Latest

ከአድማሱ ባሻገር! ሙሉቀን ተስፋው (ክፍል አንድ)

ከአድማሱ ባሻገር! ሙሉቀን ተስፋው (ክፍል አንድ)

የፀሃፊው ማስታወሻ
ያየሁትን እና የሰማሁትን በተከታታይ ማቅረቡ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል የሚል እምነት ስላለኝ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ ያለውን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ አስተያየት ስጡበት፤ ለማሳጠርም በዝርዝር ለመጻፍም ያግዛል


በአውሮፓ ጥገኝነት ለመጠየቅ የወሰንኩ ዕለት በአጭር ጊዜ ሳይሆን በአሥር ዓመትም ወደ አገሬ እመለሳለሁ የሚል ሀሳብ በኅሊናዬ ሽው ብሎብኝ አያውቅም ነበር፡፡ ለዚያም ነበር ጋሽ ስዩም ሐዲስ እያሽከረከረ ወስዶ ‹‹እዚያ ቢሮ ሒደህ እጅህን ስጥ›› ሲለኝ ተሸንፌ ያለቀስኩት፡፡

የስደተኛ ካምፕ ውስጥ እንደገባሁ ከኦጋዴንና ከአዲስ አበባ የመጡ ሁለት አንስቶችን አገኘሁ፡፡ ከኦጋዴን የመጣችሁ ብዙ አማርኛ አትችልም፤ የአዲስ አበባ እህት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በማስተርስ ተመርቃለች (አሁን በሰሜን ስዊድን ትኖራለች)፡፡ ሁለቱም በሊቢያ በኩል የመጡ ናቸው፡፡

በሰዎች ሕይወት ብዙ ትምህርት አገኛለሁ ብዬ ስለማስብ ‹‹እንዴት እዚህ ልትደርሱ ቻላችሁ?›› ብዬ ስጠይቃቸው የጅጅጋዋ ልጅ ቀድሟት እንባዋ መጣ ‹‹ወላሒ ስቃይ ነው!›› አለችኝ በአጭሩ፡፡

ወሬው ተቋረጠ፡፡ ከካምፕ ወጣሁና ሱቅ ፍለጋ ስሔድ አንዲት ኢራቃዊት ልጇን በጋሪ እየገፋች ትሔዳለች፤ የሱቁን አቅጣጫ አሳይታኝ አብረን መጓዝ ጀመርን፡፡ ባሏ ዴንማርክ ኬላ ተይዞ ብቻዋን ከልጅ ጋር ትሰቃያለች፡፡

ለምን እንደቀረ ስጠይቃት ፊቷ ተለዋውጦ ያ ፈካ ያለ ፊቷ በእምባ ታጠበ ‹‹አንተ ሰው መልሰህ መጠየቅ ሳይሆን እንድትቀርበኝም አልፈልግም!›› ብላ ስትጮኽብኝ መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠኝ ደስ ባለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ስደተኛን ምንም አልጠይቅም፤ ካወሩኝ ብቻ አደምጣለሁ (የስደት ገጠመኞችን በሌላ ጊዜ እመለስባቸዋለሁ፤ ዘልሌ አዲስ አበባ ከምገባ ብዬ ነው)፡፡

በተዋበ ከተማ፣ ለሁሉም ነገር ሥርዓት ባለበት አገር እየኖርኩ አንድም ቀን የኅልሜ መቼት እምኖርበት አገር ወይም ቤት ሆኖ አያውቅም፡፡ በበረዶ የተሞሉትን መንሸራታቻዎች እኔ ቀዬ ካለው አመድ መድፊያ ጋር እያመሳሰልኩ፣ የበረዶ ሸርታቴ የሚጫወቱትን ፍጡራን ሁላ ጂኒ ያረፈባቸው አመድ ላይ የሚንከባሉ ሰዎች አድርጌ እየሳልኩ ነው የቆየሁት፡፡

በአጭሩ ከጥልፍልፉ መሳለጫ ይልቅ ከቤቴ ጎን ያለው የሳርቤቱ የቆሻሻ ወንዝ ለእኔ ትዝታ ነበረው፡፡ በሰላጣ መልክ የሚቀርበው ጉሳንጉስ ሁሉ ከአባቴ ማሳ የምንነቅለው አረም ነው እያልኩ አገር በሌለበት አገር በኅሊናዬ ምስል ይዤ ኖሬያለሁ፡፡

የስደት ሕይወቴን አስቀያሚ ያደረጉብኝ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ፤ አንደኛው እንደወጣሁ የአማራ ተጋድሎ መጀመሩ ነው፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ የምሰማው የሲቃ ድምጽ፣ የታሠሩ ሰዎች የሰቆቃ ታሪክ፣ የሚሞቱ ሰዎች ቤተሰብ ወዘተረፈ ከልቤ እንኳ ስቄ እንዳላውቅ አድርጎኝ የጤና ችግርም አስከትሎብኝ ነበር፡፡

ሁለተኛው ግን በሥርዓቱ እንኳ ያልተሰናበትኳት እናቴ በጠና መታመሟ እና በሕይወት የመቆየት እድሏ አነስተኛ መሆኑን መስማቴ ነበር፡፡

አንድ ጊዜ እንኳ በዐይነ ስጋ እንድንገናኝ ያልተሳልኩት ስለት አልነበረም (እድለኛ ስለነበርኩ ፈጣሪን አመሰግናለሁ)፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ከአዲስ አካባቢና ሕይወት ጋር ብዙ ቢመሰቃቀልብኝ ብዙም የሚደንቅ አልነበረም፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁሉ ስሜት መካከል ነበር ወደ አገር ቤት የመሔድ ጉዳይ የመጣው፡፡

በየት ይሆን ከቶ መጓዣው ጎዳና፡
ገስግሶ ሚያደርሰኝ ካገሬ መዲና 

የኤፍሬም ታምሩን ሙዚቃ እያደመጥኩ ወደ ጠያራው ገባሁ፡፡ ወደ አውሮፕላኑ ስገባ ምግብም በደንብ የተመገብኩ አልመሰለኝም፡፡ ለዚያውም ኮሎኔል አለበል አማረ አስገድዶኝ እንጅ የመቅመስም ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ ይህን ጉዞ ካሰብኩ ቀን ጀምሮ እንቅልፍም ብዙ እየተኛው አልነበረም፡፡ ነፍሴም ስጋየም ምን እንደሚፈልጉ ግራ እስከሚገባኝ ድረስ ዝብርቅርቅ ብሎብኝ ነበር፡፡

የጢም መላጫ ማሽኔን ረስቼው የወጣሁት ለዚያም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ረዥም የአውሮፕላን መንገድ አልወድም፤ በዚያ ዕለት ግን ትዝታዎቼ እዚያና እዚህ እየረገጡ የኅሊና ፊልም ሳይ ነው ያደርኩት ማለት እችላለሁ፡፡ A Brief History of Tomorrow የሚል መጽሐፍ ይዤ ነበር፤ ስለሚቀጥለው ምዕተ ዓመት ሳይሆን ስለሚቀጥለው ማለዳ እንዲነግረኝ ጥቂት ገፆችን ገለጥ ገለጥ አደረግኩ፡፡ ኅሊናዬን ማሰባሰብ አልቻልኩም፤ ለመተኛት ሞከርኩ፡፡

አውሮፕላን አብራሪው ሊነጋጋ ሲል ድምጹን አሰማ ‹‹አሁን በአሥመራ ከተማ ላይ እያለፍን ነው›› አለ፤ በመስከት ወደታች ለማዬት ሞከርኩ፡፡ ያነቀላፋች ከተማ ጭልጭል የሚሉ መብራቶች ካድማሱ በታች በርቀት አየሁ፤ ያየሁት አሥመራ ስለመሆኗ እግዜር ይወቀው፡፡ ብዙም ሳንቆይ ለማረፍ እየተቃረብን ስለሆነ ቀበቷችሁን እሠሩ የሚል ትእዛዝ ከአብራሪው ጋ እንደገና ተሰማ፡፡

በነሐሴ ዝናባማ ጠዋት አውሮፕላኑ መሬት ላይ አረፈ፤ ያኔ ራሱ ምን እንደተሰማኝ አላውቅም፡፡ ከአውሮፕላን ወጥተን ስንሔድ ስማችን የያዘች ልጅ አስቁማ ወደ ቪአይፒ በልዩ መኪና ወሰደችን፡፡

ከዚያች ክፍል ውስጥ አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፣ አቶ መላኩ አለበልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም ጠረንጴዛ በመካከላችው አስቀምጠው ያወራሉ፡፡

ከሁሉም ጋር ተቃቅፈን ሰላም ተባባልን፤ አቶ በረከትም ለሰላምታ ተነሳ፡፡ ‹የብአዴን ጉድ እኮ አያልቅም አቶ በረከትን እንዲቀበለን ልከውት ይሆን› ብዬ አሰብኩ፡፡ አቶ በረከት በመጠራጠር ስሜት እጁን በመዘርጋትና በመሰብሰብ መካከል አየሁት፡፡

መቼስ ምን አደርጋለሁ ብዬ ፈጠን በማለት ‹‹ጤና ይስጥልን አቶ በረከት!›› አልኩና እርሱንም እንደነ መላኩ ሰላም ብዬ አቀፍኩት፡፡ እዚያው ጠረንጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ ሳስብ አቶ መላኩ ፈጠን ብሎ ሌላ ቦታ ሒደን እንድንቀመጥ አደረገ፡፡

እነ መላኩን በጠዋት በነገር እየቆላቸው ነበር አቶ በረከት፤ የእኛ መድረስ ሳይገላግላቸው አልቀረም፡፡

ይቀጥላል!

No comments