Latest

የመፃተኛው ኑዛዜ (በእውቀቱ ስዩም)

የመፃተኛው ኑዛዜ (በእውቀቱ ስዩም)
የመፃተኛው ኑዛዜ 

በእውቀቱ ስዩም


ካገር ጫፍ እስከ ጫፍ ፣ በጥላህ ከልለህ
"ተራራው የኔ ነው" ፣ ለምን ትለኛለህ?
"ወንዙ ድርሻዬ ነው" ፣ ለምን ትለኛለህ?
እንኳንስ መሬቱ ፣ አንተም ያ'ንተ አይደለህ!!!

እኔ መፃተኛ ፣አንተ "ኗሪ ነኝ" ባይ
እኔ እግሬን ስከተል ፣ ርስትህን ስታይ
ስቀርብህ ገፋኸኝ ፣ ስትገፋኝ ቦታ አጣሁ
ድንኳን ብትተክል፤ ነፋስ ሆኜ መጣሁ፡፡

ያ'ባትህ ያ'ባቴ
ጠበኛ ስማቸው
ጠበኛ ህልማቸው
በህይወት ተጣሉ ፤ ታረቁ ባፅማቸው
ባ'ፈር ተቃቃሩ ፣ አፈሩ አስማማቸው
በዙሪያቸው በቅሎ ፣ ከቧቸው ሞት ደኑ
መተቃቀፍ መርጠው ፣ ማማና ወይን ሆኑ፡፡

"ይችላል" ይሉሀል ፣ ፍልሚያ ማዘጋጀት
ያ'ባት አጥንት ወስዶ ፣ ስሎ ጦር ማበጀት።

አንተው ጦር ወርውረህ ፣ አንተው ቀድመህ ወደቅክ
አካሌ ደረቴ ፣ መሆንህን መች አወቅክ?!

No comments