Latest

ሌላ ግሩም መረጃ ስለ አዲስ አበባ! ብሩክ አበጋዝ



ሌላ ግሩም መረጃ ስለ አዲስ አበባ

አዲስ አበባ ድሮ ገና በሩቁ ድሮ እንደ ዋሻ ሚካዔል ዓይነቱን ፍልፍል ቤተክርስቲያን በጉያዋ ታቅፋ በረራ እየተባለች በምትጠራ ጊዜ እነ ዓፄ ልብነ ድንግል (ወናግ ሰገድ) የግዛታቸው ማዕከል አድርገዋት ነበር።

በጣም ቅርብ ድሮ ከምኒልክ ዳግማዊ በፊት ደግሞ እዚህም አዚያም አልፎ አልፎ ቁጭ ቁጭ ያሉ ደሳሳ ጎጆወች ነበሩ። ምኒልክ ዳግማዊ እና እቴጌ ጣይቱ ዘእምነገደ ወረሴህ የዛሬዋ አዲስ አበባ ላይ ቀልባቸው ተተከለ፣ እንደ ተተከለም ቀረ። የመንግስት ማዕከልም ሆነች ከተማነቷም እለት እለት አደገ፣ ተስፈነጠረች፣ ለኑሮ ተመቸች [በእርግጥ ለእኔ አትመቸኝም፤ ሁልጊዜም የሚናፍቀኝ ቀዬዬ ነው፤ ሌላው ቢቀር ህልም ሳይ እንኳን ሁልጊዜም የህልሙ መተወኛ ቦታ ያው ቀዬዬ ነው፤ ታዲያ ያስገርመኝ እና ህልሜ የሚተወንበት ቦታ አዲስ አበባ ወይም ጎንደር መቼ ይሆን? እላለሁ]።



እንግዲህ ዛሬ አዲስ አበባን ያም የእኔ፣ ያም የእኔ የሚላት ከተማ የሆነችው ከመሬቱ በላይ ብዙ ነገር ስላረፈባት፣ ብዙ ሀብት፣ ጉልበት እና እውቀት ስለፈሰሰባት ነው። በባለቤትነት ደረጃ አዲስ አበባ ንብረትነቷ ከመሬቷ በላይ ንብረት ላፈራባት ማህበረሰብ ይሆናል፤ ዋናው ጉዳይ መሬቱ ሳይሆን ከመሬቱ በላይ ያለው ሀብት እና ንብረት እንዲሁም ከከተማነቱ ጋር አብሮ የተፈጠረው ነገር ነው። መሬትማ ቢሆን ስንት ጠፍ መሬት ሞልቶ አዲስ አበባ የምታወዛግብ አትሆንም ነበር።




ወደ ደብረ ብርሃን መስመር ቢኬድ እስከ ጣርማ በር ድረስ ለከተማነት የሚያገለግል የተዘረጋ መሬት ሞልቷል፣ ወደ ፍቼም እንደዚያው፣ በሰበታ በኩልም እንዲሁ፣ በሁሉም አቅጣጫ ተመሳሳይ ነው። አዲስ አበባን በተመለከተ ያለው መናቆር መሰረቱ የመብት መጣስ፣ የመሬት ወረራ፣ የባህል መጥፋት፣ የቦታ ስም መቀየር ወዘተ አይመስለኝም። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሽፋን ናቸው፤ ከእነዚህ ሮሮወች ጀርባ ግን አንዳንዶች ሊናገሩት የማይፈልጉት የጥላቻ አመለካከት፣ የፀረ አንድነት አመለካከት አለ፣ አዲስአበባ ጥቅም ያላት አገር ስለሆነች ያለ ልፋት መጠቀም የመፈለግ ዝንባሌም አለ።
.
አዲስ አበባን የእኔ ናት የሚል አካል፣ በአዲስ አበባ ውስጥ የእኔ ነው የሚለው ንብረት እና ሀብት እስከ ሌለው ድረስ አዲስ አበባ ላይ ያለው መብት እንደ ዜጋ ከመንግስት ተቋማት የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት፣ ተቀጥሮ መስራት፣ በህግ አግባብ ሀብትና ንብረት ማፍራት ወዘተ ብቻ ነው።

አዲስ አበባ የአዲስ አበቤወች ብቻ ናት፤ ማንም ሰው የቃላት ድሪቶ እየደረተ እያሳማረ አጓጉል የፖለቲካ ወሬ ቢያወራ አዲስ አበባ ከነዋሪወቿ ውጭ ሌላ ባለቤት ሊኖራት ይችላል ቢለኝ እስቅበታለሁ። የአዲስ አበባ ባለቤትነትን ለማግኘት የሚፈልግ ግለሰብ ሌላውን ገንዘብ የሚፈልግ ባለ ህንጻ ብሩን አውጥቶ ሆጭ አድርጎ በመግዛት ማሳካት ይችላል።
.
ኦነግ እና ትህነግ/ሕወሓት መክረው ያወጡትና የአማራውን አከርካሪ የሰበሩበት ህገመንግስት በፈጠረላቸው ቀዳዳ በመጠቀም እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሞ ማህበረሰብ ልዩ ጥቅም በሚል ሰበብ የሚነዛው ፖለቲካ እንዲሁም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት ዲስኩር እጅ እጅ ከማለቱም በላይ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደረግ ትንኮሳ ነው።

አዲስ አበባ ከምኒልክ በፊት ስሟ ይሄ ነበር እንዲህ የሚባል የኦሮሞ ጎሳ ይኖርባት ነበር እያሉ ፖለቲካና ታሪክ አጣምረው የሚያወሩ ሰወች 350 ዓመት ወደኋላ ሄደው እዚያው ቦታ ላይ ማን እንደሚኖር ቢነግሩን አዲስአበባም ማን ትባል እንደነበር ቢያሳውቁን አብዝተን እንመርቃቸው ነበር።

ከልዩ ጥቅም እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሞ ጋር በተያያዘ እኔ ለአዲስ አበባ ዙሪያ ሰው የምከራከርለት ነገር ቢኖር መሬቱን የመሸጥ የመለወጥ ሙሉ መብት በእጁ ይኑረው እና በሰፊው ይጠቀም ነው፤ በእርግጥ ይኼ መብት ለሁሉም ኢትዮጵያዊይ ሊኖር ይገባዋል የሚል ሀሳብ አለኝ።
.
ይኸውም የመሬቱን ጥቅም በአግባቡ ማግኘት አለበት፤ መንግስት በጭልፋ እየቸበቸበ ለባለ መሬቱ በማንኪያ መስጠቱን ማቆም አለበት፤ የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሞም መሬቱን በውድ ዋጋ በመሸጥ የአዲስአበባን ትሩፋት ይቋደስ። በዚህ መልኩ አርሶ አደሩ ሲፈልግ መሬቱን ይሽጥ ከፈለገም ደግሞ ከብቱን ያርባበት አሊያም ስንዴ ይዝራበት የሚያዋጣውን ያድርግ። መንግስት አርሶ አደሩ እንዳይጭበረበር ከጎኑ በመሆን ይጠብቀው፣ ገንዘቡንም ሁነኛ ቦታ ላይ እንዲያውለው ድጋፍ እና ምክር ይስጠው።

ለአዲስ አበባ ከተማ ውሀ የሚሄደው ከኦሮሚያ ነውና ልዩ ጥቅም ይገባል የሚሉት ሰወች የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ የሚመጣው ከአባይ እና ከኦሞ ወንዝ ግድቦች ነውና የኦሞ ሰወችና የግሼ አባይ ሰወች ከአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ብለው በነካ አፋቸው መጮህ አለባቸው።

No comments