Latest

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ - ቢቢሲ

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ

ስደት ክፉ ነው። ወደ ሀገር መመለስ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ መኖር ደግሞ የክፉ ክፉ።

ከሀገር ከመሸሽ ውጪ አንዳችም አማራጭ አጥተው ኢትዮጵያን የተሰናበቱ ስፍር ቁጥር የላቸውም። በየደረሱበት ሕይወት ቢጤ ቢጀምሩም፤ ጥለውት ስለሄዱት ዓለም አዘውትረው ማሰባቸው አይቀርም።

ቤተሰብ በሞት ሲለይ. . . ሕጻናት ተወልደው ቤተሰቡን ሲቀላቀሉ. . . ቤተሰቡ ከሌላ ቤተሰብ በጋብቻ ሲተሳሰር. . .

የሚወዱትን ሰው አፈር አለማልበስ. . . አይዞሽ፣ አይዞህ ባይ በሌለበት ለብቻ ማንባት. . . የዘመድ አዝማድን ስኬት በስልክ ገመድ መስማት. . .

አንድ ቀን ለሀገሬ መሬት እበቃለሁ ብለው በተስፋ የተሞሉ ነፍሶች በአንድ ወገን፤ በሌላ ጽንፍ ደግሞ ቁረጥ ልቤ ባዮች።

ባለፉት ሳምንታት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ያስተናገደችው እኒህን ነው።

ቢቢሲ ከሦስት ኢትዮጵያውያን ጋር ቆይታ አድርጓል። ሁለቱ ከዓመታት በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፤ አንደኛው በቅርቡ ሀገር ቤት የሚገባ ነው።

ዐሥርታት ወደ ኋላ መለስ ብለው ሀገር ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ የደረሱበትን ቅጽበት፣ ስደት ያሳጣቸውን እንዲሁም ዳግመኛ ኢትዮጵያን ማየት የፈጠረባቸውን ስሜት አጋርተውናል።

"እናቴን፣ አባቴን፣ ባሌን አልቀበርኩም" ዓለምፀሐይ ወዳጆ
የኪነጥበብ ሰው ዓለምፀሐይ ወዳጆ ከኢትዮጵያ የተሰደደችው ከ27 ዓመታት በፊት ነበር። ኢህአዴግ ሥልጣን ሲጨብጥ።

የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቿ ከአመራሩ ጋር እንደማያኗኗሯት ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባትም።

"የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በሚመለከት፣ የኤርትራን ጥያቄ በሚመለከት እጽፋቸው፣ እተውናቸው፣ አቀርባቸው የነበሩትን ነገሮች፤ በነሱ የሬድዮ መቀስቀሻ ጣቢያ ላይ ያፌዙባቸው ነበር" ትላላች።

ኢትዮጵያ ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ምርጫ ተደርጎ ሕዝቡ በፈቀደው የምትመራ ሀገር እንጂ አንድ ብሔር ላይ የተመሠረተ አገዛዝ የሚሰፍንባት አትሆንም የሚል ጽኑ አቋም ነበራት።

ደርግ ሲያበቃለት የመጣው መንግሥት የተሻለ እንደሚሆን አላመነችም።

ዕለቱ ማክሰኞ ነበር። ከኪነ ጥበብ ጓዷ ታማኝ በየነ ጋር ራድዮ እያዳመጡ ነበር። ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሥልጣን መውረዳቸውን ሰሙ። የዛኑ ዕለት ከሀገር ለመውጣት ወስና፤ አርብ ልጇቿን ይዛ ወደ አሜሪካ በረረች።

የሁለት ዐሥርታት የስደት ኑሮ ለዓለምፀሐይ ቀላል አልነበረም። በግል ሕይወቷም፣ በሙያዋም ብዙ አጥታለች።

"እናቴን አልቀበርኳትም፤ አባቴን አልቀበርኩትም፤ የምወደውን ባሌን አልቀበርኩትም። ከዚህ የበለጠ በሰው ላይ ሊደርስ የሚችል በደል ያለ አይመስለኝም"

እህቶቿ፣ የእህቶቿ ልጆች፣ የአክስቶቿና የአጎቶቿ ልጆች ሲዳሩ፣ ሲወልዱ ከጎናቸው አልነበረችም። ደስታም ሀዘንም እንዳመለጣት ስትናገር ሀዘን በሰበረው ድምጽ ነው።

ባዕድ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች መካከል መኖር እንደ ጥበበኛ ዋጋ አስከፍሏታል። ከምትጽፍለት፣ ከሚወዳት ሕዝብ ርቆ መሥራት እንደከበዳት ስትገልጽ "በጽናቴና በጥንካሬዬ ጥርሴን ነክሼ ሙያዬ ውስጥ ለመቆየት ቻልኩ እንጂ፤ እጅግ አንገትጋች የስደት ሕይወት ነው የመራሁት" ትላለች።

የኢትዮጵያ የጥበብ መድረክ ያለሷ ወደፊት መጓዙም ያስቆጫታል። በየጽሑፉ፣ በየትወናው፣ በየዝግጅቱ ውስጥ ብትሆን ኖሮ ልምዷን ለወጣቶች ታካፍል ነበርና። በገዛ ሀገሯ ስለ ሥራዎቿ ማውራት፣ ጽሑፎቿን ማንበብ እንደ ወንጀል መቆጠሩም ይቆጠቁጣታል።

"ከተመልካቼ ጋር አብሬ፣ ተውቤ የማድግበት፤ ለኅብረተሰቤ ስለ እውነት፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ፍቅርና ሰላም የምዘምርበት መድረኬን ተነፍጌያለሁ።"

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዓለምፀሐይ አንድም ቀን ተስፋ አልቆረጠችም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ እንደሚለወጥ፣ ወደ ትውልድ ሀገሯ እንደምትመለስም ታምን ነበር።

እሷ እንደምትለው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረው ግፍና በደል በፈጣሪ እገዛ እንዲሁም የኅብረተሰቡ መስዋእትነት አክትሞ፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን የመጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግርን ስታዳምጥ ከመቼው በላይ ተስፋዋ ለመለመ።

"በኢትዮጵያ መሪዎች ያልተለመዱ ቋንቋዎችን ስሰማ..." ትላለች ቅጽበቱን ስታስታውስ።

አሜሪካ ሳለች ኢትዮጵያና ኤርትራ እርቀ ሰላም ሲያወርዱ ከሥራዎቿ አንዱ የሆነው የማሕሙድ አሕመድ "ሰላም" መድረክ ላይ ሲቀርብ ፊቷ በእንባ ይታጠብ ነበር።

ልጅ ሳሉ ትታቸው የሄደቻቸው የሕጻናት አምባ ታዳጊዎች ዛሬ ጎልምሰው ለዓመታት በናፈቀችው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ሲያወድሷት፤ ዕድሜና ሙያ ሳይለይ ሕዝብ በነቂስ ሲቀበላት የደስታ ሲቃ ተናነቃት።

ከስብራት ለቅሶ ወደ ደስታ እንባ ተሸጋገረች።


Fiseha Tegegn

«ቤተሰቦቼን ባገኝም ዘግይቻለሁ»ፍስሃ ተገኝ
የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ አዲስ አበባ ተናጠች። የተቃውሞ ሰልፎች ይካሄዱም ጀመር። ሰልፎቹን ተከትሎ ስለተገደሉ ሰዎች ዜና ማንበብ የፍስሃ ተገኝ ድርሻ ነበር።

"አብዛኞቹ ሰዎች የተገደሉት ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ነበር" የሚል ዘገባ ቀረበለት። ምላሹ "ህሊናዬ ስለማይፈቅድ ዜናውን አላነብም" የሚል ሆነ።

ውሳኔው ከኤፍኤም አዲስ 97.1 ብቻ ሳይሆን ከሀገር እስከ መሰደድ አድርሶት ለ13 ዓመታት በእንግሊዝ ኖረ።

የዜና አላነብም ውሳኔውን ተከትሎ ማስፈራሪያ ይደርሰው ነበር። በወቅቱ ሊቀጥረው ፍቃደኛ የነበረ መገናኛ ብዙኃንም አልነበረም። ለሦስት ሳምንት ያህል ስለ ሁኔታው ከጓደኞቹ ጋር ይመክር ነበር።

ከራስ ሆቴል አካባቢ ብዙም የማይጠፋው ፍስሃ፤ ማክሰኞ ለንባብ ለሚበቃው ኢትዮ-ስፖርት ጋዜጣ ቅዳሜ ቃሉን ሰጠ። አስከትሎም ጋዜጣው ሳይወጣ በግብጽ አየር መንገድ አድርጎ ሀገሩን ተሰናበተ።

"ቅጽበታዊ ውሳኔ ነበር፤ ጓደኞቼ ወደ እንግሊዝ የሚሄድ ተሳፋሪ ትኬት ቀይረው ሰጡኝ። ትኬቱን እንዴት እንዳገኙልኝ አላውቅም፤ ብቻ ከኪሴ አምስት ሳንቲም አላወጣሁም፤"

ኤስኦኤስ ውስጥ ያደገው የስፖርት ጋዜጠኛው፤ ዘመድ አዝማዶቹን የማፈላለግ ፍላጎት ቢኖረውም፤ ባህር ማዶ ሆኖ የሚያሳካው ነገር አልነበረም።

ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አለመቻሉ ቤተሰቦቹን እንዳያፈላልግ ብቻ አይደለም ያገደው፤ ሙያዊ እድገቱንም ገታው እንጂ።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2013 ላይ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችበትን ጨዋታን ስቴድየም ተገኝቶ አለማየቱ፣ አለመዘገቡ ያስቆጨዋል።

"አዲስ አበባ ስታዲየም ከሱዳን ጋር የተደረገውን የመልስ ጨዋታ፤ ጋዜጠኛ እንኳን ባልሆን እንደተመልካች ገብቼ አየው ነበር"

በአውሮፓውያኑ 2007 ጥሩነሽ ዲባባ በኦሳካ የአለም ሻምፒዮና በ10ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አግኝታለች። ድሉን ለተቀዳጀችው ሯጭ ቃለ መጠይቅ ቢያደርግ ከምንም በላይ ይደሰት ነበር፤ አልሆነም እንጂ።

ቤተሰቦቹን ፈልጎ ለማግኘት የግድ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዳለበት ስለሚያውቅ፤ በአውሮፕላን መመለስ ባይችልም አማራጭ መንገዶች ያሰላስል ያዘ።

በኤርትራ በኩል ልግባ? ወይስ በሱዳን አድርጌ? እያለ ሲያወጣና ሲያወርድ ኢትዮጵያ በተቃውሞ እየታመሰች ነበር።

ከዛም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሥልጣን ይዘው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ንግግር ያደረጉበት ቀን መጣ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው "ሀገሪቱን በአንድነት ለማቆየት፣ ድንበሯን ለማስጠበቅ መስዋእትነት ከተከፈለባቸው መካከል ካራማራ ይገኝበታል" ሲሉ ጆሮውን ማመን አቃተው።

ለሱ ያ ንግግር "ሀገርህ መግባት ትችላለህ" የሚል ቀጥተኛ ጥሪ ነበር። ስሙ የማይጠቀስ ቦታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲነገርለት የአውሮፕላን ትኬቱን ለመቁረጥ ወሰነ። የፖለቲካ ስደተኞች ሀገራችሁ ተመለሱ የሚለው ጥሪ ከመተላለፉ በፊትም ልቡ ተነሳሳ።

«ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ያገኛቸው ድሎች ሲነሱ፤ በደርግ ጊዜ የተገኙ ድሎች በሙሉ ከደርግ አምባገነን ሥርዓት ጋር ብቻ ስለሚያያዙ ተሰርዘው ነበር። ጠፍተው ነበር» ይላል።

የሀገሩን መሬት እንደረገጠ የቤተሰብ ፍለጋውን ተያያዘው። ፍለጋው የተጠናቀቀው በድል ነው። ዛሬ ላይ የዘር ሀረጉን አውቋል። ሆኖም ስደት ከቤተሰቡ ጋር መቀላቀል የሚሰጠውን ሀሴት አዘግይቶበታል።

"ከ 13 ዓመት በኋላ ስመለስ ቤተሰቦቼን ፈልጌ አግኝቻለሁ። የተወለድኩበትን ቦታ አውቄያለሁ፣ ዐይቻለሁ፤ ነገር ግን ዘገይቷል"

ካሳሁን አዲስ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር
ካሳሁን አዲስ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር
"ሕይወቴን እስር ቤት የማሳለፍ ፍላጎት አልነበረኝም" ካሳሁን አዲስ
ካሳሁን አዲስ እንደ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛነት በአውሮፓውያኑ ከ2005 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ተፈትኗል።

ዘገባዎቹን ተከትሎ ማስፈራሪያና ማዋከብ ደርሶበታል። ቢሯቸው አስጠርተው ማስጠንቀቂያ የሰጡት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ነበሩ።

Open Letter to Bereket Simon [ግልጽ ደብዳቤ ለበረከት ስምኦን] በሚል ርእስ ባለፈው ነሐሴ ላይ ያስነበበው ጽሑፍ መነሻም ያሳለፈው ውጣ ውረድ መሆኑን ይናገራል።

"የሥራ ፍቃድ አይታደስልህም"፣ "የዋሽንግተን ፖስት ፈቃድ እያለህ ለታይም መጻፍ አልነበረብህም"፣ "የሀገር ገጽታ ታጠፋለህ"፣ "አዘጋገብህ ትክክል አይደለም..."ብዙ ተብሏል።

በስተመጨረሻ ከሀገር ለመውጣት ውሳኔ ላይ የደረሰው የክስ መዝገብ እየተዘጋጀበት እንደሆነ ከታማኝ ምንጭ መረጃ ሲደርሰው ነበር።

ሰኞ ዕለት የፍርድ ቤት መጥሪያ እንደሚደርሰው ሲሰማ ዓርብ ዕለት ወጣ።

«ክሱ የፖለቲካ ስለነበረ አንዳንድ ቁርጠኞች እንዳደረጉት ፍርድ ቤት ሄጄ ለመታገል ወይም ሕይወቴን እስር ቤት ለማሳለፍ ፍላጎቱ አልነበረኝም» ሲል የያኔውን ውሳኔ ይገልጻል።

ካሳሁን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የብዙ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የስደት መዳረሻ ወደ ሆነችውና «አክስት ሀገር» ወደሚላት ኬንያ ሸሸ።

ኬንያ ውስጥ ሥራ ቢጀምርም "ደኅንነቶች እየተከታተሉህ ነው" የሚል መረጃ ደረሰውና ሁለተኛ ሽሽቱ ወደ አሜሪካ ወሰደው።

ብዙም ባይሆን በሙያው ሠርቷል። «የመብራትና ውሀ የሚከፍሉ» የሚላቸው ከጋዜጠኝነት ጋር የማይያያዙ ሥራዎችን ለመሥራት የተገደደበት ጊዜ ነበረ።

ቀድሞ ኢትዮጵያ ነክ ጉዳዮችን ይተነትንላቸው የነበሩ የውጪ ሀገር ሚዲያዎች ከሀገሩ በመራቁ እንደ መረጃ ምንጭ ሊጠቀሙበት አልቻሉም። ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሱ ድረ ገጾች መክፈት ቢሞካክርም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ታግደው ነበርና ነገሩ ሁሉ ትርጉም አልባ ሆነበት።

ስደት ያጠላው በሥራው ላይ ብቻ አይደለም። የቤተሰብ፣ የጓደኛ ትስስሩ ላልቶበታል። በሱ አነጋገር "ከሀገር ስወጣ የሃያዎቹን አጋማሽ አልፌ ነበር። ስለዚህ የዛን ያህል ሕይወት ትቼ ነው የወጣሁት። "

ያሳደጉት አያቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ መቅበር አለመቻሉ አሳምሞታል። ለመጨረሻ ጊዜ ዐይናቸውን አለማየቱ ሁሌም ይቆጨዋል።

ሀገር ቤት ሳለ እናቱን አልፎ አልፎ ቢጠይቅ ነው። ዛሬ ዛሬ ግን ዘወትር በናፍቆት ይቆዝማል። ለጥቂት ጊዜ አሜሪካ ሄደው ቢያያቸውም በቂ አልነበረም። በተለይም አሁን በመታመማቸው ሁሌም ከጎናቸው ቢሆን ይመኛል።

ኢትዮጵያ ቢኖር ፍሬያማ ሊሆን ይችል የነበረ የፍቅር ግንኙነት በመሰደዱ ሳቢያ ተቀጭቷል። ጓደኞቹን በስልክ ቢያገኛቸውም የልቡን አያደርስለትም።

በግንባር ቀደምነት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡ ብዙ ናቸው። ሞት ሳያስፈራቸው ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የሚወጡትን ሰዎች ቁጥር ግን አልቀነሰውም።

"አገዛዙ ብዙ አይቆይም፤ መቀየሩ አይቀርም፤ እኔም ሆንኩ ከኔ በፊትና በኋላም ከሀገራቸው ተገፍተን የወጣን ሰዎች መመለሳችን አይቀርም የሚል እሳቤ ያደረብኝ ያኔ ነው"

አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ሲፈታ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ አርበኞች ግንቦት 7 እንዲሁም ሌሎችም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች "ሽብርተኛ" ከሚለው ዝርዝር ሲወጡ ሀገሩ እንደሚገባ አገጋገጠ።

ኢትዮጵያ፣ ኬንያ ብሎ አሜሪካን ሦስተኛ ሀገሩ ቢያደርግም፤ እንደ እናት ሀገር የሚሆን የለምና የያዝነው የፈረንጆች ዓመት ሳያልቅ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ተስፋን ሰንቋል።

ዳግመኛ ላያገኛቸው ያመለጡትን የሚክስ ምን ተዐምር ሊጠብቀው ይችላል?

No comments