Latest

ብቻህን አይደለህም - ዳንኤል ክብረት



ብቻህን አይደለህም - ዳንኤል ክብረት

የቼሮቄ ጎሳዎች በደቡብ ምሥራቅ አሜሪካ የነበሩ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የቼሮቄ ወጣቶች ለዐቅመ አዳም መድረሳቸውን የሚገልጡበት አንድ ከባድ ፈተና አላቸው፡፡ ወጣቱን አባቱ ይዞት ሊመሻሽ ሲል ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡ ዓይኑን በጨርቅ ይታሠራል፡፡ ምንም ነገር ለማየት አይችልም፡፡  

ያንን ጨርቅም ከዓይኑ ላይ ለማንሣት አይፈቀድለትም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ይቀመጣል፡፡ ከተቀመጠበት ቦታም መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም፡፡ ጨለማው አልፎ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ በዚያ ጫካ ውስጥ ለብቻው አንድ ቦታ ተቀምጦ ማሳለፍና ‹ወንድነቱን› መፈተን አለበት፡፡ አካባቢው ጸጥ ያለ ነው፡፡ 

ከአራዊት ጩኸትና ኮሽታ በቀር ሌላ የለበትም፡፡ ሰውም በአካባቢው አይደርስም፡፡ ምግብና ውኃ የሚያቀብለውም የለም፡፡ የልብ ምቱን እያዳመጠ ሌሊቱን በጸጥታ ያሳልፈዋል፡፡ ይህን ሌሊት ያለ ችግር ለማሳለፍ የቻለ ወጣት ለዐቅመ አዳም ደረሰ ማለት ነው፡፡ እንዴት እንዳሳለፈውና ምን እንዳጋጠመው ከእርሱ በታች ላሉት ልጆች ለመናገር አይፈቀድለትም፡፡ እያንዳንዱ ወንድ የራሱን ማንነት በባህሉ መሠረት መፈተሽ አለበትና፡፡ 

በዚህ ሥርዓት መሠረት አንድ የቼሮቄ ወጣት በምሥራቅ ቴነሲና በሰሜን ካሮላይና ወደሚገኘው የቼሮቄ ደን ተወሰደ፡፡ ፀሐይ እየጠለቀች መሆኑን እያየ ነው የተጓዘው፡፡ አባቱ የዓይን ማሠሪያውን ጨርቅ ይዟል፡፡ ሌሎች ሸኚ የጎሳ አባላት ደግሞ ይከተሉታል፡፡ ጥቅጥቅ ያለውን ደን አቋርጠው ከዛፎቹ ርዝማኔ የተነሣ ፀሐይን ለማየት ወደማይቻልበት ሆድ ውስጥ ገቡ፡፡ ሌሊቱን የማሳለፊያው ቦታ ተመረጠ፡፡ ወጣቱም ዓይኑን በጨርቅ ታሠረ፡፡  


ታዛቢዎችም ዓይኑ በሚገባ የታሠረ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ከዚያም አንድ ቦታ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ሰዎች ተራ በተራ እየተሰናበቱት አካባቢውን ለቅቀው ሄዱ፡፡ ኮቴያቸው እየራቀው እየራቀው ሲሄድ ይታወቀዋል፡፡

አካባቢው ጸጥ ረጭ አለ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የዛፎቹ ንጽውትውታ ይሰማ ነበር፡፡ ነፋሱና ቅጠሎቹ ኅብረት ፈጥረው እያዝናኑት ነበር፡፡ እየቆየ ግን ሁሉም ነገር ረጋ፡፡ እዚህም እዚያም ‹ኮሽ› የሚል ነገር ይሰማል፡፡ ቱርር ብለው የሚያልፉ ነገሮች አሉ፡፡ በቼሮቄ ተረቶች ውስጥ ስለ ቼሮቄ ደን የሰማቸውን ተረቶችና ታሪኮች አስታወሰ፡፡ 


አዳኞች ወደዚህ ጫካ መጥተው ያፈጸሟቸው ጀብዱዎች፣ ያጋጠሟቸውንም ፈተናዎች፣ ያለፉባቸውንም ውጣ ውረዶች ይተርኩ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ደኑን በእግር አቋርጦ መውጣት ራሱ እንደ ጀግንነት ይቆጠር ነበር፡፡ መጀመሪያ በበትር እየገለጡ ለመሄድ የሚስቻለው ደን እየቆየ ግን ዓይን እስከመውጋት ይደርሳል፡፡ 

ጥቅጥቅ ይልና ቀኑን ጨለማ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ደን ውስጥ አልፎ አልፎ በጎሳዎች መካከል ውጊያ እንደተደረገ ይወራል፡፡ሌሊቱ እየጨመረ ሲሄድ ፍርሃት ይመጣበት ጀመር፡፡ ለምን እዚህ እንደመጣ፣ ይህንን ፈተና ሲያልፍ የሚያገኘውን ክብር፣ ክብሩ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡና ለጎሳው ሁሉ እንደሚተርፍ ሲያስበው እንደገና የብርታት መንፈስ ይወረዋል፡፡ 

650ሺ ሄክታር በሚደርሰው የቼሮቄ ደን ውስጥ ከ20 ሺ በላይ የእንስሳትና የዕጽዋት ዝርያዎች ይኖራሉ፡፡ ረዣዥም ተራሮች፣ ጫካ አቋርጠው የሚጓዙ ወንዞች፣ ገበታ የመሰሉ ሸለቆዎች፣ አስቸጋሪ ገደላ ገደሎችና ለጥ ያሉ ሜዳዎች በውስጡ አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ወጣቱ ያስባቸዋል፡፡ 

ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀውና የሚያስፈራው አንድ ነገር ነው፡፡ ብቻውን መሆኑ፡፡ ቼሮቄዎች ‹አሲ› ብለው በሚጠሯቸው ባህላዊ ቤቶቻቸው ውስጥ በአንድ ቤት አብረው የሚያድሩት ብዙ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ብቻውን የሚኖርም ሆነ ብቻውን የሚያድር የለም፡፡ አደን ሲሄዱ በጋራ ነው፤ ወንዝ ሲወርዱም በጋራ ነው፡፡ 


አሁን ግን ለብቻው በቼሮቄ ደን ውስጥ ያውም በሌሊት ቁጭ ብሏል፡፡ ዕንቅልፉ ይመጣና ይሄዳል፡፡ ብርታቱ ይመጣና በፍርሃት ይተካል፤ እንደገና ደግሞ በጀግንነት ስሜት ይወረራል፡፡ አንዳች አውሬ ቢመጣበት ምን ለማድረግ ይችላል? ሳያየው በድምጹና በአካሄዱ ብቻ ማንነቱን መለየት አለበት፡፡ 

ዓይኑ እንደተሸፈነ መከላከልና መቋቋምም አለበት፡፡ ያውም ብቻውን፡፡ የሚረዳው የለም፤ ምን እንደሆነ እንኳን ታሪኩን ሊነግርለት የሚችል የለም፡፡ቢቆስል የሚያያክመው፤ አውሬው ይዞት ቢሄድ የሚያስጥለው የለም፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያስብ ፍርሃቱ ያይላል፡፡

በሐሳብ ወዲያና ወዲህ እየተማታ ሌሊቱ ይገሠግሣል፡፡ አራዊቱ ይጮኻሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በአጠገቡ ናቸው፡፡ ከሹክሹክታ፣ እስከ ግሣት፣ ከሲርታ እስከ ፉጨት ድምጻቸው ይመጣል ይሄዳል፡፡ ዙሪያውን እየከበቡ የሚተራመሱ አራዊትም አሉ፡፡ በእግሩ ሥር ሲያልፉ፤ ሰውነቱን ታክከውት ሲሄዱ ይሰማዋል፡፡ ባህሉ ግን ካለበት ቦታ እንዲነቃነቅ አይፈቅድለትም፡፡ በጽናትና በትዕግሥት፣ ያለ ፍርሃትና ያለ ጭንቀት ባለበት እንደተቀመጠ የፀሐይዋን ምጽአት መጠበቅ አለበት፡፡ 


አራዊቱም፣ ነፍሳቱም፣ የጫካው ግርማም አያስጨንቀውም፡፡ የሚያስጨንቀው በዚያ ከልጅ እስከ ቅመ አያት በአንድነት በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ አድጎ በዚህ ጫካ ውስጥ ብቻውን መሆኑ ነው፡፡ ከአራዊቱ ይልቅ ብቸኝነቱ ያስፈራዋል፡፡ ለአራዊቱ አራዊት፣ ለነፍሳቱም ነፍሳት፣ ለዛፎቹም ዛፍ አላቸው፡፡ እርሱ ግን ብቻውን ነው፡፡ እንደዚህ ሌሊት ሰው ተመኝቶ አያውቅም፡፡ ግን ብቻውን ነው፡፡ እንደዚህ ሌሊት ሰው ናፍቆት አያውቅም፡፡ ግን ብቻውን ነው፡፡  


ሌሊቱ እየገሠገሠ ነው፡፡ ድካሙም እየጨመረ ነው፡፡ በዚያ የብርታቱ ሰዓት ያልመጡት አራዊት በዚህ የድካሙ ሰዓት ቢመጡ ምን ሊውጠው ነው? የኦኮናሉፍቴ ወንዝ ከዐለቱ ጋር እየተጋጨ ሲወርድ የሚፈጥረው ድምጽ ይሰማዋል፡፡ ወንዙ ከዐለቱ ጋር የሚጋጭበት ጋ ሲደርስ መልኩ ቡናማ ይሆናል፡፡ ወዲያው ደግሞ አካባቢው ቀስተ ደመና ይፈጥራል፡፡ አሁን ግን ሌሊት ነው፡፡ ምን እየሆነ እንደሆን አያውቅም፡፡ 


ሸለብ ሊያደርገው ሲሞክር የወፎቹን ድምጽ ሰማ፡፡ እየነጋ መሆኑን ሲያስብ ብርታቱ ተሰብስቦ መጣ፡፡ የመከራው ሌሊት እያለፈ ነው፡፡ ለዐቅመ አዳም የሚደርስበትና ሠፈሩ በከበሮ የሚናወጥበት ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ ጥቂት ከቆየ ፀሐይዋ ብቅ ትላለች፡፡ ዓይኑ የተሸፈነበትን ጨርቅ ማሞቅ ስትጀምር ያን ጊዜ ጨርቁን ይፈታዋል፡፡ ይህንን የብቸኝነት ጫካ እየዘለለ ለቅቆ ጎሳው በጉጉት ወደሚጠብቅበት ሥፍራ ይገሠግሣል፡፡  


እንደጠበቃት ፀሐይዋ መውጣቷን ዐወጀች፡፡ ዓይኑ የታሠረበት ጨርቅ መሞቅ ጀመረ፡፡ አሁን ጨርቁን መፍታት ይችላል፡፡ ብርዱ ያቆረፈደውን እጁን አፍታትቶ ጨርቁን በፍጥነት መፍታት ጀመረ፡፡ ቋጠሮዎቹን ቀስ በቀስ አላቅቆ ዓይኑን ነጻ ሲያወጣ፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች አካባቢው ተደናበረበት፡፡ 


ጸጥ ብሎ ቆየና ዓይኖቹን አሻቸው፡፡ ቀስ በቀስም አካባቢው በብርሃን እየተገለጠለት መጣ፡፡ ፊት ለፊት ወዳለው ጫካ ዓይኑን ሲወረውር ጉብታው ላይ አባቱን አየው፡፡ ውርጩ በላዩ ላይ ዘንቦበታል፡፡ ጦሩን ተክሎ ቀስቱን አንግቶ ተቀምጧል፡፡ 

ተወርውሮ ሄደና አቀፈው፡፡ ‹መቼ መጣህ?› አለው የልብሱ ቅዝቃዜ እየተሰማው፡፡

‹እዚሁ ነበርኩ› አለው አባቱ፡፡
‹ከመቼ ጀምሮ› አለው ልጁ፡፡
‹ከመጀመሪያ ጀምሬ›
‹ሌሊቱን እዚህ ነው እንዴ ያደርከው›
‹አዎ›
‹እኔኮ ብቻየን የሆንኩ መስሎኝ ነበር›
‹ብቻህን አልነበርክም፡፡ እኔ በንቃት እየተከታተልኩህም፣ እየጠበቅኩህም ነበር፡፡ አንተ ስታሸልብ እኔ ግን አላሸልብም ነበር፡፡ እዚሁ ነበርኩ፡፡ እያየሁህ ነበር፡፡ ምናልባት ግን ስለማታየኝ የሌለሁና ብቻህን የሆንክ መስሎህ ይሆናል፡፡ ግን አልነበርክም፡፡ ይህችን ቅጠል ታውቃታለህ? › አለው አባቱ ጎንበስ ብሎ አንዲት ሸካራ ቅጠል እየቆረጠ፡፡
‹አላውቃትም› አለ ልጁ፡፡
‹ይህቺ ቅጠል እባብና እርሱን የመሰሉትን የምታባርር ናት፡፡ ሽታዋን ከሩቁ ካሸተቱ በአካባቢዋ አይቀርቡም› አለው፡፡ 

ያንን ወንዝስ ታውቀዋለህ?› አለው በሩቁ ፀሐይዋ የምትንቦጫረቅበትን ወንዝ እያሳየ፡፡ 

‹እርሱንማ አውቀዋለሁ፤ የኦኮናሉፍቴ ወንዝ አይደል እንዴ› አለና መለሰለት፡፡ ‹ታድያ የቱ አውሬ ነው ይህንን ገደላማ ወንዝ ተሻግሮ የሚመጣብህ› አለ አባቱ እየሳቀ፡፡ ልጁም ሳቀ፡፡ ‹ይህንን ሌሊት ሌሊት የሚመጣ ወፍስ ታውቀዋለህ› አለና አንድ ሽው ብሎ ያለፈ ወፍ አሳየው፡፡ ልጁ ወፉን ለማየት የሚችልበት ርቀት ላይ አልነበረም፡፡ ወፉም በሽውታ ነው ያለፈው፡፡ 

‹አላየሁትም› አለው ልጁ፡፡


‹ይህ ወፍ ሌሊት ሌሊት ያጉረመርማል፡፡ እርሱ ወደሚያጉረመርምበት ቦታ አራዊት አይቀርቡም፡፡ እነዚህ ሁሉ ሳያውቁህና ሳታውቃቸው አንተን ሲጠብቁህ ነው ያደሩት፡፡ አየህ ልጄ አብረውህ ሲጠብቁህ ያደሩ ብዙ ናቸው፡፡ ወንዙ፣ ዛፉ፣ ተራራው፣ እነዚህ ሁሉ አብረውህ ነበሩ፡፡ 


ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔ አባትህ አብሬህ ነበርኩ፡፡ አንተ ግን ብቻዬን ነበርኩ አልክ፡፡ ብቸኝነትህን ያመጣው ብቻህን መሆንህ አይደለም፡፡ አብሮህ ያለውን አለማወቅህ እንጂ፡፡ ከዚህ ሌሊት እንድትማር የምንፈልገው አንዱ ትምህርት ሰው ምንጊዜም ብቻውን እንዳልሆነ እንድታውቅ ነው፡፡ 

አካባቢህን ካላወቅህ በሰዎች መካከል ሆነህ እንኳን ብቻህን ትሆናለህ፡፡ አካባቢህን ካወቅከው ግን መቼም ብቻህን አትሆንም፡፡› 

አባትና ልጅ በደስታ እየተጨዋወቱ ከጫካው ወጥተው በጉጉት ወደሚጠብቃቸው ሕዝብ ተቀላቀሉ፡፡

No comments