Latest

በኢትዮጵያዊነት ልክፍት የተነደፈ ኢትዮጵያዊ!-ታማኝ በየነ!



በኢትዮጵያዊነት ልክፍት የተነደፈ ኢትዮጵያዊ!-ታማኝ በየነ!

ታማኝ በየነ ማን ነው?
ታማኝ በየነ ከታዋቂ የመድረክ አስተዋዋቂዎች አንዱ ነው። ታማኝ በየነ ጐንደር ውስጥ አይከል ከተማ በ1955 ዓ.ም. ተወለደ። ታማኝ ከልጅነቱ አንስቶ በትያትርና በሙዚቃ ክበባት ውስጥ በድምፃዊነት ያገለግል ነበር፡፡ በ1969 ዓ.ም. ጋይንት አውራጃ ውስጥ በግል ጥረቱ ባቋቋመው የህፃናት የኪነት ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስተዋዋቂነት ሚና በመውሰድ ተጫወተ።

በአካባቢው የነበሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች የወጣቱን የአስተዋዋቂነት ችሎታ በመገንዘብ በቀዳሚነት የአውራጃው እንደገናም የክፍለ ሀገሩ የኪነት ቡድን አስተዋዋቂ ሆኖ እንዲሰራ ዕድሉን ሰጡት፡፡

እሱም ከቀን ወደ ቀን በሙያው እየተካነ የትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያስደስት ወዝና ለዛ ያለው ዝግጅት ማቅረብ ጀመረ። ታማኝ በ1974 ዓ.ም. ለቀይ ኮከብ ዘመቻ ከብሄራዊ ቲያትር ተጨዋቾች ጋር ወደ አሥመራ በመሄድ በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ ከያኒያን ጋር ከመተዋወቁም በላይ የተዋጣለት ዝግጅት ለማቅረብ በቅቷል።

ሚያዚያ 30 ቀን 1975 ዓ.ም. ለትንሣኤ በዓል ዋዜማ በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ


“ወጥ እንኳን አይጣፍጥ በርበሬ ካነሰው፣
ክትፎም አይጣፍጥም ሚጥሚጣ ካነሰው፣
እንዴት ለዚህ ኪነት ጭብጨባ ይነሰው!?”


እያለ በብሄራዊ ቲያትር ቤት የነበረውን ተመልካች ሲያስጨበጭብ ፕሮግራሙን በቀጥታ በቴሌቪዥን ይተላለፍ ስለነበር በዚህ ቀን ከመላው የኢትዮጵያ ተመልካች ጋር የመተዋወቅ እድል አጋጠመው፡፡ ታማኝ መጋረጃው ተከፍቶ የማስተዋወቅ ሥራውን የሚጀምረው "ሠላምታ" በሚለው ቃል ውስጥ የሚገኙትን ፊደሎች ትርጓሜ አንድ በአንድ በመተንተን ነው፡፡

“ሠ”- ሰውን አከብራ ለሁ፣
“ላ“ - ላዝናና እጥራለሁ፣
"ም" - ምንጊዜም እደክማለሁ፣
“ታ” - ታማኝ እባላለሁ፡፡

እያለ ራሱን በመግለፅ ወደ ዋናው ጉዳይ ይገባል። አንዳንዶቹ የታማኝ በየነ ቀልዶች ፖለቲካዊ ይዘት አላቸው ይላሉ። የደርግ መንግሥት ወድቆ የኢህአዴግ መንግሥት አገሪቱን ከመቆጣጠሩ ትንሽ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተዘጋጀው የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ሻዕቢያንና ወያኔን የሚያበሳጩ ቀልዶችን ቀልዶ ነበር።  

ቀልዱን ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነው ኤርትራና ኢትዮጵያ ውስጥ ይተላለፉ የነበሩት የሻቢያና የወያኔ ተዋጊዎች የተጋነኑ የጦር ሜዳ የድል ዜናዎች እንደሆኑ የሚናገሩ አሉ። ታማኝ ከዚህ በመነሳት “የሻዕቢያና የወያኔ ሬዲዮኖች በየቀኑ አምስት ሺ ገድልን፣ አምስት ሺ አቆሰልን፣ አሥር ሺ ማረክን ይላሉ፡፡

እነሱ የገደሉት የእኛ ሠራዊት በአጠቃላይ ሲደመር አሁን ካለው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በልጦ ከሚመጣው ትውልድ 5 000 000 ህዝብ ተበድረን ሞተናል” ሲል ኃይለ ቃል የታከለበት ቀልድ አዘል ትችት ሰንዝሯል፡፡ የሻዕቢያ ደጋፊዎች ይሁኑ የወያኔ በውል አልታወቀም እንጂ ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ችግር ሊፈጥሩበት ሞክረው እንደነበር ይነገራል፡፡  

ታማኝ በየነ በመድረክ አስተዋዋቂነት የአቀራረብ ስልቱ ትረካን፣ ቃሪ-ምልልስንና ዜማን ያካትታል፡፡ ታማኝ በየነ አንድነትን በመስበኩ እና ፖለቲካዊ ለዉጥ እንዲመጣ ድምጹን በማሰማቱ ከ22 አመታት በፊት ወደ አሜሪካ በስደት ለማቅናት ተገዷል፡፡ 

ታማኝ በየን በአሜሪካ ቆይታዉ የበጎ ስራዎችን በማከናወን፣ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን እና በኢትዮጵያ ለዉጥ አንዲመጣ በመታገል ይታወቃል፡፡ ህዝቡም ፖለቲካዊ ንቃቱ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ካደረጉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኢትዮጵያዊያን መካከል ግንባር ቀደም ነዉ፡፡ 

ታማኝ ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ ሀገሩ ገብቷል፡፡ "ካገሬ የወጣሁት ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው፤ ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም" በማለት ታማኝ በየነ ሀገሩ ሲገባ የተሰማዉን ተናግሯል፡፡

አዘጋጆች፡- ዮሀንስ ልጃለም እና ቢኒያም መስፍን

No comments