Latest

ኢትዮጵያዊቷ ሰው አልባ አውሮፕላን - ቢቢሲ



ኢትዮጵያዊቷ ሰው አልባ አውሮፕላን

በአሁኑ ሰዓት የሰው አልባ አውሮፕላኖች ለተለያዩ አገልግሎቶች እየተሰሩ ነው። ከእነዚህ መካካል የጤና አገልግሎትን ለመደገፍ የተሰራችው ንስረ ጤና አንዷ ናት።

ከሰው አልባ አውሮፕላን ጀርባ ያለ አእምሮ

አቶ ፋሲካ ፍቅሬ የኤሮ ስፔስ ኢንጂነር ነው ያጠኑት፤ ካናዳ ተምረው እዛው ሲሰሩ ቆይተው አሁን ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል።

ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ ግን ባዶ እጃቸውን አልነበረም፤ በሙያቸው ለመስራት ተማሪ እያሉ ጀምሮ ያስቡ የነበረውን የሰው አልባ አውሮፕላንን ሀሳብ ይዘው እንጂ።

ሙያቸው አውሮፕላንና የሕዋ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ሌሎች በራሪ አካላትን ንድፍ መስራትን ያጠቃልላል። የአውሮፕላን፣ የመንኮራኩር፣ የሳተላይትን ሁሉ ንድፍ ይሰራሉ።



አቶ ፋሲካ ፍቅሬ (በስተቀኝ በኩል) ከጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እና ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ተወካይ ጋር።

አቶ ፋሲካ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በሰው አልባ አውሮፕላን ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን አላዩም ነበር። "እውቀቱም ተቀባይነቱም ምን ድረስ መሆኑን ለማወቅ ፈታኝ ነበር" ይላሉ ጊዜውን ሲያስታውሱ።

አሁን ግን ይላሉ አቶ ፋሲካ "እውቀቱም ያላቸው በዘርፉ ላይ አንቅስቃሴዎችንም የሚያካሄዱ ወገኖች ተበራክተዋል።"

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋር በዚህ ዘርፍ እንደሚሰሩ የሚናገሩት አቶ ፋሲካ እንደውም አሁን የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የራሱ ኤሮ ስፔስ ቴክኖሎጂን ለማስተማር በጥናት ላይ እንደሆኑ አውቋል፤ እርሱም በሙያው እንዲያግዛቸው ተጠይቆ በቅርቡ እዚሁ ላይ እንደሚሳተፉ ነግረውናል።

አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሮ ስፔስ ኢንጂነሪንግ በባለሙያዎች ዘንድ በደንብ እየታወቀ ነው የሚሉት አቶ ፋሲካ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ለማስተማር ያለውን ዝግጅትና የተለያዩ ወጣቶች በዘርፉ ላይ ለማሰማራት ያሳዩት ንቁ ተሳትፎ እንደበጎ ጅማሮ ያነሳሉ።

ንስረ ጤና ሰው አልባ አውሮፕላን

አቶ ፋሲካ ሰው አልባ አውሮፕላን ከወታደራዊ አገልግሎት ውጪ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን የሚለው ላይ ጥናትና ምርምር ሲሰሩ ነው የቆዩት።

ወደ ሃገራቸውም ለመምጣት ሲያስቡ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን የሚለውን ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ ከወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ድርጅት አቋቋሙ።

ድርጅታቸው ትርፍን ከማግኘት ባሻገር ማህበራዊ ግልጋሎትን መስጠት የሚል ዓላማን ስለያዘ በመጀመሪያ ሞባይል ጤና የሚል ስራ ላይ ተሰማሩ።

በዚህ ስራቸው ለነፍሰጡር እናቶች በተንቀሳቃሽ ስልክ የአጭር መልዕክት ስለራሳቸውና ጨቅላ ህፃናቶቻቸው የጤና መረጃ እንዲደርሳቸው የሚያስችል መተግበሪያ ሰሩ።

ይህንን መተግበሪያ ለመስራት ጥናቶች ሲያደርጉ በእርግዝናና በወሊድ ወቅት የእናቶችን ሞት ከሚያስከትሉ ነገሮች መካከል ቀዳሚው የደም መፍሰስ መሆኑን ተገነዘቡ።

የደም መፍሰስ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የሚያስፈልገውንም ደም ለማግኘት አለመቻል ለሞቱ መበራከት ሌላኛው ሰበብ እንደሆነ ተረዱ።

ይህንን ሀሳባቸውን ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጋር ሲነጋገሩ በሰው አልባ አውሮፕላን ለእናቶች ጤና የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁስ ማድረስ የሚለው ሃሳባቸው ላይ ቢሮው በጎ ምለሽ ሰጣቸው።

እነርሱም ይህንን የቢሮውን በጎ ምላሽ በመያዝ ከዚህ ቀደም በንድፍ ደረጃ ወረቀት ላይ ያስቀመጧቸውን የሰው አልባ አውሮፕላንን ለሰብዓዊ ድጋፍ ማዋል የሚያስችል ስራ ማጠናቀቅ ያዙ።

ከዚህ በኋላ ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ላይ ሃሳባቸውን አቅርበው በመወዳደር የገንዘብና የሙያ ድጋፍ አገኙ።

ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰራ

ከዚህ በመቀጠል ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተነደፈችውና የተሰራችውን ሰው አልባ አውሮፕላን ወደ ማምረት ገቡ።

የዚህች ሰው አልባ አውሮፕላን ስያሜ ንስረ ጤና ይሰኛል። ንስረ ጤና ደም ለሚያስፈልጋቸው ነፍሰጡር እና ወላድ እናቶች ደም ለማድረስ ብትሰራም ከዚያ ጋር ግን ተያያዥ የሆኑ ከማዕከል ቦታ መኪና ወደ ማይገባባቸው ስፍራዎች ለማድረስ ተሰርታለች።

ይህንን ጉዳይ ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ንስረ ጤናን ክትባት ለማድረስ እንድትሆን አድርገውም ሰርተዋታል።

ንስረ ጤና 3 ኪግ ጭና በአንድ ጊዜ እስከ 100 ኪሜ ድረስ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማድረስ የምትችል ናት።

ይህች ሰው አልባ አውሮፕላን ገበያው ላይ ካሉ ሌሎች ሰው አልባ አውሮፕላኖች የምትለየው ብዙ የመጫን አቅሟ እና ብዙ ርቀት መሄድ መቻሏ እንደሆነ አቶ ፋሲካ ይናገራል።

"ከገበያ ላይ የሚገዙት ቪዲዮ ለመቅረፅ የሚያገለግሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሀይለኛ ንፋስን የመቋቋም አቅም የላቸውም። ንስረ ጤና ግን እስከ 50 ኪሎ ሜትር ድረስ ፍጥነት ያለው ንፋስ የመቋቋም አቅም አላት" ብለዋል።

ሌላው ገበያ ላይ ያሉትና ተሻሽለው የተሰሩትም ቢሆኑ ዋጋቸው የሚቀመስ እንዳልሆነ አቶ ፋሲካ ጨምረው አስረድተዋል።

እነርሱ የሰሩት ሰው አልባ አውሮፕላን የኢትዮጵያን አየር ሁኔታንና መልከአ ምድር አቀማመጥ ያገናዘበ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፋሲካ ከመስራታቸው በፊት ከአፋር እስከ ቱሩሚ ከዛም እስከ ሞያሌ ድረስ ጥናት አድርገው ወደ ተግባር መግባታችን ይናገራሉ።

ንስረ ጤና ኢትዮጵያ ውስጥ ተነድፋ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰራች መሆኗን የሚናገሩት አቶ ፋሲካ የ3ዲ ማተሚያ ከውጭ በማስመጣት የአካል ክፍሎቹን እዚሁ ተነድፎ እዚሁ እንደተመረተ ተናግረዋል።

የንስረ ጤናን ሞተር እነርሱ ንድፉን ሰርተው ማስመረታቸውን የተናገሩት አቶ ፋሲካ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰው አልባ አውሮፕላን ማብረር ስለማይፈቀድ፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በኩል ለማብረር የሚያስችላቸውን ልዩ ፈቃድ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

ፈቃዱን የሚያገኙ ከሆነ ንስረ ጤናን ለሙከራ በዚህ የጥቅምት ወር ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመረጣቸው ስድስት የክልል ከተሞች ላይ ያበራሉ።

No comments