Latest

በግፍ በኢትዮጵያ እስር ቤት 11 ዓመታት የተደበቀው የወልቃይት ተወላጅ ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ (በለገሠ ወ/ሃና)



ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ


ውድ አንባቢ ሆይ ይህንን ጽሁፍ ካነበቡ በኋላ ለሌሎች ያስተላልፉ ዘንድ እንጠይቃለን!!

ከዓመታት በፊት ልሳነ ግፉዓን የሚባል ተቋም ከወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጥፋታቸውን በሚዲያ ሲገልፁ ሰምቼ ነበር ምን አልባት ከነዚህ ደብዛቸው ከጠፉት የወልቃይት ልጆች አንዱ ዘካርያስ ይሆን?

አቶ ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ነው በአዲስ አበባ በንግድ ስራ ተሠማርቶ ውጤታማ ነገዴ መሆን የቻለ ሰው ነበር በመዲናችን አዲስ አበባ ላይ ጎጆ ቀልሶ ንግዱን እያከናወነ የሚኖረው አቶ ዘካርያስ ነሐሴ 14/2000 ዓም በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በደህንነቶች ቁጥጥር ስር ዋለ።

በቁጥጥር ስር ያዋሉት ግለሰቦች መጀመሪያ አዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን /3ኛ /አሰሩት ከተወሰነ ወራት በኋላ ቦሌ ፓሊስ መምሪያ ቀየሩት እንደገና ከወራት በኋላ አራዳ ክ/ከተማ የሚገኝ ፓሊስ ጣቢያ አዛወሩት። 


ከዚህም ከወራት በኋላ ልደታ ክ/ከተማ የሚገኝ ፓሊስ ጣቢያ ይዛወራል ከልደታ ወደ ቃሊቲ ተወስዶ ለወራት ከታሰረ በኋላ ወደ ቅሊንጦ በመጨረሻም አሁን ወደሚገኝበት ቃሊቲ አዛውረው ያስሩታል ከእስር ቤት እስር ቤት እያዘዋወሩ ያሰሩት አቶ ዘካርያስ ከሶስት አመት ክርክር በኋላ ፍርድ ቤት ነፃ ይለዋል።  

እስካሁን ያሰረኝን ሳላውቅ ሶስት አመት ተንገላታሁ አሁን ነፃ ተብያለሁ ፍቱኝ የሚል ጥያቄ ያቀርባል አዎ ነፃ ተብለሃል ግን ይግባኝ ተጠይቆብሃል ተብሎ ፍች ሲጠብቅ በይግባኝ እስር ቤት ሆኖ ለ2 ዓመት በክርክር ያሳልፋል ከ5 ዓመት እስር በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነፃ ይወጣል። 

አሁንም ነፃ ወጥቻለሁ ፍቱኝ የሚል ጥያቄ ያቀርባል አዎ በዚህ ክስ ነፃ ተብለሃል ግን ሌላ የ17 ዓመት ፍርድ አለብህ ይባላል ዘካርያስም ማን ከሶኝ መቼስ ክስ ደረሰኝ በየትኛው ፍርድ ቤት ቀርቤ ተከራክሬ ነው የተፈረደብኝ የፈረደብኝ ፍርድ ቤት ውሰዱኝ የሚል ጥያቄ ያቀርብና ፍርድ ይወስዱታል።

ፍርድ ቀርቦ 17 ዓመት የተፈረደብኝ በምን ወንጀል ነው ? ማነው ከሳሼ ? ክስ አልደረሰኝ የመሳሰለውን ጥያቄ ያቀርባል ዳኛው እኛ አልፈረድንም የምናውቀው ነጻ መውጣትህን ነው ታዲያ ማነው 17 ዓመት የፈረደብኝ ? እኔ ተከራክሬ ነፃ ወጥቻለሁ መፍቻ ፃፉል የሚል ጥያቄ ለዳኛ ያቀርባል ዳኛ ያንተ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው መፍቻ አንፅፍም የሚል መልስ ይሰጠዋል።  

ዘካርያስ ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ክርክር ይጀመራል ዳኛው ለዘካርያስ መፍቻ ከመጻፍ ይልቅ 6 ዓመት ቅጣት ማን እንደፈረደ ባልታወቀው 17 ዓመት ላይ 6 ዓመት ጨምሮ በድምሩ የ24 ዓመት ፍርድ ተፈርዶበት ወደ ቃሊቲ እስር ቤት በልዩ ቅጣት ኮንቴነር ቤት ወደሚባለው ጨለማ ቤት ይወረወራል ዘካርያስ ጉዳዩን የሚከታተሉለት ጠበቆች ቢያቆምም በስውሩ እጅ 8 ጠበቆቹ የሱን ጉዳይ እንዲተው በማስፈራራት 8 ጠበቆች አባረውበታል።

በዚህ ሁኔታም ሆኖ ዘካርያስ ተስፋ ሳይቆርጥ ለፍትህ ሚኒስትር አቤቱታ ያቀርባል ፍትህ ሚኒስቴር በዚህ የመዝገብ ቁጥር .... ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ የሚባል ሰው አናውቅም በዚህ መዝገብ ቁጥር አማን ከሊፋ የሚባል ሰው ነበር የተከሰተው እሱም በሽግልና ጉዳዩ በማለቁ መዝገቡ ተዘግቷል የሚል መልስ ፍትህ ሚኒስትር ለዘካርያስ ገ/ፃዲቅ ደብዳቤ ይልካል።  

ዘካርያስም አቤት የሚልበት ተቋም በማጣቱ ከነሐሴ 14/2000 ዓም ጀምሮ በልዩ ልዩ እስር ቤት ዛሬም ድረስ የመከራ ጊዜውን እየገፋ ይገኛል በተለይ ቃሊቲ እስር ቤት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሰኔ 26 /2010 ዓም ድረስ ከሰው ተለይቶ መታሰሩን ገልጿል። 

ከሰኔ 26/2010 ዓም ጀምሮ ቃሊቲ ዞን 6 ከሰው ተቀላቅሎ ማን እንዳሰረው ማን እንዳሳሰረው ሐምን እንደታሰረ ሳያውቅ 11 ዓመታት አስቆጥሯል ።

ለመንግሥት ሀላፊዎች

ላለፉት 27 ዓመታት ልክ እንደ ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ በግፍ የታሰሩ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው እና በአገዛዙ ሰዎች ቀጭን ትዕዛዝ በርካታ ዜጎች በግፍ ታስረው እንደሚገኙ የታወቀ ነው በአሁኑ ሰዓት የመንግስትነት ስልጣን የጨበጣችሁ ሰዎች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ እስር ቤቶች ላይ ፍተሻ በማድረግ ያለ አግባብ የታሰሩ ሰዎች ነፃ እንዲወጡ ታደርጉ ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ።

ለሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች

ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ እና እንደሱ በግፍ የታሰሩ ወገኖችን ጉዳይ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ እስር ቤት የተወረወሩ ወገኖችን ጉዳዩ በማጣራት ከግፍ እስር ነጻ እንዲወጡ ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ አስተላልፋለሁ ።

No comments