Latest

ፖለቲካችን ሃፍረት አያውቀውም - መስከረም አበራ

ፖለቲካችን ሃፍረት አያውቀውም - መስከረም አበራ

ስለራስ ጉዳይ በራስ ስለመወሰን መታገል ወንጄል ነው ብሎ ንፁሃንን ሲከስ ልክ ነኝ እያለ ነው፤ይህን ክስ ብሎ የሰማው ፍርድቤትም የሰባት ቀን ቀጠሮ ይሰጣል፡፡  


ግሩም ነው መቼም....! ብሄር ብሄረሰብ ሁሉ ራሱን ያስተዳድር ተብሎ ምድረ ብሄር ብሄረሰብ የራሱን ጎጥ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት አስከብሮ እንደጨረሰ ሲሰማውና ቀን የወጣለት ሲመስለው በአውቶብስ ተሳፍሮ አዲስ አበባ ይሄድ እና ሌላውን ካላስተዳደርኩ ሞቼ እገኛለሁ ይላል ፡፡

የጎጥ ፖለቲከኛ ሲያድግ እንዲህ ነው- ነፃነት የሚያስፈልገኝ ለእኔ እና ለዘር ማንዘሬ ብቻ ነው ያሰኘዋል፡፡
ሚካኤል መልዓከ እና ሄኖክ አክሊሉ የተከሰሱት አዲስ አበባ ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ እያጣጣመ ያውን በራሱ ሰው የመተዳደር መብት ልታገኝ ይገባል ስላሉ ነው፡፡  

ከፍልስጤም ኢምባሲ ጋር ያላግባብ ግንኙነት መፍጠር የሚለው አሰቂኝ ማጀቢያ ለጨዋታው ድምቀት የታከለ ነው፡፡ ሆኖም ነገሩን በደንብ ስለማውቀው እውነታውን ላውጣ፡፡ ተከሳሽ ሚካኤል መልዓከ ከፍልስጤም ኢምባሲ ጋር ያላግባብ ጀመረው የተባለው ግንኙነት ከጎሬ ተጎትቶ የወጣው ዛሬ ነገሩ ስለተፈለገ እንጅ ግንኙነቱን የተጀመረው አምና ነው፡፡

የሰው ሁሉ መበደል እረፍት የሚነሳው ሚካኤል መልዓከ በአለም ላይ ያሉ ሃገሮች ሁሉ የፍልስጤም ወዳጅነት ማህበር አላቸው ፤የእኛ ሃገር ቀደም ብላ ፍልስጤም ኢምባሲ እንድትከፍት የፈቀደች ሃገር ብትሆንም ይህ ማህበር የለምና ብናቋቁም ምን ይመስልሻል ብሎ አማክሮኝ ነው እንቅስቃሴውን የጀመረው፡፡ 

እንቅስቃሴው ኢትዮጵያዊያን የፍልስጤም ወዳጆች ማህበር ለማቋቋም ያለመ ነበር፡፡ እንደመነሻ በማህበሩ ውስጥ የሃሳቡ አፍላቂ የሚካአል መልዓከ የቅርብ ሰዎች የሆንን እኔ እና ስዩም ተሾመን ጨምሮ ከዚህ በታች ፎቷቸውን የምታዩ ወገኖችም እንዲካተቱ ተነጋግረን ማህበሩን ህጋዊ በምናደርግበት ነገር እና በሃገራችን ስለ እስራኤል እና ፍልስጤም ያለውን ግንኑነት በተመለከ ያሉትን የተዛቡ አመለካከቶች አንስቶ ትክክለኛውን መረጃ ለማቅረብ ማህበሩ ምን ሊሰራ ይችላል በሚለው ነገር ዙሪያ ስንመክር ቆይተናል፡፡

በመሃል ማይክ ትንሽ ስላመመው ማህበሩ የተፈለገውን ያህል ሳይራመድ ቆይቶ ነበር፡፡ ባለፈው አመት የተባበሩት መንግስታት የአለም አቀፍ የወንድማማችነት ቀን ሲከበር ኢምባሲው ጋብዞን ከታች እንደምትመለከቱት እኔም ተገኝቼ ነበር፤ማይክ ከመሰጠቱ የተነሳ ትንሽ አሞት ሰንብቶ እያለ እንኳን ጥሪውን አክብሮ ተገኝቶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ የኢህአዴግ ባለስልጣን አቶ እስማኤል ደደፎ ጭምር ተገኝተው ነበር፡፡ 

ይህ ለክስ ስላልተፈለገ እንደ ህገወጥ ግንኙነት ተወስዶ አልተወራም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መሰለኝ ኢምባሲው የእራት ግብዣ እንደጠራን እና ከተመቼኝ እንድገኝ ማይክ ደውሎ ነግሮኝ ነበር፡፡ ይህ ሰዓት ማይክ በአዲስ አበባ ላይ እንቅስቃሴ ከጀመረባቸው ቀናት ጋር ስለገጠመ ወንጄል ሆኖ ተቆጠሮ እያስከሰሰው ነው፡፡

ከዚህ የተረዳሁት ልጁ በአዲስ አበባ የራስን በራስ ማስተዳደር ላይ ለመስራት እንደሚንቀሳቀስ ካወቁ ጀምሮ እየተከታተሉት ነበር፡፡ይሄኔ ባለፈው ሳምንት የፍልስጤም ኢምባሲ በጠራው ጥሪ ላይ እንደተገኘ አወቁ ፤ከዛ ከፍልስጤም ጋር ግንኙነት በማድረግ ብለው የጅል ክስ መሰረቱ፡፡ 

ፍልስጤም ጠላታቸው ከሆነች ለምን ከዓለም ሃገራት ሁሉ በፊት ኢምባሲ በኢትዮጵያ ተሰጣት? ከፍልስጤም ጋር መገናኘት ወንጄል ከሆነ ለምን ኢምባሲውን ጭምር አብረው አልከሰሱም?!

No comments