Latest

የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ የማንነትና የአከላለል ጥያቄ ከየት ወዴት፣ እንዴትስ ይፈታ?

የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ

[ውድ አንባቢዎች ይህን ጽሁፍ የላኩን የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ (የሆኑ) ሰው ናቸው። እርሳቸው የብዕር ስም ስለተጠቀሙ እኛም በዚሁ ስም ጽሁፉ እንዲወጣ አድርገናል። በወልቃይት ጉዳይ የሚያውቁትን መረጃ ያካፍሉናል። ጽፉን ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው አውጥተነዋል። መልካም ንባብ]

ከድልበቶ ደጎዬ ዋቆ 
(15/12/2010)


"በደል ከጥንብ ይገማል፣
ሰው አይወድም በደል፣
ከብት አይወድም ገደል።"
ያንተ ልጅ ሲበላ የኔ ልጅ አልቅሶ፣
ያንተ ቤት ሲታደስ የኔ ጎጆ ፈርሶ፣
የኔም መሄጃዬ ያንተም መጥፊያህ ደርሶ።"

እኔ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የከምባታ ተወላጅ ስሆን ርዕሰ ጉዳዩን በተመለከተ ለየትኛውም ተፋላሚ ወገን በአድልኦ የምፈርድበት ምክንያትም ሆነ ህሊና የለኝም፣ የማውቀውን እውነት በማስተጋባት በጉዳዩ ላይ ወሳኝ ስልጣን ያላቸው የመንግስት አካላት ከረጅም ጊዜ አንስቶ እጅግ አጨቃጫቂና ደም አፋሳሽ ሆኖ ያለአንዳች ሰላማዊ መፍትሄ ከአመት ወደአመት ሲንከባለል የቆየውን የወልቃይት ጠገዴ የማንነትና የአከላለል ጥያቄ በጥሞናና በሰከነ መንፈስ መርምረውና አጣርተው የማያዳግም ውሳኔ በማሳለፍ የአጎራባች ወንድማማች ማህበረሰቦችንና ህዝቦችን የፍቅር፣ የሰላምና የመተጋገዝ የዘመናት ታሪካቸውን እንዲያድሱ እንዲያበቃቸው ለማሳሰብና ለመለመን ብቻ ነው፣ ሁለቱም ህዝቦች በወንድማማችነት እንጂ በጠላትነት መፈላለግ የለባቸውምና።  

ስለወልቃይት ጠገዴ ዛሬ እኔ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጅ ለመናገርና ለመመስከር እንዴት ድፍረት አገኘህ ትሉኝ ይሆናል፣ መባልም ያለበት ተቀባይነት ያለው ጥያቄ ነው። ስለዚህም ቀጥሎ በተጠቀሰው መጣጥፍ ባጭሩ ለመግለፅና ስለመፍትሄውም ጭምር ያለኝን ግላዊ አስተያየትና ምክር ከዚህ ቀጥሎ ለመሰንዘር እሞክራለሁ።

በ1962 አም ከቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁ በሁዋላ በመንግሥት ሠራተኛነት የተቀጠርኩት በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ስር ይተዳደር በነበረው የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ነበር።  

በ1963/64 አም የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን በመላ አገሪቱ ስናቋቋም ለሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ የሚያገለግል ቅርንጫፍ መ/ቤት የተቋቋመው በጎንደር ከተማ፣ ለትግራይ በመቀሌ ፣ ለኤርትራ ደግሞ በአስመራ ከተማ እንደነበር አስታውሳለሁ። 

ያንጊዜ የጠቅላይ ግዛቱ ስያሜ የቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ተብሎ ሲጠራ የንጉሠነገስቱ እንደራሴና ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ኮሎኔል ታምራት ይገዙ ነበሩ፣ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ልኡል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የኤርትራ ደግሞ ልኡል ራስ አስራተ ካሳ ነበሩ።

በ1963 አም በወልቃይት ጠገዴ በሚገኘው የሁመራ መሬት ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ በሰፊው የሚያመርት "የወልቃይት ጠገዴ ሁለገብ የገበሬዎች ማህበር" ነበር፣ በማህበሩ ውስጥ አባል ሆነው ለመሰማራት የሚሹ ሁሉ ከኮሎኔል ታምራት ይገዙ ከጎንደር የድጋፍ ደብዳቤ እየተፃፈላቸው ነበር የሚመዘገቡት፣ አያሌ ሀብታም ባለትራክተር ግለሰቦችን ያፈራ የልማት ማህበር ነበር።  

የማህበሩ የቀን ሰራተኞች በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች እንደነበሩ ሳስታውስ (ልክ የወንጂና መተሃራ የስኳር ፋብሪካዎች የቀን ሰራተኞች በአብዛኛው የከምባታና የሀዲያ ተወላጆች እንደነበሩ ሁሉ) የሁመራ ከተማ ባለሆቴሎችም አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ወደሁመራ ከተማ የሱዳን ዜጎች ያለአንዳች ገደብ እየገቡና እየተዝናኑ እንደሚመለሱና ኢትዮጵያውያንም በነፃነት ወደሱዳን እየገቡ ይነግዱ፣ ይመላለሱ እንደነበር አስታውሳለሁ።

የወልቃይት ጠገዴ ሁለገብ የገበሬዎች ማህበር በወቅቱ ከአለም ባንክ ብድርና እርዳታ የሚያገኝ እጅግ የዳበረ ጠንካራ የእርሻ ልማት ማህበር ነበር፣ ምርታቸውን በተመለከተ ማሽላውን ወደከረንና አስመራ የሚያስጭኑ ሲሆን ጥጡንና ሰሊጡን በምጽዋ ወደብ በኩል ወደውጭ አገሮች ነበር ኤክስፖርት የሚያደርጉት። እነዚህን ምርቶች ወደምፅዋ የሚጭኑት የቀይባህር ኤርትራ የጭነት ማመላለሻ ማህበር እንደነበር አስታውሳለሁ።

እኛም የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር (ዛሬ የትራንስፖርት ባለሥልጣን) ቡድን በ1963 አም ወደሁመራ የሄድነው ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ማህበራት በጭነት ታሪፍ የተነሳ ስላልተስማሙ ለማስታረቅ ነበር፣ ባጭሩ ለመግለፅ፣ የሁለቱን ማህበራት መሪዎች በማወያየትና በማደራደር በኩንታል 3 ብር የነበረው የጭነት ታሪፍ ወደ4 ብር በኩንታል ከፍ እንዲል በማስማማት ወደጎንደር እንደተመለስን አስታውሳለሁ።

ያንጊዜ ማለትም የዛሬ 46 አመት ወልቃይት ጠገዴ ምንም በማያሻማና በማያወዛግብ ጂዎግራፊያዊ አቀማመጥና ፖለቲካዊ የግዛት ይዞታ የቤጌምድርና ስሜን አካል ሲሆን ከዚያ ወዲህ በዘመናዊ የወያኔ/ኢህአዴግ ነፍጠኛ አቅኚዎች በወረራ መልክ በሃይል ካልተያዘ በስተቀር ከዛሬው የአማራ ክልል ይዞታ ውጭ የሚሆንበት ታሪክ ሊከሰት አይችልም፣ በወሎ በኩል ከአላማጣ፣ ኮረምና ከራያ አካባቢዎች ተቆርሰው በጊዜአችን የህወሃት ወራሪዎች የተነጠቁትን ወረዳዎች ጨምሮ ("መሬት የሁሉም ናት ባለቤት የላትም፣ ሃይለኛው ያስገብራል እየሄደ የትም"፣ ሲል የኢጣልያ ተወላጅ ቹሊ የተባለ ሰው በትእቢት የተናገረውን ያስታውሷል!)።

ያንጊዜም ሆነ አሁን የቤገምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛትና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት የድንበር ወሰን ደግሞ የማያሻማና ግልፅ የሆነ የተፈጥሮ ወሰን የተከዜ ወንዝ እንደነበርና ዛሬም እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከሁመራ የሚጫነውም ምርት ተከዜ ሰቲትን ተሻግሮ ከኦምሀጀር (ኤርትራ) ወደምፅዋ ወደብ ድረስ የሚጓጓዝ ነበር።  

ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከደርግ ውድቀት ድረስ ወልቃይት ጠገዴ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነመንግስት (1923-1966 አም) የቤገምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ክልል፣ በደርግ ዘመነአገዛዝ ደግሞ (1966—83 አም) የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ክልል አካል ሆኖ ኖሮአል፣ በነዚያ የአገዛዝ ዘመናት አማራ የሚባል ክልል አልነበረም። 

ብዙዎች እንደሚያውቁት፣ ከ1965—70 አም ከአርማይጮ አንስቶ እስከቃፍትያ፣ መዘጋ፣ ጠለምት ጠገዴ፣ ወዘተ ባሉት አካባቢዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ሰራዊት በትግራይ ክልል በኢሮብ ምድር ከነበረው የአሲምባ ዋና ማእከል ወይም ቤዝ (base) በተጨማሪ እንደመከላከያ ምሽጎች የሚገለገልባቸው ስፍራዎች እንደነበሩ ይታወቃል። 

ነገር ግን በ1970 አም የኢህአፓ ሰራዊት ከሻእቢያ የፖለቲካ ጫና እንዲሁም ከህወሃትና ከኢዲህ የተቃጡበትን የጦር መሳሪያ ወራራ እና በውስጡ የተከሰቱትን የአንጃዎች ግጭትና ጫና መቋቋም ተስኖት ሲፈረካክስና ሲበታተን ከወልቃይት ጠገዴም በህወሃቶች ወረራ ተገፍቶ እንዲወጣ ተገደደ፣ ከዚያም ብዙዎች አባላቱ በሱዳን ለተወሰኑ ወራትና አመታት ቆይታ አድርገው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን አጋዥነት ወደተለያዩ የውጭ አገሮች ሲሰደዱ፣ ጥቂቶች ደግሞ ኢህዴን የሚባል የፖለቲካ ቡድን መስርተው ወደ ህወሃት የፀረ-ደርግ ትግል ወደውና ፈቅደው በአጋርነት ተቀላቀሉ፣ ሌሎች ደግሞ ለደርግ እጃቸውን ሰጥተው የኢህአፓን ህልውና በወሳኝ መልኩ እንዲያከትም አደረጉት፣ ዛሬ በአሜሪካና በአውሮጳ አገሮች ኢህአፓ አሁንም ትግሉን አላበቃም የሚሉ ግለሰቦች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ።

በሌላ አንፃር፣ አማራ የሚባል ክልል ቀድሞ ያልነበረ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አራማጆች የዘሩትን የጎሳ ፖለቲካና የረጩትን የዘረኝነት መርዝ ተከትሎ ‘የጥምቀት‘ ስያሜ ተሰጥቶት የተዋቀረው ከ25 አመታት በሁዋላ በ1987 አም የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከፀደቀ በሁዋላ ከሌሎች ተጨማሪ 8 ስምንት ክልሎች ጋር እንደነበር የሚታወስ ጉዳይ ነው።


ክልሎቹም የተዋቀሩት በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 46 መሠረት "በህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት" ስለነበር ከ46 አመታት በሁዋላ በመሬት ላይ የተከሰቱትን አስገራሚና ሊታመኑ የማይችሉ የቋንቋ፣ የማንነት፣ የስነልቦናዊና ማህበረሰባዊ ጥንቅር (demographic) ለውጦች እንዴት እውን ሊሆኑ እንደቻሉ በፍፁም አላውቅም፣ እነዚያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኩሩና ጀግና ወልቃይቶች ወዴት ተሰወሩ? 

በሙሴ መሪነት እስራኤሎች ከግብፆች ባርነት ተላቅቀው ወደከነአን ምድር ሲጓዙና የቀይ ባህርን በተአምር የባህሩ ውሃ በሙሴ ትእዛዝ ለሁለት ተከፍሎ ለመሻገር ሲችሉ ከባርነት በመለቃቀቸው የተቆጨው የግብፁ ፈርኦን ወታደሮቹን አሳድደው እንዲመልሷቸው ቢያዝም እነዚህ ወታደሮች ተከታትለው በመሄድ እንደእስራኤሎቹ ለመሻገር የሚቻላቸው መስሏቸው ወደባህሩ ሲገቡ እዚያው ተውጠው እንደቀሩ ሁሉ ወልቃይቶችም ባህር ካጠገባቸው ባይኖርም ምናልባት ወደተከዜ ወንዝ ተወርውረውና ተበልተው አልቀው ይሆን? ግራ የሚያጋባ እንቆቅልሽ ነው፣ አሳዛኝ የህዝብ ወገን ታሪክ ነው ።

አንድ በግልጽ መጤን ያለበት እውነታ እንደነበረ ከላይ መገለፁን አስታውሱ፣ ይሐውም ከ1967—70 አም በነበሩት አመታት የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በተለይም መዘጋ፣ ቃፍትያ፣ አዲረመጥ፣ አርማይጭዎና ሌሎች የስሜን ተራራ ኮረብታማ ወረዳዎችና ዋሻዎች የኢህአፓ (የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ሰራዊት ምሽጎች እንደነበሩ ይነገር ነበር።  


በ1970 አም ህወሀት የኢህአፓን ድርጅት ከአሲምባ ምሽጉ በጦር ሃይል አስገድዶ ሲያስወጣና ድርጅቱ ከውስጥ አንጃዎች፣ ከውጭ ደግሞ የህወሀትና የሻእቢያን ዱላ ለመቋቋም ባለመቻሉ ተፍረክርኮ ሲበታተን አብዛኛዎቹ ወደሱዳንና ወደተለያዩ አገሮች ሲሰደዱ የወልቃይት ጠገዴ ምሽጎቹን ለህወሀት ታጋዮች ለቅቆ መውጣት የግዴታው ስለነበር ይህንን እስትራተጂክ የሱዳን መውጫና መግቢያ በር ህወሀቶች ፈጥነው ለመቆጣጠር እንደበቁ ይታወቃል፣ ኢትዮጵያውያን እስከሆኑ ድረስ ጥያቄና ተቃውሞ አልተሰነዘረባቸውም በዚያን ዘመን። 

ከዚያን ጊዜ አንስቶ የህወሀት ሰራዊት አባላትና ደጋፊዎች የሁመራንና የአካባቢውን ለም የእርሻ መሬቶች ሁሉ ቀስ በቀስ በተወላጆቻቸው ቋሚ ይዞታ ስር ለመጠቅለል በቅተዋል ማለት ነው፣ በዚህም ሳቢያ የወልቃይት ነባር ተወላጆችን (ወልቃይቶችን) ልክ ጽዮናዊቷ እስራኤል ፍልስጤሞችን ከገዛመሬታቸው ቀስ በቀስ በግድም ሆነ በውድ፣ በግድያም ሆነ በማፈናቀል እንዲነቀሉና እንዲሰደዱ እንዳደረጓቸው ማለት ነው። 

በዚህም የተነሳ ዛሬ የብሄርተኝነት ነቀርሳ ባስከተለው መዘዝ የተነሳ በአንድ ወገን፣ የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የወልቃይቶች (የአማራ ክልል) ነው፣ ጥንትም ዛሬም፣ በሌላ ወገን ደግሞ የለም የትግራይ ነው ጥንትም ሆነ ዛሬ የሚሉ እርስ በእርስ የሚጣረሱ አቋሞች እየተራገቡ ናቸው። አሳዛኝ ትርክት ነው። ይህ በዚህ እንዳለ ቢሆንም፣ የኢህአፓ ርዝራዦች የነበሩት ጓዶች "ኢህዲን" (በሁዋላ "ብአዴን" ተብሎ የክርስትና ስያሜ በህወሀት ተሰጥቶት) የሚል የህወሀት ተቀጥላ ድርጅት መስርተው እስከዛሬ ለመዝለቅ በቅተዋል።

ሆኖም በኢፌዴሪ ህገመንግስት ድንጋጌዎች መሰረት የተከናወኑት የክልሎች/የዞኖችና የልዩ ወረዳዎች የወሰን አከላለል ሂደቶችና አፈፃፀሞች በሰላማዊ መንገድ የተከናወኑ ሣይሆን በተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ደምአፋሳሽ ሁኔታዎች ተከስተዋል፣ የሰዎች ህይወት ሳይቀጠፍና የንብረት ውድመት ሳይኖር የተከናወነ የወሰን አከላለልና አወቃቀር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ዛሬ የወልቃይቶችንም ሆነ የማንኛውንም ዘውግ ማንነት የሚወስኑት ራሳቸው ማህበረሰቦቹ እንጂ ማንም ሌላ አካል የነርሱን የዘውግ ማንነት እንደቦሎ አይለጥፍላቸውም ፣ እንዲሁም ያለፈቃዳቸውና ያለፍላጎታቸው ወደየትኛውም ክልል እንዲካለሉ መወሰን የማንም ስልጣን አይደለም። 


ይህንን የመወሰን መብት የራሳቸው የወልቃይቶች የማይገሰስ መብት ነውና። በሌላ አንፃር፣ በኢፌዴሪ ሕገመንግሥቱ አንቀጽ 48 መሠረት፣ "የአከላለል ለውጥ ወይም የክልል ወሰን የመደንገግ ወይም የመለወጥ/የማሻሻል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ ጉዳዩ በማህበረሰቡና በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት መፈጸም ይኖርበታል። እነዚህ ለመስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የህዝብ አሰፋፈርንና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ"፣ በሕገመንግሥቱ ተደንግጓል ። 

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ራሱ ደርግን የገረሰሱት የአሸናፊዎቹ የህወሃት ትሪክት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰፊ ጊዜ ወስዶና በበቂ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ያሳለፈውን ስምምነትና ውሳኔ እንዳልነበር በጊዜው የነበርን የቅርብ ተሳታፊዎችና ታዛቢዎች በትክክል የምንመሰክረው እውነታ ነው።  

ልክ እንደቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነመንግስቱ የ1923 እና የ1948 አም ሁለት ህገመንግስቶችና እንደደርጉ የ1979 አም የኢህዲሪ ህገመንግስት የወያኔ/ኢህአዴግ የ1987 አም የኢፌዴሪ ህገመንግስትም "ለሚወዱትና ለሚወዳቸው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች"፣ ወድደውና ፈቅደው የሰጡት ስጦታ ነው። በዚህም የተነሳ ሰጪዎቹ ባለፉት 27 አመታት ህገመንግስቱን እንዳሻቸው ሲጥሱ በመቀጠላቸው ሰነዱ የወረቀት ላይ ነፃነት ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

ለማንኛውም የወልቃይት ጠገዴ የማንነትም ሆነ የአከላለል ጥያቄ በኢፌዴሪ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች ምላሽ የሚያገኝ ውስብስብ ጉዳይ አይደለም፣ በዛሬው ዘመን የትግራይ ነፍጠኛ ወራሪዎችና ጉልበተኞች በቅኚነት ተይዞ የቆየ የአማራ ክልል ይዞታ ስለሆነ ያለአንዳች ቅድመሁኔታና ማካካሻ ለወልቃይት አማራ ማህበረሰብ በአስቸኳይ መመለስ የግዴታ ይሆናል፣ የሚመለከታቸው የፌደራልና የሁለቱም ክልሎች የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን አሁንም በአግባቡ ለመወጣት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።  


ለወልቃይት ጠገዴም ሆነ ከወሎ ጠቅላይ ግዛት ተቆርሰው የተወሰዱትን የአላማጣ፣ የኮረምና የራያ አዘቦ የአማራ ይዞታ የነበሩትን መሬቶችንም ሆነ ከአፋር ክልል በጉልበት የተወሰዱትን መሬቶች ጭምር በተመለከተ የፌደራል መንግስት ብዙ ጊዜ ሳይወስድ የማያዳግም የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጠውና የአካባቢው ሰላም እንዲከበር ሊያደርገው ይገባል፣ ይቻላልም።

በመጨረሻም፣ የፌዴራል አባላት ክልሎችን ወሰን በተመለከተ በየጊዜው መከለስና ለህዝቦች መስተጋብር በሚያመች ሁኔታ ጂዎግራፊን፣ የኢኮኖሚ አዋጪነት፣ የማህበረሰብ አሰፋፈር ፣ የሚመለከታቸው ወገኖች ፍላጎት፣ የክልሎች እኩልነት ወይም ተመጣጣኝነት፣ ወዘተ መስፈርቶች በመጠቀም ማካለል አዲስ ክስተት አይደለም፣ ከናይጄሪያ እስከ ህንድ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካናዳ፣ ከስዊትዘርላንድ እስከአውስትራልያ ያሉት የፌዴራል አገሮች በየጊዜው የአባል ክልሎቻቸውን ወሰኖች ይከልሳሉ፣ ያሻሽላሉ፣ ይለውጣሉ። 


የኢትዮጵያ መንግስትም የወልቃይት ጠገዴንም ሆነ ሌሎች የፌደራል ክልሎችን በተመለከተ በየጊዜው የሚነሱትን ጥያቄዎች እየመረመረና እያስጠና በተመሳሳይ አካሄድ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲቋጩ ማድረግ ይኖርበታል፣ በነዚህ አይነት የማንነትና የአከላል ጥያቄዎች የተነሳ አስፈለጊና ተገቢ ያልሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግጭቶች ደም—አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ክስተቶችን ማስከተል በፍፁም አይኖርባቸውም። 

ከዚህ ውጭ በማወቅም ሆነ ከግንዛቤ እጦት በመነጨ አጉል እንቅስቃሴ የሁለቱን ክልሎች ወንድማማች ህዝቦች ወደግጭትና ወደጠላትነት የሚያስገባ እንቅስቃሴ ሁሉ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ አጥብቀን እንጠይቃለን፣ በዚህ ረገድ የሚደረገው አሉታዊ እንቅስቃሴ ወይም ሴራ ሁሉ በፅኑ መወገዝ አለበት። የህዝብ እውነት ምንጊዜም አቸናፊ ነው።

No comments