Latest

የቂሊንጦ እስር ቤት ለምን ተቃጠለ? የነሃሴ 28/2008 ዓም ማስታወሻ (ጌታቸው ሽፈራው)

የቂሊንጦ እስር ቤት ለምን ተቃጠለ?

የሰው ልጅ ጭቆናን በቃኝ፣ አገዛዝን አሻፈረኝ ከሚሉት እንሰሳት መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው የሚያስብ እንሰሳ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ የወደፊት ህይወቱ ተስፋ ሲያጣ፣ በደል ሲበዛበት፣ በመሰሉ ከመጠን በላይ ሲገዛ ሕይወቱን የሚያሳጣው ቢሆን እንኳ ከማመፅ ወደኋላ አይልም፡፡  


በመገዛቱ ቂም ሲያካብት፣ ጥላቻ ሲያዳብር ደግሞ እርምጃው የከፋ ይሆናል፡፡ መኖርያውን ብቻ ሳይሆን እራሱን ያቃጥላል፡፡ ቂሊንጦም የተከሰተው ይኸው ነው፡፡

ምግብ፣ ልብስና መጠለያ የሰውን ልጅ እስረኛ ነው ተብሎ የሚነፈገው ነገር አልነበረም፡፡ በቂሊንጦ እስር ቤት እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች ሳይቀር በተለያየ መንገድና ደረጃ ይከለከላሉ፡፡ ምግብ ተብሎ ለእስረኛ የሚቀርበው አሳሪዎቹ ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን የክብር ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡ ‹‹ደያስ›› ተብሎ የሚጠራው ለእስረኛው የሚቀርበው ምግብ ለሰው ይቀርባል ተብሎ ለማሰብ የሚከብድ ነው፡፡  

‹‹ምግቡ››ን የቀመሰ ሰው ሰሪዎቹ እህልን የማበላሸት ብቃታቸውን ያደንቃል፡፡ እንደሰው ለማይመለከቱት እስረኛ ምግብን እንዳይበላ አድርገው በመስራት አዲስ ግኝት የፈጠሩ ይመስላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ድረስ የጨውን ያህል የረከሰ ነገር ባይኖርም ቢያንስ ጨው እህልን እንደሚያጣፍጥ ያውቃሉና ብናኝ ጨው እንኳ አይጨምሩበትም፡፡  

ቅባት የሚታሰብ ነገር አይደለም፡፡ እስረኛው ከምግቡ ጣዕም የለሽነት ባሻገር የሚጨነቀው ለሽታው ነው፡፡ እስረኛው ለምሳና ራት ተብሎ የሚታደለውን ወጥ የሚያስቀዳው አፍንጫውን ይዞ ነው፡፡ ሰው ይበላዋል ተብሎ የተዘጋጀ፣ ነገር ግን ያን ያህል ለምን እንደሚሸት አይገባኝም፡፡ 

ጨው መጨመር ያልፈለጉ ሰዎች፣ እስረኛው ሌሊት እንዳያመልጥ የሚያደነዝዝላቸውን የእንቅልፍ ክኒን ግን በገፍ ይጨምሩበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ወጥ ተብዬው ላይ የሚታየው ቅመምና ቅባት ሳይሆን የላርጋቲን (የእንቅልፍ ክኒን) ለኸት ነው፡፡ ከወጡ በተጨማሪ፣ እንጀራው ከመኮማጠጡም በላይ አንጀት የሚያርድና ለብዙዎቹ የጨጓራ በሽታ መንስኤም ሆኗል፡፡  

የእስር ቤቱ አስተዳደሮች እስር ቤቱ የሚያቀርበውን ምግብ እንደመቅጫ ዘዴ ስለሚያዩት ይመስላል፣ ከቤተሰብ ምግብ ሲገባ ደስ አይላቸውም፡፡ በፈለጉ ቀን ደግሞ የቤተሰብ ምግብን ይከለክላሉ፡፡ የምግቡን መጠን ጭምር የመወሰን መብትን ለራሳቸው አቀዳጅተዋል፡፡ ማን ከማን ጋር መብላት እንዳለበትና እንደሌለበት ጭምር ይወስናሉ፡፡ ይህ በመጨረሻ ያመጣውን ጦስ የምናየው ነው፡፡

እስር ቤት ውስጥ ሌላኛው ትልቅ ችግር ማደሪያ (መጠለያ) ነው፡፡ ሰው ጠባብ ግቢ ውስጥ ቀኑን አሳልፎ፣ የማይከፈትም ከሆነ ሲጫወት ውሎ ሌሊት ሲመጣ የሚያስጨንቅበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ሌሊት ሁሉም እስረኛ ወደ ቤት ስለሚገባ ክፍሉ ይጨናነቃል፣ ቤቱ ይግላል፡፡ 

ቀን ፖሊስ ሲያዳፋው የዋለውን እስረኛ፣ ሌሊት ደግሞ ትኋንና ቅማል ይቀበለዋል፡፡ የቂሊንጦ ቤቶች ስፋታቸው ቢበዛ እስከ 150 ካሬ ሜትር ቢሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ ከ130-150 እስረኛ ያድርባቸዋል፡፡ ከቃጠሎው በኋላ እስከ 170 ሰው ታጉሮባቸዋል፡፡  

እነዚህ ቤቶች ውስጥ፣ ተደራራቢ አልጋ የነበር ቢሆንም በርካታ እስረኛ የሚተኛው መተላለፊያ ላይ ሲሆን ከአልጋ መሃል ቦታ ሊያገኙ የሚችሉት ጓደኛ እና ገንዘብ ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ መንገድ ላይ በቆሻሻ ፍራሽ ላይ ወድቀው የሚያድሩ እስረኞች፣ አላፊ አግዳሚው ሲረግጣቸው አድሮ፣ ቀን እቃቸውን ማስቀመጫ አያገኙም፡፡

አንድ እስረኛ አልጋ እስኪያገኝ በዚህ ሁኔታ ለወራት ይቆያል፡፡ ከእስር ቤቱ አስተዳደሮች ጋር፣ በሆነ ባልሆነው ግጭት ውስጥ የገቡ እስረኞች ቤት ውስጥ አለኝ የሚሉትን ትልቁን ንብረት፣ አልጋቸውን ተቀምተው መተላለፊያ (ደቦቃ) ላይ እንዲተኙ ይቀጣሉ፡፡ 

ከዚህ ሲብስ ደግሞ፣ ሌትም ቀንም ተዘግቶ ወደሚውለውና ምንም አይነት የፀሃይ ብርሃን ወደማያገኙበት ጨለማ ቤት ይላካሉ፡፡ እንደ ቂሊንጦ አይነት እስር ቤት ውስጥ፣ ሰው ሀገሩን ብቻ ሳይሆን በጠባብ ቤቱ ውስጥ የነበረውን አልጋ፣ ይህ ባይሆን እንኳ ሰላማዊ እንቅልፍ የሚተኛበትን ወለል ሁሉ የተቀማ የባይተዋሮች ባይተዋር ነው፡፡

እስር ቤት የሚዘነጥበት ቦታ ባይሆንም፣ እስረኛም እንደማንኛውም ሰው ልብስ ያስፈልገዋል፡፡ እስከ 2008 ዓ/ም ክረምት መግቢያ ድረስ፣ ቂሊንጦ ውስጥ ማንም የፈለገውን መልበስ ይችል ነበር፡፡ ሆኖም የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመፅና በዚህ ሰበብ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈፅመውን በደል እስረኞች ጥቁር ልብስ በመልበስ መቃወም ሲጀምሩ፣ እስረኞች ዩኒፎርም እንዲለብሱ የሚያስገድድ ሕግ ተግባራዊ ሆነ፡፡ 

እስረኞች ጥቁር ልብስ ለብሰው ወደ ፍርድ ቤት በሚሄዱበት ወቅት በእስር ቤቱ አስተዳደሮች ትዕዛዝ ልብሳቸውን ተቀምተው፣ ራቁታቸውን ወደ ማደሪያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ብዙዎቹ ተደብድበዋል፡፡ ፍርድ ቤት አንቀርብም ያሉት እነ በቀለ ገርባ በቁምጣ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት ተገደዋል፡፡ ልብሳቸውን አናወልቅም ያሉ ወጣቶች፣ እጃቸውን በካቴና ታስረው ተደብድበዋል፡፡ 

እነዚህ ወጣቶች እጃቸውን ታስረው እንዲያድሩ ስለተወሰነባቸው ይህን የተቃወሙት እነ ዮናታን ተስፋዬና ፍቅረማርያም አስማማውን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች መዳረሻቸው የፀሃይ ብርሃን ወደሚከለከልበት ጨለማ ቤት ሆኗል፡፡ እስረኛው አስቦ ለበሰው አለበሰው ጥቁር ልብስ (ሙሉ ላይሆን ይችላል) ተቀምቶ ሳይመለስለት ቀርቷል፡፡ 

ጥቁር ልብስ ለብሰሃል ተብለው ፍርድ ቤት እንዳይሄዱ ከተከለከሉት እስረኞች መካከል እኔም አንዱ ነኝ፡፡ ሆኖም እስረኛውን ከፍርድ ቤት ስለሚያስቀሩት፣ በካቴና ስለሚታሰር ወይንም ስለሚደበደብ ብቻ የአዘዦቹን የልብስ ምርጫ ሊቀበል አልቻለም፡፡

የእስረኛውን የጥቁር ልብስ ተቃውሞ ለማብረድ ዩኒፎርም እንደ ዋነኛ አማራጭ ተወሰደ፡፡ ትህነግ (ህወሓት) ከባለሃብቶች ጋር ተዋውለው ጥራቱ እጅግ የወረደ፣ መካከለኛም፣ ትልቅም ተብሎ ተመሳሳይ፣ በተለይ ሱሪው ሰፋፊና ረዣዥም ዩኒፎርም አስፍተው እስረኛውን በግድ ለማልበስ ሞከሩ፡፡  

ይህ አንድ ዩኒፎርም በ750 ብር ዋጋ የመጣ ነው ቢባልም ኩንትራቱን ከወሰዱት አንዱ ለቂሊንጦ በ175 ብር እንዳስረከበው በሙስና ለታሰረ ዘመዱ አረጋግጦለታል፡፡ እስረኛው በወጉ ያልተሰፋውን ዩኒፎርም መርፌ ደብቆ አስገብቶ አጥብቦና አሳጥሮ ልብስ አስመስሎ በመስፋቱ ይደበደባል፡፡ 

ያን በወጉ ያልተሰፋ ልብስ ካለበሰ ቤተሰብ አታገኝም፣ ፍርድ ቤት መሄድ አትችልም ሲባል አማራጭ ሲያጣ መልበስ ነበረበት፡፡ እየቀፈፈውም ቢሆን ልብሱን ለመልበስ ተገዷል፡፡ እየጠላው፡፡

ከዚህ ወጭ እስረኛ በሆነ ባልሆነው ይደበደባል፣ ጨለማ ቤት ይገባል፡፡ የትህነግ (ህወሓትን) ስም በክፉ ያነሳ የትኛውንም በደል መፈፀም ስራቸውን ማከናወን በሚቆጥሩት የእስር ቤቱ አስተዳደሮች ጥርስ ውስጥ ይገባል፡፡ እስረኛ የሰው ልጅ እንደሆነ አይታሰብም፣ ኢትዮጵያዊ ነው ብለው አያምኑትም፡፡  

ገና የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ለእነሱ ግን ፍርደኛ ነው፡፡ በሽብር የተከሰሰው ሽብርተኛ ነው፡፡ በነፍስ የተከሰሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ በስርቆት የተከሰሰው ሌባ ነው፡፡ እነሱ ከፍርድ ቤት ቀድመው ፈርደውበታል፡፡ ፈርደውበት ያገልሉታል፡፡ 

ለአብነት ያህል በፖለቲካ የተከሰሰ ሰው ገና ንፁህና ጥፋተኛ መሆኑ ሳይታወቅ የትኛውም አይነት ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ ወይንም የአስተዳደር ቦታ ውስጥ እንዳይገባ ይከለከላል፡፡ ነፃ ሲባል እንኳ አይለቁትም፡፡ ለማዕከላዊ ደውለው መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ‹‹ያ አሸባሪ ነፃ ተብሏል ተረከበን›› ብለው፡፡ ማዕከላዊ ተቀብሎ ደብድቦ፣ የሀሰት ምስክር አዘጋጅቶ ሌላ የ‹‹ሽብር›› ክስ ይመሰርታል፡፡

ይህ ሁሉ በደል በተከመረበት ሌላ እሳት ጨመሩ፡፡ ለመብላት ይቅርና ሽታው የሚያውከውን ምግብ ብቻ እንጅ የቤት ምግብ መመገብ እንደማይቻል የሚያትት የአዛዦቹ ሕግ ወጣ፡፡ ማንኛውም እስረኛ ከቤተሰብ የቤት ምግብ እንዳይገባለት ተከለከለ፡፡ 

ከዛ በፊት የፖለቲካ ጥያቄ ሲነሳ፣ ሀገራዊ ጉዳይን በተመለከተ የርሃብና ሌሎች አድማዎች ሲደረጉ ብዙ እስረኞች አይሳተፉም ነበር፡፡ የምግብ ጉዳይ ግን የሁሉም ጉዳይ ሆነ፡፡ በሙስና የተጠረጠሩት ሳይቀሩ በእስር ቤቱ ሕግ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በነፍስ፣ በውንብድና እና በመሰል ወንጀሎች የሚገቡና በተለምዶ ‹‹ዱርዬ›› ተብለው የሚጠሩት እስረኞች በቤተሰቦቻቸው ከሚጠየቁት መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ እስረኞች ከእስር ቤቱ አስተዳደር ጋር የማይስማሙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ እስረኛውን ለማሳደም ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ናቸው፡፡

ነሃሴ 26/ 2008 ዓ/ም ከቤተሰብ ምግብ እንዳይገባ የወጣው ማስታወቂያ ለነሃሴ 28/2008 ዓ/ም ተግባራዊ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ ይህ የእስር ቤቱ ውሳኔ ገና ማስታወቂያው የወጣ ቀን ዞን ሶስት የሚባለው የእስር ክፍል ላይ አድማ በመጀመሩ ምንም አልመሰላቸውም፡፡ 

በዚህ ወቅት ከየ እስረኛው ተመርጠው የዞን ወኪሎች የሆኑ እስረኞች የእስር ቤቱን ዋና አስተዳደር ኮማንደር ተክላይን ‹‹ምግብ በመከልከሉ ምክንያት እስረኛው ተቆጥቷል፡፡ በልብሱ ተማሯል፡፡ ብዙ የሚያስመርሩ ነገሮች አሉ፡፡ ይህኛው ሲጨመር ችግር ይከሰታል፡፡ ቢያንስ እናወያየው›› ብለው ጠይቀው ነበር፡፡ የኮማንደር ተክላይ መልስ ‹‹እስረኛን እሽሩሩ አንልም›› የሚል ነበር፡፡ እንሰሳ እንኳን የማይበላው ምግብ ለሚያዘጋጅለት እስረኛ፣ ከቤተሰቡ ምግብ መቀበል፣ እሹሩሩ ማለት ነው ለእሱ፡፡

በአስተዳደሮቹ ግትርነት የተበሳጨው እስረኛ፣ ቅዳሜ ማንም እስር ቤቱ የሚያድለውን ምግብ (ቁርስ) እንዳይበላ ተስማማ፡፡ የቅዳሜውን የአድማ መንፈስ አርብ ማታ የተረዱት አዛዦች በማታው ቆጠራ እስረኛውን በዱላ ለማስፈራራት ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ 

ጠዋት ቁርስ ሲመጣ ሻይ የያዘው ጎላና ዳቦ የያዘው ኬሻ ውጭ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ ለቆጠራ የመጡት ፖሊሶች ይህ ቁርሱ እንዲገባ ቢያዙም የሚሰማቸው አላገኙም፡፡ አድማው የበረታ መሆኑን ሲያውቁ እስረኛው ከማደሪያው ወደ ካፌ፣ ሱቅ፣ ቤተመፅሃፍትና ሌሎች አገልግሎት የሚያገኝባቸው ቦታዎች የሚሄድበትን የግቢውን በር ዘግተው ወጡ፡፡ ሌላ ጊዜ ጠዋት ጠዋት ይህ በር አይዘጋም፡፡  

ትንሽ ቆይተው ራቅ ብለው እስረኛውን መከታተል ጀመሩ፡፡ በርካታ መሰረታዊ መብቶቹን ተከልክሎ የምግብ ደረጃ የሌለውን የእስር ቤቱን ‹‹ሬሽን›› ብቻ እንዲበላ ለተወሰነበት እስረኛ የብሶቱ ማንደጃ ሆነ፡፡ የግቢው በር እንዲከፈት መጮህ ጀመረ፡፡ የእስር ቤቱን አስተዳደሮችና ፖሊስን መውቀስ፣ መስደብ ቀጠለ፡፡ ያን በግድ እንዲለብስ የተደረገውን ዩኒፎርም አውልቆ ሜዳ ላይ አቃጠለ፡፡

ይህ ብሶት እዛው እስር ቤት ብቻ የሚቀር አይደለም፡፡ በቴሊቪዥን የሚታየው ኢቲቪ ብቻ ነው፡፡ በየትኛውም ወንጀል የገባ ይሁን፣ እስረኛ ሌላ አማራጭ ስለሌለው በሚዲያው ይማረራል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢቲቪን ያገኘ ሲመስለው ‹‹እሱን ውሸታም አውርድ!›› ብሎ ቴሌቪዥኑንም እሳት ውስጥ ከተተው፡፡ የትኋንና የቅማል መናሃሪያ የሆነውና ደቦቃ ላይ የሚተኛበትን ቆሻሻ ፍራሽ እሳት ውስጥ ጨመረ፡፡ ከዚህ በላይ ስሜታዊ የሆነ እስረኛ፣ ቤት እስከመለኮስ ደረሰ፡፡

እስረኛው የብሶቱን ማመፅ ሲጀምር፣ ወዲያውኑ ፖሊስ ከየ አቅጣጫው ወደ ጠባቦቹ ግቢዎች መትረየስ መተኮስ ጀመረ፡፡ የቂሊንጦ እስር ቤት አራት ማዕዘን ሆኖ ወደ ዞኑ የሚያስገባው በር ጠባብ ነው፡፡ ፖሊስ እነዚህ በሮች ትይዩ ሆኖ እስረኛው ወዳለበት ሜዳ እሩምታ ተኩሷል፡፡ በርካታ የጭስ ቦንቦች ተወርውረዋል፡፡  

ውስጥ እስረኛው ሲያቃጥላቸው ከነበሩት ቁሳቁሶች ጋር ሲዳመሩ እስር ቤቱ ስለጨለመ፣ እስረኛ ወደየት እንደሚሄድ እንኳ አያውቅም፡፡ በዚህ እሩምታ መካከል በርካቶች ተመትተዋል፡፡ በዚህ ሩምታ ምክንያት እስረኞቹ ተደግፈዋቸው የነበሩት የቤቱ ግድግዳዎች በጥይት ተበሳስተዋል፣ አግዳሚ ብረቶች በጥይት ተመትተዋል፡፡  

ይህ አሁንም በማስረጃነት ያለ ምልክት ነው፡፡ በርካቶች ቆስለው፣ እስረኞች ተደግፈዋቸው የነበሩት ግድግዳዎች አሁንም ድረስ ተበሳስተው እየታዩ የሞቱትን እስረኞች እሳት እንደበላቸው አድርገው አቅርበዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዞን ሁለት በቤተሰብ መጠየቂያው በኩል ለማምለጥ፣ እንዲሁም ሜዳ ላይ በሩምታ የተገደሉትን እስረኞች፣ እስረኛ ያቃጠላቸው ለማስመሰል በጥይት የደበደቡትን አስከሬን አንስተው እሳት ውስጥ መጨመራቸው ነው፡፡ እስረኞች በጥይት በመደብደባቸው ሜዳ ደም ፈሷል፡፡  

እስረኛውን ወደ ዝዋይና ከሽዋ ሮቢት ሲመለስ ደሙን ለመሸፈን ተብሎ ሜዳው አዲስ አፈር ለብሶ ነበር፡፡ ይሁንና መጋቢት 2009 ዓ/ም ላይ ዝናብ ሲዘንብና ይህ ጊዜያዊ አፈር ሲታጠብ፣ የፈሰሰው ደምና እሳት ላይ የተጣለው የሰው ልጅ ገመና የተጣበቀበት ሜዳ ተጋልጦ ነበር፡፡

የእስር ቤቱ አስተዳደሮች ጥፋታቸውን ለመሸፈን የሞቱትን ሰዎች እስረኛ እንደገደላቸው አድርገው ሲያወሩ ከርመዋል፡፡ እነ ሰጠኝ ሙ ተሻለ በቀለና ሌሎችም በቤተሰብ መጠየቂያው በኩል (ተቃጥለው ከተገኙበት ግቢ ውጭ) እንደተመቱ ከጎናቸው የነበሩት የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡

ሆኖም የእስር ቤቱን አስተዳደር ተጠያቂ ላለማድረግ ሲባል ከዚህ በፊት ከፖሊስ ጋር የማይስማሙ እስረኞችን ሸዋ ሮቢት ወስደው በመደብደብ በሀሰት ገድለናል ብለው እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል፡፡ መንግስት ያቋቋመው ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንኳ የተኩስ ሩምታ እንደነበር ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርቱ መግለፁ ሟቾቹ በጥይት እንደተገደሉ ማስተባበል እንደማይቻል ያሳየ ነው፡፡

ከቃጠሎው በኋላ እነዚህ የዞን ኃላፊዎች በቃጠሎው ሰበብ እስረኞችን ሲመረምሩ ለነበሩት ደህንነቶች የቃጠሎው ዋነኛ ምክንያት እነ ተክላይ እንደሆኑ በግልፅ ተናግረው ነበር፡፡ እስረኞቹ ‹‹ለዚህ ሁሉ የዳረጉን፣ ለበርካቶች መሞት ምክንያት የሆኑት እነ ተክላይ ናቸው፡፡›› ብለው ተናግረዋል፡፡ ከኮሚቴዎቹ መካከል አበበ አንዱ ነው፡፡ ዞን አንድ ውስጥ 18 በላይ የጪስ ቦንቦች ሲወረወሩ እሱም ታፍኖ ከሞት ነው የተረፈው፡፡ አበበ ለደህንነቶቹ ‹‹ተጠያቂው ማንም አይደለም፡፡ ከእስር ቤቱ አስተዳደሮች ውጭ ሊጠየቅ የሚገባው ሰው የለም፡፡  

ነግረናቸው ነበር፡፡ ለዚህ ሁሉ መከራ የዳረጉንን እነ ተክላይን ክሰሷቸውና እኔ የመጀመሪያው ምስክር እሆናለሁ፡፡ እኔኮ እነሱ ባመጡት ጦስ ሞቼ ነበር›› ብሎ በግልፅ ሲነግራቸው የእስር ቤቱን አመራሮች እንደሚያስሩ ቃል ገብተው ነበር፡፡ በእርግጥም የእስር ቤቱ አመራሮች የችግሩ መንስኤ እንደሆኑ ታምኗል፡፡ ግን አልታሰሩም፤ አልተከሰሱም፡፡ ቅጣቱ ከቂሊንጦ ወደ ዝዋይ ማዛወር ብቻ ነበር፡፡

የእስር ቤቱ አመራሮች እስረኛውን መሰረታዊ ፍላጎት ነፍገው፣ መሰረታዊ መብቱን ጥሰው፣ በምሬት እስር ቤቱ እንዲቃጠል ሲያደርጉ የተደበደቡትና የተከሰሱት ከማንም ጋር መገናኘት የማይቻልበት ጨለማ ቤት የነበሩት እነ ማስረሻ ሰጤ፣ አበበ ኡርጌሳ፤ በወቅቱ ቂሊንጦ ግቢ ውስጥ እንኳን ያልነበሩት የግፍ እስረኛው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ ለወራት ያህል ጨለማ ቤት፣ ከዛም ተፈርዶበት ዝዋይ የነበረው ፍቅረማርያም አስማማው፣ በቃጠሎው ወቅት ከቤታቸው ያልተነቃነቁት እነ አግባው ሰጠኝ፣ ከበደ ጨመዳ እና ሌሎችም ንፁሃን ናቸው፡፡  

እነዚህ ንፁሃን ያልነበሩበትን አድርገናል ብለው እንዲያምኑ፣ የእስር ቤቱ አስተዳደሮች ለፈፀሙት እነሱ እንዲቀጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪዎች ሸዋ ሮቢት ወስደው ጭካኔ ፈፅመውባቸዋል፡፡ ተሰቅለዋል፡፡ ተገርፈዋል፡፡ ተከሰዋል፡፡ ሸዋ ሮቢት የደረሰባቸውን በደል ፍርድ ቤት ሲናገሩ ታዳሚ አስነብተዋል፡፡

(የሰቆቃ ድምፆች መፅሐፍ ላይ የቀነጨብኩት ነው)

No comments