Latest

ወንጀልን ለማቆንጀት፣ ሰበብና ማመካኛ መደርደር ይብቃ! (ዮሃንስ ሰ)

ወንጀልን ለማቆንጀት፣ ሰበብና ማመካኛ መደርደር ይብቃ!
  • አለዚያ፣ ህግና ስርዓት፣ ለጉልበት ወይ ለትርምስ ተሸንፎ ማጣፊያው ያጥረናል።
  • “የሕዝቡ ጥያቄ ስላልተደመጠ ነው” ብሎ ያሳብባል አንዱ ምሁር። (ጥፋትና ጭካኔን የሚያስውብተዓምረኛ እውቀት የያዘይመስል።)
  • “መንግስት ፈጣን ምላሽ ስላልሰጠ ነው” ይላል አንደኛው ፀሐፊ ። (ክፋትንና ምቀኝነትን የሚያቆነጅ ልዩ አስማት ያገኘ ይመስል።)
  • “የመወያየትና የመነጋገር እድል ስለሌለ ነው” ይላል አንደኛው ፖለቲከኛ (በዚህች ንግግሩ፣ ወንጀልን እንደፍትህ የሚቆጠርለት ይመስል።)
በአሉባልታ ጭፍን ጥላቻንና ዛቻን የሚዘሩ፣... የሰውን ንብረት የሚዘርፉና የሚያቃጥሉ፣... ሰውን ከመኖሪያው የሚያሳድዱና የሚገድሉ ወንጀለኞችን ለማቆንጀት፣ እንደበቀቀን ነጋ ጠባ፣ ማሳበቢያ ቃላትን ማነብነብ፣ ማመካኛ አባባሎችን ሌት ተቀን መደጋገም ይብቃ!

የስንቱ ሕይወት ጠፋ? የስንቱ አካል ጎደለ? ሚሊዮኖች ተፈናቅለው፣ ንብረታቸው ተዘርፎና ወድሞ፣ ኑሯቸው ሲናጋ፣ እለት በእለት እያየንም እንኳ፣ ትንሽ ሰከን ብለን ማሰብ አንጀምርም? አሁንም ሰበብ አስባብ መደርደር?
መነሻው፣ ምንም ይሁን ምን፣ ጭፍን እምነትም ይሁን ሌጣ አላዋቂነት፣... ፖለቲካን እንደቁማር ጨዋታ የማየት ሞኝነትም ይሁን የአእምሮ ድንዛዜ፣ የዘረኝነት በሽታም ይሁን አልያም ሌላ መነሻም ይኑረው፣... የወንጀል ድርጊትንና ጥፋትን ለማቆንጀት፣ እንደ ልማዳዊ የእለት ስራ፣ ልማዳዊ ሰበቦችና ማመካኛዎች፣ በበቀቀን ደመነፍስ እየተነበነቡ፣ በሰላም መቀጠል አይቻልም - ወደባሰ ጥፋት ነው የሚያወርዱን።
“ይሄኛው ጥያቄ ተገቢ ነው። ያኛው አቤቱታ ትክክለኛ ነው። ተሰሚነት ማግኘት አለባቸው። መንግስት ተገቢ ጥያቄዎችን ካላደመጠ፣ ባለስልጣን ትክክለኛ አቤቱታዎችን ካልሰማ፣ ትልቅ ጥፋት ነው። በዚያ ላይ፣ ለአጥፊ ወንጀለኞች መንገድ ይከፍታል” ብሎ ማብራራት አንድ ጉዳይ ነው። 

እንዲሁ የምበደፈናው፣ “የህዝብ ጥያቄ” እያሉ ማነብነብ ግን፣ ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም። በዚያ ላይ፣ ጥቃት የሚፈፅሙ አጥፊ ወንጀለኞችንና፣ ጥቃት የሚደርስባቸው ብዙ ሚሊዮን ሰላማዊ ነዋሪዎችን በጅምላ፣ “የሕዝብ ጥያቄ” በሚል ድፍን አባባል ማቀላቀል፣ የንፁህ አእምሮ ምልክት አይደለም።
የመንግስትና የባለስልጣን ጥፋት፣ የመንግስትና የባለስልጣን እዳ ነው - በሌላ ላይ በመላከክና በማሳበብ ለማድበስበስ መሞከር፣ አምባገነንነትን መጋበዝና ማበረታታት ይሆናል። የመንደር ጋጠወጥና ወንጀለኛ ጥፋትም፣ የወንጀለኞቹ እዳ መሆን አለበት - በሌላ ላይ ለማላከክና ለማሳበብ መሯሯጥ፣ ተጨማሪ ወንጀልን እንደመጥራት ነው። 

ወንጀለኛውንና ሰላማዊውን ነዋሪ ለይቶ ላለመመዘን፣... “መንግስት የህዝብን ጥያቄ ስለማያደምጥ ነው” ብሎ ማሳበብና ማመካኘት፣... ወንጀለኞችን በንግግር የማስዋብ፣ ለተጨማሪ ጥፋት የመጋበዝና የማበረታታት ድጋፍ ይሆናል። ነውርነቱም እዚህ ላይ ነው። ታዲያ ነውርነቱ ለምን ተረሳ?
የአመፅና የዝርፊያ፣ የውድመትና የግድያ ጥፋት በተከሰተ ቁጥር፣ “የሕዝቡ ጥያቄ ስላልተደመጠ ነው፤ አቤቱታውን የሚሰማለት ስላጣ ነው...” እያለ ሰበብ ለመጎልጎል የሚሽቀዳደም ምሁር ሞልቷል። ለምን? ጥፋትንና ጭካኔን ለማስዋብ መሞከር፣ ክፉ ነውር መሆኑ ተረስቷል። በተቃራኒው፣ ተዓምረኛ ድግምት ያገኘ ይመስል፣ ሰበቦችን እልፍ ጊዜ ደጋግሞ ማነብነብ፣ እንደአዋቂ የሚያስቆጥር እየሆነ ነው።
ግን፣ የማሳበብና የማመካኘት ሩጫው፣ በአገር እና በኑሮ ላይ የሚኖረው ትርጉም ምንድነው? “መንግስት ጥያቄያችሁን ስላላደመጠላችሁ፣ የናንተን ጥያቄ የሚሰማ ባለስልጣን ስላጣችሁ... ማንም ጋጠወጥ ዱርዬ፣ መውጪያ መግቢያ ቢያሳጣችሁ፣ ማንም ክፉ ወንጀለኛ ቢዳምጣችሁ፣ ቅር አይበላችሁ። ይሄ፣... ነፃነትን የሚያሳጣችሁ የጥፋት ወንጀል ሳይሆን፣ ለነፃነት የሚከፈል የመስዋዕትነት ትግል ስለሆነ፣ እንደ ክፉ አትቁጠሩት” እንደማለት ነው - የማሳበብ ሩጫው ትርጉም።
ሌላኛው ጸሐፊም በፊናው ተነስቶ ተጨማሪ ሰበብና ማመካኛ ያራግባል - “መንግስት ፈጣን ምላሽ ስላልሰጠ ነው” ይላል - ክፋትንና ምቀኝነትን የሚያቆነጅ አስማተኛ የሆነ ይመስል። 

ግን፣ የዚህ አይነት አባባልስ፣ ትርጉሙ ምንድነው? “መንግስት ለዜጎች ፈጣን ምላሽ ካልሰጠ፣ የየመንደሩ ወንጀለኛ፣ እንዳሻው ሚሊዮን ዜጎችን የማጥቃት፣ ንብረታቸውን የመዝረፍና የማቃጠል መብት አለው” እንደማለት ነው። የመንግስት ባለስልጣን ነዋሪዎችን ከጎዳ፣ ወንጀለኞችም እንዲሁ ነዋሪዎችን የማጥቃት መብት ይኖራቸዋል?
“የመወያየትና የመነጋገር እድል ስላልነበረ ነው” ይላል አንደኛው ፖለቲከኛ - በዚህችው ንግግሩ፣ ክፋትን እንደቅድስና፣ ወንጀልን እንደፍትህ የሚቆጠርለት ይመስል። በሃይማኖት፣ በመንደር፣ ወይም በዘር የተቧደኑ ወንጀለኞች፣ ሰውን ሲያሳድዱና ሲገድሉ... ድርጊታቸው፣ ክፉ የወንጀል ድርጊት ሳይሆን፣ በአንዳች ተዓምር ልዩ መብት ይሆናል? ውይይትና ንግግር የለም በሚል ሰበብ!
በቅርቡ፣ የሕይወት፣ የአካል፣ የንብረት ውድመትን ያስከተለ፣... ሃምሳ ሺ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉበት ጥፋትና ወንጀል የተፈጠረ ጊዜስ ምን አይነት ማሳበቢያ ሰማን? “ቅዳሜ የሚጀመር የስራ ዘመቻ፣ በዋዜማው አርብ እለት እንደተጀመረ የሚያስመስል የተሳሳተ ዜና በሬድዮ ስለተላለፈ ነው” የሚል ማመካኛ!
ሌላ ጊዜስ፣... “የመንግስት ባለስልጣን የተጣራ መረጃ ስላልሰጠ፣... የወንጀል የምርመራ ውጤት በፍጥነት ስላልተገለፀ ነው ችግር የሚፈጠረው”... የሚል አስተያየት ይቀርባል። አንዱ ጋዜጠኛ በሬድዮ የተሳሳተ መረጃ ስለተናገረ፣ አንዱ ባለስልጣን የተጣራ መረጃ ስላልሰጠ፣... በቃ፣ በአሉቧልታ ዘመቻ አገርን ከማናወጥና የሰውን ንብረት ከማቃጠል በስተቀር ሌላ ምንም አማራጭ የለኝም? 

በቃ፣ ያኔ፣ ወንጀለኞች፣ ያሻቸውን ቢፈፅሙ፣ አይፈረድባቸውም? “የወንጀል ምርመራ ውጤት በፍጥነት አልተገለፀልኝም። ስለዚህ፣ እጥፍ ድርብ ጥፋት ባዛምት፣ መብቴ ነው! የሰፋ የከፋ እልፍ ወንጀል ብፈፅም፣ የሕዝብ ጥያቄ ነው።” የሚሉ ጋጠወጦች አይፈረድባቸውም?
እንዲህ አይነቱን ትርጉም ያዘለ ማሳበቢያና ማመካኛ፣ በጣም ከመለመዱ የተነሳ፣ ስህተትነቱና ነውረኛነቱ ሁሉ ተረስቷል። አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ፣... እዚህና እዚያ ብቻ፣... በዚህና በዚያ ጉዳይ ብቻ፣... በአጋጣሚ የተከሰተ ስህተት አይደለም።
በየከተማውና በየክልሉ፣ በየአደባባዩና በየመንገዱ፣ በየሰፈሩና በየገበያው... የየመንደሩ ጥቂት ባለጌ ጋጠወጦችና ጥቂት ክብረቢስ ወንጀለኞች በየሰፈሩ ሲነግሡ በተደጋጋሚ እልፍ ጊዜ እያየንም እንኳ፣... አይናችንን ጨፍነን እውነታውን ለማድበስበስና ራሳችንን ለማታለል የመሯሯጥ አመል፣ ማመካኛ ቃላትን እንደበቀቀን ለመደጋገም የመሽቀዳደም አባዜ፣... ከመቀነስ ይልቅ፣ ይባስ እየተዘወተረ ነው።  

በዚያው ልክ፣... ያልነካቸውን ሰው የሚዳፈሩና ንብረት የሚዘርፉ፣ ያልደረሰባቸውን ሰው የሚያሳድዱና የሚገድሉ፣ ጥቂት የየመንደሩ ጋጠወጦችና የየሰፈሩ ወንጀለኞችም፣ ይበልጥ እየተመቻቸው ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊስ? ሰው አክባሪነት ያልራቀው አብዛኛው ጨዋ ዜጋ፣ ህግ አክባሪነትን ያልረሳ አብዛኛው ሰላማዊ ነዋሪ፣... ለወራት ከዚያም ለአመታት፣.. ያለፋታ በየሳምንቱና በየእለቱ፣... ለከፋ ስጋት፣ ለጥቃትና ለጉዳት ሲዳረግ እየተመለከትንም እንኳ፣... አሁንም ድረስ፣ ሰበባሰበብና ማመካኛ መስማታችን አልቀረም።  

በየመንደሩ ጥቂት ጋጠወጦችና ወንጀለኞች እየነገሡ፣ አብዛኛው ጨዋ ሰውና ህግ አክባሪ ዜጋ ደግሞ ያለፋታ ለጥቃት እየተጋለጠም ቢሆንእንኳ፣... ይህንን ግልፅ እውነታ ለመሸፋፈንና ለማድበስበስ፣... እልፍ ሰበብ የመፈልፈል ልማድን የሙጢኝ መያዝ ምን ይባላል?

 እያዩ የማለቅ አሳዛኝ ይጥፋት ጉዞ ይሉሃል ይሄ ነው። ግን ምን ይሄ ብቻ! ነባሮቹን የማሳበቢያ አባባሎች መላልሰው እያመሰኩ መደጋግመው የማኘክ ልማድ፣... ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከተ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም።

No comments