Latest

ቅንጥብጣቢ የአስመራ እና ምፅዋ ወግ ክፍል ፪ (ከሕይወት እምሻው)

ሕይወት እምሻው

አስመራ - ከተወራላት በላይ የምታምረው ከተማ

ለስድስት ቀን ቆይታዬ በፊልሞን አማካኝነት ወደተያዘልኝ አምባሳደር ሆቴል ገባሁ፡፡ የእንግዳ መቀበያውና በኋላ ያየሁት በስተግራ ያለው ሻይ ቤት ነገረ ስራው ሁሉ የፒያሳውን ቶሞካ አስታወሰኝ፡፡ ሞቅ ባለ ሁኔታ የተቀበለኝ አስተናባሪ ሻንጣዬን ይዞ ክፍሌን የሚያሳየኝ ጎልማሳ መድቦልኝ አሳንሰሩ ጋር ሄድን፡፡  


እጅግ ጥንታዊ ነው፡፡ ተሸራርፈው ያለቁ ከሚመስሉ ድርድር ቁልፎች ውስጥ አንዱን ተጫነው፡፡ የተጫነው ቦታ ቀይ መብራት በራ፡፡ ‹‹እየመጣ ነው›› አለኝ ጎልማሳው ፈገግ ብሎ፡፡ ድምፁ ግን ተምዘግዝጎ ይከሰከስ ይመስል ያስፈራል፡፡ ክፉኛ ያጓራል፡፡ ያቃስታል፡፡ በመጨረሻ ደረሰና ገባን፡፡ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ሶስት መካከለኛ ስፋትና ክብደት ያላቸው ሰዎች ቢይዝ የሚሞላ አይነት ጠባብ፡፡ እያቃሰተ አምስተኛ ፎቅ ደረስንና ክፍሌን ከፍተን ገባን፡፡ ረጅምና ሰፋ ያለ ኮሪደር ተቀበለኝ፡፡

በስተቀኝ ከአዲስ አበባ ቤቴ ሳሎን የሚስተካከል ሰፊ መታጠቢያ ቤት አለ፡፡ ሮዝ ቀለም ባላቸው ሴራሚክ የመታጠቢያ ቤት እቃዎች አሸብርቋል፡፡ ሰፊ ሮዝ ገንዳም አለው፡፡ ከእሱ ቀጥሎ ጠበብ ያለ ሳሎን ውስጥ ቢጫ የቆዳ ሶፋ ተቀምጧል፡፡ ሌላ ነገር የለውም፡፡ 

በስተግራ ደግሞ ሰፋ ያለ መኝታ ክፍል አለው፡፡ እቃዎቹ ዘመናዊ አይደሉም፡፡ አልጋው ይንቋቋል፡፡ ወንበሩ ያቃስታል፡፡ ኮመዲናው ይንገዳገዳል፡፡ ኮመዲኖው ላይ ያለው ቴሌቪዥን ዘመን ያለፈበትና በድብደባ ምስል የሚያመጣ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ቢሆንም ማረፊያዬ ንፁህና ቁጭ በሉብኝ በሉብኝ፣ ተኙብኝ ተኙብኝ፣ እረፉብኝ እረፉብኝ የሚል አይነት ነው፡፡

የመኝታ ቤቴን መስኮት መጋረጃ ከፈትኩ፡፡ ዝነኛው…ከልጅነታችን አንስቶ የአስመራ ፖስትካርድ ላይ የምናየው የካቶሊክ ቤተክርስትያን ካቴድራል ከነ ሙሉ ግርማው ይታያል፡፡ በደስታ መጮህ አማረኝ፡፡

ከነደስታዬ አልጋው ላይ ሄጄ ዘፍ አልኩ፡፡ ፍራሹ ሰመጠ፡፡ አልጋው አቃሰተ፡፡

ማታ ላይ ፊልሞን እና የሃያ አመት ወጣት የሆነው ወንድሙ እራት ይዘውኝ ወጡ፡፡

ነጮች የሚበዙበት ለቅንጦት የቀረበ ቤት መሆኑን ስመለከት ከፋኝ፡፡

- እኔ ማየት የምፈልገው ሁሉም ሰው የሚሄድበትን ቦታ ነው..እንደዚህ አይነት ቦታ አታምጣኝ አላልኩም? አልኩት

- ለዛሬ ብቻ ነው…ከነገ ጀምሮ እንዲህ አይነት ቤት አንሄድም አለኝ ፊልሞን፡፡ ፊልሞን ጥርት ያለ አማርኛ ቢናገርም ወንድሙ ሳሚ ግን ጆሮውን ቢቆርጡት አይሰማም፡፡ ቢነቀንቁት አይናገርም፡፡

እድሜውን ላገናዘበ አስገራሚ አይደለም፡፡ ከሳሚ ጋር በእንግሊዝኛ፣ ከፊልሞን ጋር በአማርኛ፣ ከአስተናጋጆቹ ጋር ( ፊልሞን በይ በይ እያለኝ ) በሚያስቅ ቁርጥርጥ ትግርኛ ሳወራ ዞረብኝ፡፡

አስመራ ውስጥ ስቆይ አማርኛን በተመለከተ ያገኘሁት ስብጥር አስገራሚ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ምንም እንኳን ከአርባ የዘለለ እድሜ ቢኖሩም አማርኛን ጨርሶ አያውቁም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ቅኔ መዝረፍ ሲቀራቸው እንደ ውሃ ኩልል የሚል አማርኛ ያወራሉ፡፡ ብዙዎቹ ከ25 አመት በታች የሆኑ ልጆች አማርኛ አይችሉም፡፡ አንዳንድ በአስራ ቤትና እስከ ሃያ መጨረሻ ያሉ ደግሞ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ ፊልሞን ይህንን ሁኔታ እንዲያስረዳኝ ስጠይቀው እንዲህ አለኝ፡፡

‹‹አየሽ ኤርትራ ውስጥ በተለይ አስመራ ውስጥ ሶስት አይነት አማርኛ ተናጋሪዎች አሉ፡፡ አምቼ፣ ሰምቼ እና አብይቼ ይባላሉ›› ብሎ ጀመረ፡፡

‹‹አምቼ ኢትዮጵያ ተወልደው፣ ኢትዮጵያ አድገው፣ ኢትዮጵያ ኖረው ስንጣላ እዚህ የመጡ ናቸው፡፡ እነሱ እዛ በመኖራቸው አማርኛ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሰምቼ የሚባሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቲቪ በተለይ ቃና እያዩ አማርኛን ብዙ ጊዜ በመስማት የቻሉ ናቸው፡፡ አብይቼ የሚባሉት ደግሞ ዶክተር አብይን ከመውደዳቸው የተነሳ እሱ የሚለውን ለመስማት አማርኛ መማር የጀመሩ ናቸው…›› ብሎ አስረዳኝ፡፡

ከዚህ በኋላ የተለያዩ ሰዎች ምፅዋም አስመራም በአማርኛ ሲያወሩኝ ይሄኛው አምቼ ነው…ይሄ አብይቼ ነው…ይህች ደግሞ ሰምቼ እያልኩ መቦደን ጀመርኩ፡፡

እንዴት አደርሽ አስመሪና?

በነጋታው አስመራን በብርሃን ለማየት ማልጄ ነቃሁ፡፡ አስራ ሁለት ሰአት ላይ ካቴድራሉ ደወል ሲደውል ሰማሁ፡፡ በኋላ እንደሰማሁት ይሄ ደወል በየሰላሳ ደቂቃው ይደወላል፡፡ የአካባቢው አጃቢ ሙዚቃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቁርሴን ሆቴሌ በልቼ ወጣሁ፡፡

ፊልሞንን ሶስት ሰአት ላይ አግኝቼ መደበኛ ጉብኝቴን እስክጀምር አላስችል ብሎኝ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ካቴድራሉ ደረጃዎች ላይ ብዙ ሰዎች ተቀምጠው አየሁ፡፡ ጥቂቶቹ ጋዜጣ ይዘዋል፡፡ በኋላ ላይ እንደተነገረኝ በኤርትራ አንድ ለእናቱ የሆነውን ሃዳስ ኤርትራን ነው የሚያነቡት፡፡ ሌሎቹ አጠገባቸው ካለ ሰው ጋር ያወራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ዝም ብለው አላፊ አግዳሚ ይቃኛሉ፡፡

ያልተለመደ ሆነብኝ፡፡ አስፋልቱን ተሻግሬ አንዱ ደረጃ ላይ ተቀምጬ እንደገና አየኋቸው፡፡

ጋዜጣ የሚያነቡ፣ ከሌላ ሰው ጋር የሚያወሩ፣ አላፊ አግዳሚውን የሚቃኙ፣ ዝም ብለው የተቀመጡ እንጂ ብዙ ከተማ እንደተለመደው ስልካቸው ላይ ያቀረቀሩ ሰዎች የሉም፡፡ በስተቀኝ ወዳለው የአውቶብስ ፌርማታ ተመለከትኩ፡፡ ያው ነው፡፡

ሞባይላቸው ላይ የማያቀረቅሩት ኤርትራ በሞባይል ስልክ ኢንተርኔትን ማቅረብ ስላልጀመረች ነው፡፡ እየቆየሁ እንደተረዳሁት አስመራ ለኑሮ ውድ ከተማ ብትሆንም የኢንተርኔት ብርቅነትና ውድነት ግን አቻ የለውም፡፡  

በከተማው በብቸኝነት ኢንተርኔት አገልግሎት የሚያቅርቡት ተቋማት የኢንተርኔት ካፌዎች ሲሆኑ በቁጥር ብዙ በአገልግሎት ግን ውስን እና ውድ ናቸው፡፡ እየተቆራረጠ ጨጓራ ለሚልጥ ኢንተርኔት በሰአት ወደ አርባ ብር ገደማ ያስከፍላሉ፡፡

የባህር በር ያለው ሃገር ምንም እንኳን በሞባይል ባይሆንም በተገኘ ጊዜ ግን ጀት የሆነ ኢንተርኔት ይኖረዋል የሚለው ግምቴ አፈር የበላው ወይ ከቤተሰብ ለመገናኘት፣ ወይ እንደ ገበቴ ውሃ የሚዋልለውን የሃገሬን ሁኔታ ለመከታተል በሰአት 40 ብር ለኢንተርኔት ካፌዎች ስከፍል ነው፡፡  

 ያም ሆኖ ስልክ ላይ የሚያቀረቅር ህዝብ አለመኖሩ ከተማዋን ሕይወት ሰጥቷታል፡፡ ካፌ ስትገቡ ሰው አብሮት ካለው ሰው ጋር ይጫወታል እንጂ ስልኩ ላይ አያቀረቅርም ፡፡ ቢራ ይዞ ከወዳጁ ይስቃል እንጂ ስልኩን አስሬ አይነካካም፡፡ ከመንገድ ኬክ ቤት ተቀምጦ ኬኩን በሻይ እያማገ ከአልፎ ሂያጅ ውስጥ የሚያውቀውን ሰው አይቶ ና ተቀመጥ እያለ ያግደረድራል እንጂ ከቅርብ ሰው ተነጥሎ ከሩቅ አይገናኝም፡፡

የሆነ ደስ የሚል..እኛ ያጣነው እነሱ ግን የያዙት ነገር እንዳለ ተሰማኝ፡፡ ፌስቡክን ከፍቶ ወሬ የማየት ጉጉቴ ሰቅፎ ቢይዘኝም እፎይታ ግን ተሰማኝ፡፡

ፊልሞን እስኪመጣ ቁጭ ብዬ አላፊ አገዳሚውን ስመለከት ሌላ ነገር አስተዋልኩ፡፡ ሁሉም ሰው እቃውን ይዞ ላይ ታች የሚለው በተመሳሳይ ከቃጫ የተሰሩ ከረጢቶች ወይ ደግሞ በተሸለሙ ዘምቢሎች ነው፡፡ ዘምቢል ትዝ ይላችኋል?

ፊልሞን ሲመጣ ጠየቅኩት፡፡

‹‹እዚህ ሃገር ፌስታል ተከልክሏል፡፡ አስር አመት ሆኖታል›› አለኝ፡፡

አስመራን እየወደድኳት ነው፡፡ አስመራን በጣም እየወደድኳት ነው፡፡

(ይቀጥላል)

No comments