Latest

“ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት አንድም የረባ ጄኔራል አላፈራችም” ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ክፍል ፫)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ግዮን፡- ወደ ኢህአዴግ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ስንመጣስ? 
ተመስገን፡- ኢህአዴግ ጋር ስንመጣ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታው ይበልጥ አስቂኝ ነው:: ሁላችንም እንደምናስታውሰው በሽምቅ ውጊያ አሸናፊ ሆኖ ነው ወደ ቤተ መንግሥት የገባው:: እንግዲህ ኢህአዴግ በርካታ ታላላቅ ጥፋቶችን ፈፅሟል። 

ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚገባው ኢትዮጵያ ብዙ ወጪ ያፈሰሰችበትን ጦር ሠራዊት:- ጄኔራሎች፣ ኮሎኔሎች፣ ሻለቆች ጀምሮ እስከ ተራ ወታደሮች ድረስ ያሉትን አባላት በጅምላ ወንጅሎና አባርሮ ሲያበቃ፤ ከበረሀ የመጡትን የሽምቅ አዋጊዎችን በአዛዥነት ቦታ ላይ ማስቀመጡ ይመስለኛል:: ሽምቅ ተዋጊ ለመሆን ከቤትህ ወጥተህ ጫካ ገብተህ መሸፈት ብቻውን በቂ ነው:: ምንም አይነት ወታደራዊ ሥልጠና አያስፈልግህም።  

ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ፣ የመንግስትነትን ሥልጣን እንደያዘው ሁሉ፤ ለእዚህ ድል ያበቁትን ሽምቅ ተዋጊዎች በሙሉ፣ በጫካ እንደነበረው ኃላፊነታቸው ነው የኢትዮጵያን ሠራዊት በተዋረድ እንዲተኩ ያደረገው:: 

የኢህአዴግ ትልቁ ስህተት፣ ሀገር የገደለበት፣ ሀገር ያዋረደበት፤ ነገር ግን ብዙ ያልተወቀሰበት ጥፋቱ ለ50 ዓመታት እየወደቀና እየተነሳ የዘለቀውን የሠራዊት ግንባታ ሙሉ በሙሉ አፍርሶ፤ የሽፍታ ባህርይ ባለው ሽምቅ ተዋጊ ተክቶ ‘የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብራለሁ፤ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋምም በረህኞቹ ብቁ ናቸው’ ብሎ የወሰደው እርምጃ ነው::  

መቼም ኢትዮጵያን የምታህል የነፃነት ቀንዲል ሀገር ክብርን በገበሬ ሠራዊት የማስከበር ብላሃት ለእነ መለስ ብቻ የተገለጠ "ጥበብ" ይመስለኛል። በወቅቱ መከላከያ ሚንስትር ተደርጎ የተሾመውን አቶ ስዬ አብርሃን ብትወስደው በትግሉ ዘመን የኢህአዴግ ወታደራዊ አዛዥ ሲሆን፤ ከትግሉ በፊት ደግሞ የህክምና ተማሪ ነበር፤ የደርግ ሥርዓት አስከፋኝ ብሎ ጫካ ገባ፤ ልክ እንደ እሱ ያሉትን ተማሪዎች እና የገበሬ ልጆችን ሰብስቦ ሲያበቃ ወታደራዊ አዛዣቸው ሆነ::  

በተለያየ ውስጣዊና ውጪያው ምክንያት ደርግ ሲገረሰስ የመከላከያ ሚንስትር ሆነ፤ ሌሎች ጓደኞቹንም እንዲሁ በተለያዩ የአዛዥነት ቦታዎች ሾመ። ስለዚህ በኢህአዴግ ጊዜ ስለ ዘመናዊ ሠራዊት ልናወራ አንችልም:: ከጻድቃን ገ/ትንሣኤ ጀምረህ እስከ አበበ ጆቤ፤ ከሳሞራ የኑስ እስከ ሀየሎም አርዕያ፤ ከሰዓረ መኮንን እስከ ዮሀንስ ገ/መስቀል ድረስ ያሉ ዋና ዋና አዛዦችን ብንገመግም አንዳቸውም ሚሊተሪ ኮሌጅ ገብተው ሥልጠና አልወሰዱም::  

በጦረኝነት ክብር ታገኝ ይሆናል፤ ነገር ግን በየትኛውም ሀገር ጦረኛ ስለሆንክ ብቻ የጄኔራልነት ማዕረግ ይዘህ በተቋም ኃላፊነትም ሆነ በአዛዥነት አትሾምም:: ወታደራዊ ሳይንስ ከባድና ጠጠር ያለ ፍልስፍና ነው፤ በዚህ መስክ ብቃትና ዕውቀት ይዘህ ነው በእርከን ቀስ በቀስ ጄኔራልነት ቦታ ላይ የምትደርሰውም ሆነ በኃላፊነት የምትቀመጠው:: 

ኢህአዴግ ያሳየን ግን የጄኔራልነት ሹመት ከጫካ ስለመጣህ ብቻ እንደሚገባህ ነው:: ይህንን የኢህአዴግ የወረደ አሠራር ተቀብላ የተገበረችው እኔ እስከማውቀው ድረስ የትናንቷ ደቡብ ሱዳን ብቻ ናት፤ ኤርትራም ተመሳሳዩን መንገድ ብትከተልም፤ ከዚህ ወቀሳ ነፃ ነች:: ምክንያቱም ሻዕቢያ ‘ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም’ ብሎ ነው ለግንጠላ ጫካ የገባው፤ ስለዚህም ሥልጣን ሲይዝ የኢትዮጵያን ሠራዊት ይዞ ሊቀጥል አይችልም:: 

እናም ወያኔ/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሠራዊት በትኖ የራሱን ሲያዋቅር፤ በወቅቱ የነበረው የውጊያ ብቃት፣ ልምድና አስተሳሰብ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ከነበሩ ወታደሮች እምብዛም የራቀ አልነበረም:: ይህ በንጉሡና በደርጉ ጊዜ ከነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር በፍፁም አይነፃፀርም:: 

ከጫካ ያመጣቸውን ሽምቅ ተዋጊዎችን በጅምላ አጥምቆ ሲያበቃ የመንግስት ወታደር መሆናቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ካርድ ነው ያደላቸው። ውትድርና ደግሞ በበቂ ስልጠናና ትምህርት የሚገኝ ሙያ እንጂ፣ መታወቂያ ስለያዙ ብቻ ብቁ የሚኮንበት የስራ መደብ አይደለም።  

እነ አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቦይ ስብሃት፣ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ተወልደ፣ አባይ ፀሀዬና ጓዶቻቸው ይሄንን ሲያደርጉ፣ በደርግ ሥርዓት የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አዛዦች ብቃት ላይ ጥርጣሬ ኖሯቸው አልነበረም:: ለዓመታት ለፈፀሙት ጭቆና እና የጥቂት ቡድኖችን ጥቅም የሚያስከብር ሥርዓት ሕልውና ዘብ የሚቆሙት ከጫካ በሽምቅ ተዋጊነት የመጡት እንደሆኑ ስለሚያምኑ ብቻ ነው::  

ግዮን፡- የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ሂደቱን በተመለከተ ያለህ ጠቅለል ያለ አስተያየትን ግለፅልኝ? 
ተመስገን፡- ችግሮቹና ልዩነቶቹ ቀደም ሲል ያነሣኋቸው ነጥቦች ሲሆኑ፣ መከላከያ በዋናነት እየወረደ የመጣው፣ መ/ቤቱ ብቻ ሳይሆን ክብሩም ጭምር ነው:: በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ወታደር ሠርግና ድግስ ሲጠራ፣ የወታደር ልብሱን ለብሶ ካልሄደ የጋባዦችን ክብር መንካት ተደርጎ ነበር የሚቆጠረው:: ምክንያቱም በወቅቱ ውትድርና የተከበረና የሚያኮራ ሙያ ስለነበረ ነው።  

በደርግ የመጨረሻዎቹ ጊዜያት ደግሞ ወታደርነት ይጠላ ነበር፤ ሀገሪቱ ከባድ ጦርነት ላይ ስለነበረች ተቀጥረህ ገና በደንብ ሳትሰለጥን ወደ ጦርነት ነበር የምትላከው፤ ጉዳዩ የእናት ሀገር በመሆኑ አፈሳም ነበር:: መንግሥቱ ኃ/ ማርያም ይህንን መንገድ ለመምረጥ የተገደደው በሰሜን ቅድም የጠቀስናቸው አማፂያን ጋር ውጊያ ውስጥ ስለነበረና ‘የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው’ ብሎ ስላመነ፤ መደበኛውን ወታደራዊ ሥልጠና ሰጥቶ፣ ውጭ ሀገር ልኮ አስተምሮ ብቁ ወታደር የሚያወጣበት የእፎይታ ጊዜ ስላልነበረው መሆኑንን መረዳት አያዳግትም::  

የወያኔ ዘመን ደግሞ የባሰበት ነው፤ ሠራዊቱን እንደ መመኪያ ጋሻ የሚቆጥረው የለም፤ በግልባጩ በጠላትነት ነው የሚያየው:: ይህ የሆነው ሀገር እንዲቆረስ በማድረጉ፣ የሀገሪቱ አንድነት እንዲዳከም ለፖለቲከኞች ኃይል በመሆኑ፤ ባልታጠቁ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ ጥይት የሚያርከፈክፍ ጅምላ ጨፍጫፊ የቤተ-መንግስት ሎሌ ስለሆነ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና አሁን ያለው የኢህአዴግ መከላከያ ሠራዊት ወዳጅ ሆነው አያውቁም:: ‘  

የኢህአዴግ ወታደር ነኝ’ ብሎ ደፍሮ መናገር የሚያሳፍርበት ዘመን ላይ ነው የደረስነው:: ‘በወያኔ ጊዜ የመከላከያው መዋቅር ብቻ ሳይሆን፤ ክብሩም ጭምር ነው የወረደው’ ያልኩት ለዚህ ነው:: 

ግዮን፡- እንደ መፍትሔ የአንተ ሐሳብ ምንድን ነው? 
ተመስገን፡- በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ሠራዊቱ እንዲመለሱ የተደረጉት በደርግ ሥርዓት የነበሩ የጦር መኮንኖች ያቀረቧቸው ፕሮፖዛሎች ሥራ ላይ ውለው በጣም ጥሩ ጥሩ የሆኑ የሚሊተሪ ኮሌጆችና ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ተቋቁመዋል:: 

ይሄ ጥሩ ጅምር ነው። ችግሩ ምንድን ነው? ካልን፣ በአዛዥነትም ሆነ በተለያየ የአስተዳደር ቦታዎች የተቀመጡት ቅድም የጠቀስናቸው የሽምቅ ውጊያ ጄነራሎች ናቸው፤ እነሱ ለዘመናው ትምህርትና ስልጠና አላርጂክ ናቸው። አልፎ ተርፎም ወደ ማሰልጠኛም ሆነ ወደ መከላከያ ዩንቨርስቲ የሚገቡ የሠራዊቱ አባላት አብዛኛው በነበራቸው የትምህርት ብቃት ወይም ደግሞ በመግቢያ ፈተና በሚያስመዘግቡት ነጥብ አይደለም:: 

በዘመድ አዝማድ ነው፤ ህወሓት ሠራዊቱን እንደ ግል ዘቡ ይቆጥረዋል የሚባለውም ለዚህ ነው:: በተረፈ የትምህርትና የሥልጠና ተቋማቱ መገንባታቸው ጥሩ ነው፤ የዶ/ር አብይ መንግሥት የሚሰማ ከሆነ፣ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ የጄኔራልነት ማዕረግ የያዙት ወደ ኮሎኔልነት ዝቅ ብለው፤ ሌፍተናንት፣ ሜጀር እና ብርጋዴል ጄኔራሎች በጠቅላላ ወደ ሻለቃነት ዝቅ ብለው፤ ከኮሎኔልነት ጀምረው ያሉት ደግሞ እንደየ እርከኑ ወደ ታች ወርደው፣ ማዕረጋቸውን ቀንሰው፣ ወታደራዊ ሥርዓት ግንባታው ከዜሮ መጀመር አለበት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት አንድም የረባ ጄኔራል አላፈራችም:: 

በሚሊተሪ ሳይንስ አካዳሚ ገብቶ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ወታደራዊ ተቋማት ተፈትኖ የተረጋገጠለት ብቁ ጄኔራል ስለሌለ፤ አሁን "ጄኔራል" ነን የሚሉት ሰዎች ካሉበት ወርደው አስተዳደሩ ላይ እንደ የአቅማቸው ቢመደቡ፣ አልያም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወታደራዊ ትምህርት እንዲማሩ ተደርገው ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፣ ተመልሰው ኃላፊነታቸውን እንዲረከቡ ቢደረግ ጥሩ ቁመናና ቅርፅ ያለው ዘመናዊ ሠራዊት ማፍራት ይቻላል:: 

አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከእኛ የበለጠ መከላከያውን ስለሚያውቁትና በዚያ ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው፤ እርሳቸውም የኮሎኔልነት ማዕረግ ላይ ሲደርሱ፣ በየትኛውም ደረጃውን በጠበቀ ወታደራዊ ትምህርት ቤት ገብተው አለመሆኑን አይስቱትም። ወያኔ ለራሷ ታጋዮች ማዕረግ እንደ ፀበል ስትረጭ፣ ለማስመሰል ለብአዴንና ለኦህዴድ አባላት በኮታ መልክ በስሱ የመበተኗ ውጤት ነው ኮለኔል ያደረጋቸው:: 

አሁን ኢህአዴግ ከዚህ መሰሉ የኮታ አስተሳሰብ ወጥቶ፣ በችሎታ ላይ የተመሰረተ ቅጥር፣ ሥልጠናና ሹመት መስጠት መቻል አለበት፤ ኢትዮጵያ ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሚመጥን፣ በአባይና በወደብ ጉዳይ ከሌሎች ሀገራት ጋር ውዝግብ ውስጥ ብትገባ፤ እንዲሁም በአፍሪካ በሚደረጉ የተለያዩ ፉክክሮች ላይ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በጣም ጠንካራ የሆነ ሠራዊት መገንባት ይጠበቅባታል:: 

በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ መከላከያው ላይ ይተገበራል የተባለው የሪፎርም ፖሊሲ የብሔር ኮታን ማመጣጠን ታሳቢ ያደረገ ነው የሚባለው አደገኛ መሆኑን ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።  

ግዮን፡- በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት የተከተሰተውን የፖለቲካ ልዩነት ተከትሎ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወደ ሠራዊት እንዲመለሱ ተደርገው የነበሩ የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት በአጋጣሚው ከኃላፊነታቸው እንዲነሡ ተደርገዋል፤ አሁን በአዲስ መልክ መዋቀር ባለበት የዘመናዊ ሚሊተሪ ውስጥ እነዚህ ሰዎች መካተት የለባቸውም?  
ተመስገን፡- ስለ ምርጥ ሠራዊት ስናወራ ዋናው አጀንዳችን አዛዦችና መኮንኖች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ምክንያቱም አመራሩ ረብ የለሽ ከሆነ ብቁ ወታደሮችን ከታች ማፍራት አይቻልምና:: ሳይንሱም የሚለው "የሠራዊት ራስ አመራሩ ነው"። 

እነ መለስ ዜናዊ የረሱትም ይህንን ነው። በ1990 ዓ.ም በደርግ ዘመን የነበሩት ጄነራሎችና ኮለኔሎች የተጠሩት ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ ነው:: በነገራችን ላይ እነዚያ የኢህአዴግን ጥሪ ተቀብለው ሠራዊቱን የተቀላቀሉት ጄነራሎች፣ ከማንም በላይ ባለውለታና በአደባባይ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው:: 

ከእስር ቤት የመጡ ሁሉ አሉ፤ ‘ይሄ ሥርዓት ሰባትና ስምንት ዓመት ከሥራችን አባሮ፣ እስር ቤት ወርውሮናል፤ ሜዳ ጥሎናል’ ብለው አላኮረፉም፤ ‘የሀገር ጉዳይ ነው’ ብለው ነው የመጡት፤ እነዚህ ሰዎች ያላቸውን ንቃተ ሕሊናና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በዚህ መለካት ትችላለህ: በጦርነቱ ላይም የስትራቴጂስት ሚና የነበራቸው እነርሱ ናቸው:: 

የተገኘው ድል የእነርሱ የአእምሮ ውጤት እንደሆነም ይነገራል። ይህም ሆኖ በወያኔ በኩል እምነት ተጥሎባቸው በቀጥታ ሠራዊት ይዘው ግንባር ላይ ውጊያ እንዲመሩ አልተደረገም:: 

ነገር ግን ከሜጀር ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሣኤ እና ሳሞራ የኑስ ጀምሮ ሁሉምን አዛዦች ማዕረጋቸውን አስወልቀው፣ ደብተር አስይዘው የአጭር ጊዜ ትምህርት አስተምረዋቸዋል፤ የተለያየ ስልጠና ሰጥተዋቸዋል፤ የካርታ አነዳደፍና አነባብ እውቀትን በጨረፍታ አስጨብጠዋቸዋል፤ ፀረ-ማጥቃቱን በሙሉ በአሸዋ ጉብታ ላይ የጨረሱት እነዚህ የቀድሞ የጦር መኮንኖች ናቸው:: ይህም ሆኖ ከጦርነቱ በኋላ በመከላከያ ውስጥ እንዲቀጥሉ ከተደረጉት መኮንኖች መሀል አንድም ሰው በወሳኝ ኃላፊነት ላይ አልተመደበም::  

አማካሪነትም እንደ ወሳኝ ሥልጣን ታይቶ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ ብዙዎቹ ተባርረዋል፤ ለተራዘመ እስርም ተዳርግዋል:: ዝዋይ እስር ቤት በነበርሁበት ጊዜ፣ እነ ኮ/ል አበበን የመሳሰሉ ስምንት ያህል የጦር መኮንኖች፣ ‘የቅንጅት አባል ናችሁ’ ተብለው በሀሰት ተከስሰው፣ የክፉ ቀን ውለታችው ሁሉ ተዘንግቶ ዐሥራ ስምንት ዓመት ተፈርዶባቸው ሲማቅቁ ቆይተው ዘንድሮ ከእኛ ጋር ነው የተፈቱት::  

ያኔም ቢሆን ወያኔ የጠራቸው በኃላፊነትና በመሪነት ሊያስቀምጣቸው ሳይሆን፤ በችሎታቸው ሊጠቀም ስለፈለገ ብቻ ስለሆነ፣ በትክክል ሠራዊቱ ውስጥ ነበሩ ማለት አንችልም:: በዚህ አጋጣሚ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ማሳሰብ የምፈልገው፣ በየትኛውም ዓለም ውስጥ በሠራዊት ውስጥ የሚዋቀር ሚሊተሪ ካውንስል የሚባል አለ::  

በብዙ የአደጉ ሀገራት የሚሊተሪ ካውንስል አባል ሆኖ የሚሾመው ጡረታ የወጣ ጄኔራል ነው። በቂ ልምድ አለው ተብሎ ስለሚታሰብ። ኢህአዴግ ያደረገውን ብናይ ግን ከአስራ ስድስቱ የሚሊተሪ ካውንስል አባላት ሁሉም በስራ ላይ ያሉ ናቸው:: ራሱ ስለሚመራው ተቋም የካውንስል ኮሚቴ ውስጥ ሆኖ ምን አዲስ ሐሳብ ያመጣል? ተብሎ እንደተሾመ ሊገባኝ አልቻለም::  

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን ሠራዊት አዘምናለሁ ብለው ካሰቡና የተዘጋጀ ፖሊሲ ካላቸው፣ መጀመሪያ ሚሊተሪ ካውንስሉን ሙሉውን በትነው፣ በደርግ ጊዜ የነበሩትን ጄኔራሎች ወደ ካውንስሉ በማካተት ሠራዊቱ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚሸጋገርበትን ዕቅድና ምክር እንዲሰጡ ቢያደርጉ መልካም ነው::  

በወያኔ ዘመን ጡረታ የወጡትን የካውንስሉ አባል ማድረግ አይጠቅምም፤ ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ ነው። መከላከያ እነርሱ ሲመሩት የነበር ተቋም በመሆኑ፣ የተሻለ ጠቃሚ ሃሳብ ቢኖራቸው ኖሮ ስራ ላይ እያሉ ይተገብሩ ነበር። ስለዚህም እነሱን መልሶ የካውንስል አባል ማድረግ፣ ችግሩን መልሶ ማምጣት ነው።

No comments