Latest

ሀገራችን ከገባችበት አዘቅት እንድትወጣ ከሚያግዙ ነጥቦች ጥቂቶቹን እነሆ! (ምሕረት ዘገዬ)

ሀገራችን ከገባችበት አዘቅት እንድትወጣ ከሚያግዙ ነጥቦች ጥቂቶቹን እነሆ! (ምሕረት ዘገዬ)

ከአሁኑ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ጋር ሲወዳደሩ የደርግና የቀ.ኃ.ሥላሤ መንግሥታት በአጋጣሚ ካልሆነ እንዳሁኑ ዘመን በመርህ ደረጃ በጎሣና በነገድ የተዋቀሩ እንዳልነበሩ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ 

ስለዚህ ከነዚህ ያለፉ መንግሥታት በሕይወት ያሉ የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤቶችን አሁን ከያሉበት ጋብዞ ለውጡን እንዲቀላቀሉና እንዲሣተፉ ቢደረግ ሀገር ትጠቀማለች፡፡ ሙያቸውንና ሀገር ወዳድነታቸውን እያጣሩ በአግባቡ ቢገለገሉበት ሀገራችን አንድ እርምጃ ወደፊት ትራመዳለች – በተለይ በመከላከያና በደኅንነት ረገድ የማይናቅ ሀብት እንዳለን መገንዘብ አለብን፡፡

አሻጥር ቢፈጸምባቸው ሕዝብንና ሀገርን የሚጎዱ የሥራ ኃላፊነቶችና የሥራ ክፍሎች በአፋጣኝ ከወያኔዎች ቁጥጥር ወጥተው ወደ ጤናማ ሰዎች እጅ ይግቡ፡፡ የለውጡ ኃይል ይሉኝታ ገደብ ይኑረው፡፡ ለምሣሌ 
  • ኢንተርኔት አሁንም ይቆራረጣል፤ ይዘጋል፤ ከዘላኖቹ ሶማሌዎች እንኳን የሚቀራረብ አገልግሎት አናገኝም፡፡ 
  • መብራት ኃይል ይቆራረጣል፤ ይጠፋል፤ ከሁሉም ሀገሮች ያነሰ አገልግሎት የምናገኝ ሳንሆን አንቀርም፡፡ 
  • ሕዝብን ማገልገል የሚገባው ሲቪል ሰርቪስ በሕዝብ ላይ የሚንጠባረርና በጉቦ የተነከረ እንጂ የሙያ ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡  
ይህ አካሄድ በአስቸኳይ መለወጥ አለበት፡፡ ሕዝብ እንደባርያ መቆጠሩ ያብቃ፡፡ ሕዝብ ደሞዝ ከፋይ ነው፤ ሕዝብ የሁሉም ነገሮች ምንጭ ነው፡፡ ሕዝብን መናቅና ማንኳሰስ የኋላ ኋላ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል እያየን ነው፡፡

ጦሩንና ደኅንነቱን ከዘረኝነት አረንቋ ማውጣትና ሁሉንም ዜጎች እኩል የሚያገለግል ሀገርና ሕዝብ ወዳድ የሆነ ተቋም መገንባት፡፡ አሁን ያለው ጦርና የፀጥታ ኃይል የአንድ ጎሠኛ ቡድን አገልጋይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የሀገራዊ ዋይታና ልቅሶ መንስኤም ይሄው የአንድ ጎሣ የበላይነት ያመጣው አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ በደል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሸውራራ አካሄድ በቶሎ መታረም አለበት፡፡

የለውጡ ኃይል ከዘረኞች በሚሰነዘርበት ጥቃት ሳቢያ ጉዳት እንዳይደርስበት ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ሰውን ማመን በመሠረቱ መልካም ቢሆንም የማይቀለበስ ጉዳት ደርሶ ሕዝብ ተስፋ እንዳይቆርጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ 

በተለይም ከሰኔ 16/2010 የቦምብ ፍንዳታና ከኢንጂኔር ስመኘው ግድያ ብዙ መማር ይገባል፡፡ የሀገራችን ጠላት ይህን ለውጥ ሳያዳፍን ዕንቅልፍ የማይወስደው መሆኑን ከዘነጋን የራሳችንን መቃብር ከሚቆፍሩ ወገኖች ጋር እንደመተባበር ነው፡፡

የለውጡን ተቃዋሚዎችና ታሪካዊ የሕዝብ ጠላቶች ከመጠን ባለፈ እሹሩሩ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ትግስት ድንበር ካልተበጀለት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የፍርሀትንና የትግስትን ወሰን እንዲያውቁ ካልተደረገ የሚከሰተው ጥፋት ከባድ ይሆናል፡፡

የኦሮሞና የአማራ ሥሙር ግንኙነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ጠላትን እንደመብረቅ እየፈረካከሰ የሚገኘው ይህ ግንኙነት ነው፡፡ የጠላትን ሸር መረዳትና በቶሎ መንቃት ከተጨማሪ ዕልቂትና መከፋፈል ያድናል፡፡ ስለዚህ ‹የአማራ መንግሥት‹ ለኦሮሞ አክቲቪስቶችና ታዋቂ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሰዎች፣ ‹የኦሮሞ መንግሥት› ለአማራ አክቲቪስቶችና ታዋቂ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሰዎች ሽልማት (ሞራላዊም ቁሣዊም) ቢሰጥ የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ይበልጥ ያጠብቀዋል፡፡  

ተላላኪዎችንም ያሣፍራል፡፡ ይህ ነገር በደምብ ይታሰብበት፡፡ የኦሮሞ ሀብታሞች ለኦሮሞ አክቲቪስቶች፣ የአማራ ሀብታሞች ለአማራ አክቲቪሰቶች … መሸለሙ በራሱ ክፋት ባይኖረውም የሽልማት አሰጣጡ ሰፋ ያለ አድማስ ቢኖረው ጥሩ ነው፡፡ በአንዲት ትንሽ ሀገር ውስጥ በጎሣና በዘውግ እየተሳሳቡ ልዩ ቀረቤታንና መሸላለምን መፍጠር ጠላት በቀደደው ቦይ መፍሰስ ነው፡፡

የሃይማኖት አባቶች ፍቅርን እንዲሰብኩ ይሁን፡፡ ጥላቻንና ክፍፍልን ከሚያራምድ ንግግርም እንዲቆጠቡ በግልጽ ይነገራቸው፡፡ በሃይማኖትና በዘር መወዛገብ ለጠላቶች ምቹ የመራቢያና የመስፋፊያ መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም አባቶች በሚለያዩዋቸው ላይ ሳይሆን አንድ በሚደርጓቸው ላይ ያነጣጥሩ፡፡ ያኔ መንጋውም በፍቅርና ውዴታ እየተቆራኘ ይከተላቸዋል፡፡

ፀረ-ለውጥ ኃይሉ ያሰማራቸው የአማራና የኦሮሞ ሆዳሞች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰድ፡፡ በነፈሰ የሚነፍሱ የሁለቱንም ዘውጎች እበላ ባዮች እንዝመትባቸው፡፡ በተጨማሪም ቋንቋ እየተማሩና እየለመዱ ሁለቱን ሕዝቦች ለማጣላት በየሥፍራው የሚሰማሩ የጠላት ተላላኪዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ተገቢ ፍርድ እንዲያገኙ ይደረግ፡፡ አለበለዚያ ለውጡ ግቡን አይመታም፡፡

የጦሩና የፀጥታው ክፍል አመራር ከሕወሓት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣት አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው ዘረኝነትን በዘረኝነት ለመተካት ሳይሆን ለውጡን ከሕወሓት ቅልበሳ ለመታደግ ብቻ መሆኑ ይታወቅ፡፡ በየእሥር ቤቱ አሁን ድረስ የሚሰቃዩ ዜጎች መኖራቸው ይታወቃልና እንዲለቀቁ ጥረት ይደረግ፡፡  

ጥቆማዎችን ከሕዝብ በመቀበል በየግለሰቦች ቤት ሣይቀር የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ ይሁን፡፡ በተለይ ትግራይ ውስጥ ከመሀል አገር እየተወሰዱ በየዋሻው የተጣሉና ለማያባራ ስቃይ የተዳረጉ ዜጎች እንዲፈቱ ጥረት ይደረግ፡፡
የእሥር ቤቶች ኃላፊዎችና ገራፊዎች አሁኑኑ ይነሱ፡፡ 

ዜጎች በሕወሓት ገራፊዎችና ማይም “መርማሪዎች” መሰቃየት የለባቸውም፡፡ ይህን የወንጀል ምርመራ ተግባር ጤነኛ ሰዎች እንጂ በጥላቻ የሰከሩ ጎሠኞች ሊያከናውኑ አይገባም፡፡ ወንዶችን ሲያኮላሹ፣ በወፌላላ ሲያሰቃዩ፣ ወንድን በወንድና ሴትን በሴት ሲያስደፍሩ፣ በጨለማ ቤት ሲዘጉ፣ ጥፍርን በጉጠት ሲነቅሉ፣ ኮዳን በብልት ሲያንጠለጥሉ፣ በማይድን በሽታ ሰዎችን ሲበክሉ፣ በፈላ ዘይት ሲጠብሱ፣ በርሀብ ሲያሰቃዩ፣ በዘረኝነት ስድብ ሞራልን ሲሰብሩ….  

የነበሩ ዘረኛ የእሥር ቤት ካቦዎችና ገራፊ-አስገራፊዎች ፍርድ ቤት ቀርበው የሥራቸውን ሊያገኙ ይገባል፡፡ የፍትህን ዐይን ሲያፈሱ የነበሩ ክፉ ሰዎች የሥራቸውን ሊያገኙ ይገባል፡፡ ይህ ነገር በሚገባ ይታሰብበት፡፡

የዘር ጥላቻና ቅስቀሳ የሚያስቀጣ ወንጀል ሊሆን ይገባል፡፡ በሚዲያ የሚሰራጩ ሕዝብን የሚያሳስቱ የዘር ቅስቀሳዎች ሲያጋጥሙ እነዚህን እያጣራ ተገቢውን እርምጃ የሚያስወስድ አካል ይኑር፡፡ በተጨማሪም ጎሣንና ሃይማኖትን መለያ አድርጎ የፖለቲካ ፓርቲ መቋቋምን የሚከልክል ህግ ይውጣ፡፡

በሀገር ውስጥ የሚታየው የባንዲራ ብዛት ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስላልና ይታሰብበት፡፡ ችግራችን የባንዲራ ሳይሆን የዳቦና የዴሞክራሲ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የባንዲራ ጉዳይ ቅንጦት ነው፡፡ ጊዜው የመኖር ወይ ያለመኖር ጥያቄ ገንኖ የወጣበት አስቸጋሪ ወቅት ነው፡፡

የጠላትን የሚዲያ ሥርጭት በየቀኑ -ከየቋንቋውና ከየሚዲያ ዓይነቱ – እየተከታተለ ዋና ዋና ጭብጦችን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የሥራ ኃላፊዎች የሚያቀርብ የባለሙያዎች ቡድን መኖር አለበት፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ጠላቶች ለሚነዙት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ተገቢ ምላሽ መሰጠት ይኖርበታል፡፡

ዝምታ አምኖ እንደመቀበል ሊቆጠር ይችላልና፡፡ ለምሣሌ ትግራይ ቲቪ በዚያን ሰሞን አንድ ዝግጅቱ ሀገርን የሚያምስ ቃለ መጠይቅ ከአንድ የጦር ጄኔራል ጋር ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ትግርኛ የሚችሉ የለውጡ ኃይሎች እንደዚህን ያሉ በጥባጮችን በየቋንቋው ማጋለጥ አለባቸው፡፡

በፎቶሾፕ እየተሠሩ በፌስቡክና በመሳሰለው የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ የሚሠራጩ የጠላት የሀሰት ፎቶዎች አሉና ሕዝቡ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆኖ እርስ በርስ እንዳይጨራረስ ተገቢው ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ለምሣሌ – “ኢትዮጵያ ማለት አማራ ብቻ ነው” የሚለው በፎቶሾፕ የተቀነባበረና ቀደም ካለ በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተወሰደ ምሥል፡፡

በኦሮሞና አማራ መካከል የምትነሳ አንዲት ትንሽ ልዩነት ያለፈውን የ27 ዓመታት የዘር መድሎና የመከራ ዘመን ልትመልሰው ትችላለችና የማኅበራዊ መሃንዲሶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ እውነትን ተናግሮ ከማጣላት ይልቅ ዋሽቶ እንኳን ቢሆን ማስታረቅ እንደሚገባ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ 

ያለን ብቸኛ ምርጫ በታሪክ ቁስል እየነፈረቁ ዛሬን መርሳትና በዱሮ ትውስታ መጃጃል ሳይሆን ታሪክን ለታሪክ ሰጥቶ ከዛሬ መከራና ስቃይ ለመውጣት መጣር ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን እያሻቀቡ የሚገኙት ጠላቶቻችን ራሳቸውና ጃዝ ብለው የላኳቸው የጠላቶቻችን ታዛዦች ናቸው፡፡ 

ይህንንም የሚያደርጉት የለውጡን ኃይል ተስፋ ለማስቆረጥና ለውጡን ከጅምሩ ለማጨናገፍ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የመቶ ብር ዕቃ እስከ አንድ ሽህ ብር መድረስ አልነበረበትም፡፡ ይህ የኢኮኖሚ አሻጥር በቶሎ መቀጨት አለበት፡፡ ነጋዴዎችም ላስቲክ ሆዳቸውን መላ ይበሉት፡፡

የጠላትን ተፅዕኖ በመፍራትም ይሁን በሙስና በመጨማለቃቸው ምክንያት ለውጡን ለመቀበል ፈራ ተባ የሚሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተራ ሠራተኞች ላይ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ “ቢያዩኝ እስቅ፣ ባያዩኝ እሰርቅ” እንዲሉ በተለይ በየወረዳውና በየከፍተኛው እንዲሁም በሌሎች የመንግሥት መ/ቤቶች የሚገኙ እነዚህ ዜጎች በአድርባይነትና በመሀል ሠፋሪነት ሕዝቡን እንዲያሰቃዩ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ 

አንዱን እንዲይዙ ይደረግ፡፡ ምርጫው የነሱው ነው፡፡ “የአፄ ኃ/ሥላሤ መንግሥት ይመለሳል፤ ያኔ ጉድ እንሆናለን” ከሚል ፍራቻ የየካቲት 66 ዓመተ ምሕረቱን ሀገራዊ ለውጥ ላለመቀበል የሚወላውሉ ብዙ ዜጎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ …

መታወቂያ ላይ ብሔር የሚለው ቢጠፋና በምትኩ ይልቁናስ የደም ዓይነት ቢሆን ለደም ልገሣም ጠቃሚ ነው፡፡ የመታወቂያ ብሔርና ጎሣ ለዕልቂት እንደሚዳርግ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞቹም አልተረዱትም፡፡ ፈጣሪ ይሁነን እንጂ የሚፈራው ቢደርስ የመጀመሪያ ሰለባዎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡

ሠራተኛ ሲቀጠር በዘሩ ሳይሆን በሙያ ብቃቱና በችሎታው፣ በሥራ ልምዱና በትምህርቱ ቢሆን – ለዚህም እንደ አጋዥ አሠራር ከስም ይልቅ የሥራ ማመልከቻዎች የቁጥር ኮድ ቢሰጣቸውና የጽሑፍም ሆነ የቃለ መጠይቅ ፈተናዎች ላይ ፈታኞች ተፈታኞችን በቁጥር ብቻ እንዲያውቋቸው ቢደረግ መልካም ነው፡፡ 

ለምሣሌ ፈታኙ “አምበርብር” ቢሆን “ጓንጉል” ለሚል ተፈታኝ አግባብነት የሌለው ዘውጋዊ መድሎ – ሳይታወቀውም ቢሆን – ሊያሳይ እንዳይችል በምሥጢራዊ መንገድ ሥራን ማቀላጠፍ ይቻላል፡፡ ስለሆነም “ጓንጉል፣ ፈይሣ፣ ሐጎስ፣…” በሆነ ቁጥር ቢወከሉ የማንንም ጎሣዊ ስሜት አይፈትኑምና ለእውነት የቀረበ የሠራተኛ ምልመላና ቅጥር ማካሄድ ይቻላል፡፡

ፓርላማውና የመንግሥት የሥራ ክፍሎች በተማረ ሰው እንዲሞሉ ይደረግ፡፡ የሀገር ልጅነትና የጎሣ ቀረቤታ፣ የዝምድናና የጉርብትና አሠራር ተወግዶ ትምህርትና ሙያዊ ብቃት ቦታ ይኑራቸው፡፡ ‹ትክክለኛው ሰው ለትክክለኛው ቦታ‹ ይመደብ፡፡ የሀገር ፍቅር ስሜት በተለይ በወጣቱ እንዲዳብር የቀን ከሌት ጥረት ይደረግ፡፡ ለብዙ መጥፎ ነገሮች መበራከትና መስፋፋት ዋናው መንስኤ የሀገር ፍቅር ስሜት መቀዝቀዝና መጥፋት ነው፡፡ አሁን ግለኝነት ሠፍኗል፤ አደገኛ ነገር ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማትም ጠፍተዋልና ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው የጠፋው ትውልድ ወደ ቀደመው የሞራልና የሃይማኖት ዕሤቶች እንዲመለሱ ጥረት ይደረግ፡፡ ሆዳምነትና ሙሰኝነት፣ ክህደትና ቃላባይነት ሀገራችንን በየዘርፉ አንቀው ስለያዟት ስንዝር መራመድ አልቻልንም፡፡ ስለሆነም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የነፃ ሚዲያ አስተዋፅዖ በእጅጉ ያስፈልገናልና በዚህ ረገድም ትኩረት ይሰጥ፡፡

የራስን ዜጎች መሰለል፣ ስልካቸውን መጥለፍ፣ ኢሜላቸውን ሰብሮ መግባት፣ በሆነ ባልሆነው ቤታቸውንና አካላቸውን በመፈተሸ ማስጨነቅ ከወያኔ ጋር ማለፍ አለባቸው፡፡ የመናገር፣ የመጻፍና የመሰብሰብ ነፃነቶች ይከበሩ፡፡

ባሳለፍነው የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን ሕወሓትን ተማምነው በዘር በመደራጀት በቡድንም ሆነ በተናጠል ወንጀል የሠሩ፣ አገርንና ሕዝብን የዘረፉ፣ ፍርድን ያዛቡ፣ ዜጎችን ከመኖሪያቸውና ከቀያቸው – ከእርሻቸውና ከንግዳቸውም ጭምር ያፈናቀሉ በወንጀል ይጠየቁ፡፡ ሀብት ንብረታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ቤታቸውን የተቀሙ ዜጎች አቤቱታቸው እየተጣራ ይመለስላቸው፡፡

mz23602@gmail.com

No comments