ኢትዮጲያን እገዛላታለሁ !!!! ከነህዝቡ ከነ ሃይማኖቱ ...ከነ ቤተ ክርስቲያኑ ከነ መስጊዱ እገዛላታለሁ.....

ሳድግ ኢትዮጲያን... ከነተራራው ከነራስ ዳሽኑ ከነሸለቆው ከነ ጫካው ...ከነዋልያና ጭላዳው ...ከነ አዋሹ... ከነ ጫሞእና አብያታው ....ከነ ሶፍመሩ... ከነላሊበላው... ከነ ፋሲለደሱ ......ከነጣናው ከነ አባዩ ... ከነአዋሹ ከነአክሱሙ .... እ ገ ዛ ላ ታ ለ ሁ!!

አዎ እገዛላታለሁ !! ‹‹አልፈልግም የኔ እንቦቀቅላ የሄ ሁሉ ምን ያደርግልኛል›› ብትልም አልሰማትም እገዛላታለሁ ........!!!

ሳድግ ......ትልቁ የልቧ ስባሪ የነፍሷ ቀንዲል የፍቅሯ በር የእኔም አለኝታ እንደቀልድ የወደቀባትን ምድር...................





እገዛላታለሁ ለ እ ማ ም የ !!!!!!!!

No comments