Latest

ኢትዮጲያዊ ነኝ! (አሌክስ አብርሃም)

ኢትዮጲያዊ ነኝ! (አሌክስ አብርሃም)

ከኢትዮጲያ ምድር እግሬ ከለቀቀበት ሰዓት ጀምሮ እስከትላንት ድረስ ኢትዮጲያ ውስጥ ሰለሚፈጠሩ ዝርዝር ጉዳዮች እንጅ ሰለኢትዮጲያዊነት ለሰከንድ አስቤ አላውቅም ! 


አለማሰብ ካለመሆን የሚመጣ ጉዳይ አይደለም! እንደውም አለማሰብ ሁኖ ከመጨረስ የሚመጣ መረጋጋት ይመስለኛል ! ያው ብር ከሌለህ ስለብር ታስባለህ ፣ካላገባህ ስለማግባት ፣ ካልወለድክ ሰለመውለድ ፣ ካልተማርክ ሰለመማር ፣ስራ ከሌለህ ሰለስራ . . .  

ኢትዮጲያዊ ከሆንክ በቃ ነህ ኢትዮጲያ ውስጥ ሰለሚከወኑ ጉዳዮች እንጅ ስለኢትዮጲያዊነት ምን ልታስብ ትችላለህ? እና በተለይ አሜሪካ ከገባሁ በኋላ በራሴ ጉዳዮች ተጠምጀ ይሁን ወይም በሄደበት የሚለምድ ተፈጥሮየ አስረስቶኝ ብቻ ኢትዮጲያ ውስጥ ሰላሳለፍኩት ሕይዎት ምናምን ቦታ ሰጥቸ ማሰቤ ትዝ አይለኝም!

ትላንት ግን እንዲህ ሆነ ! አንድ በጣም የምወደው የግሪኮች ቡና መሸጫ ቤት አለ! በተለይ አሁን ወቅቱ ጸሃያማ ስለሆነ በረንዳው ላይ ተቀምጨ ፊት ለፊት እስከአድማስ የተዘረጋው ንጹህ ሰማያዊ ውሃ ላይ የሚንሳፈፉ ጀልባዎችንና አልፎ አልፎም ውሃ ላይ የተሰራ ከተማ የሚመስሉ ትላልቅ መርከቦችን እያየሁ ቡናየን መጠጣትና እዛው ቤት የሚሰሩ ጣፋጭ ብስኩቶችን ማጣጣም ደስ ይለኛል !  

አልፎ አልፎ ደግሞ እጅግ ዝቅ ብለው የሚበሩ አውሮፕላኖች ያልፋሉ ! በጣም ዝቅ ከማለታቸው ብዛት ድምጻቸው የቡና ሲኒየን ሲያንቀጠቅጠው ሁሉ እያየሁ ደስ ይለኛል ! አውሮፕላኖቹ በዛ ዝቅታ የሚያልፉት በቅርብ ርቀት የአውሮፕላን ማረፊያ ስላለ ነው!! ለብዙ ወራት በዙ አውሮፕላኖችን ከማየቴ ብዛት አሁን አሁን ብዙም ትኩረት አልሰጠውም !

ትላንት ታዲያ አንድ አውሮፕላን እጅግ ዝቅ ብሎ ሲበር ድምጹን ሰማሁና እንዲሁ ቀና ብየ አየሁት ፣ ግዙፉ የኢትዮጲያ አየር መንገድ አውሮፕላን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራውን ጅራቱ ላይ አጋድሞ ልክ እንደህልም እየተንሳፈፈ ሲያልፍ ዘልየ ከወንበሬ ተነሳሁ (ምን አስበረገገኝ) የቡና ጠረጴዛውን ጫፍ ነካሁት መሰል ቡናየ ተከነበለ!

ይህን ቅጽበት በምንም ቋንቋ መግለጽ አይቻልም ልቤ በድንጋጤ ቀጥ ያለች ነው የመሰለኝ ! ከእግር ጥፍሬ እስከእራስ ጸጉሬ የማላውቀው ስሜት ወረረኝ ! ሰማዩን ሰንጥቆ የተገለጠ መልዓክ ያየሁ ያህል ነበር አግራሞቴ ! ወሬ ለማሳመር አይደልም እንዲሁ ነው የተሰማኝ ! የመጀመሪያየ ነው የኢትዮጲያ አውሮፕላን እዚህ አገር ሰማይ ላይ ስመለከት !

ወደቀልቤ ስመለስ ትንሽ አለፍ ብሎ የተቀመጠውን ጢማም ሽማግሌ ፈረንጅ ፈገግ ብየ <<ኢትዮጲያዊ ነኝ! አሁን ያለፈው አውሮፕላን የኢትዮጲያ ነው>> አልኩት የምንተፍረቴን በጣቴ ወደሰማይ እየጠቆምኩ ! ደግነቱ ፈረንጅ ጋር ወሬህን ከየትም መጀመር ትችላለህ ! መግቢያ ምናምን አያስፈልግህም ወሬ የጠማቸው ህዝቦች !  

<<ኦ እውነትህን ነው ? >> ብሎ ሞቅ ያለ ፈገግታ ካሻረኝ በኋላ ሸርተት ብሎ ተጠጋና ለትውውቅ እጁን ዘርግቶ ስሙን ነገርኝ ! ማንም እንዳለኝ እንጃለቱ ! ወዲያው ነው የረሳሁት ! ቀጠል አድርጎ << እንደማይህ ከሆነ አውሮፕላን አድናቂ ነህ. . . ታበር ነበር?>> ብሎኝ እርፍ !  

ሊያቆም ነው እንዴ? ጡረታ የወጣ አብራሪ እንደሆነና ከምናምን ሺህ ማይልስ በላይ የአገር ውስጥና አለም አቀፍ በረራዎችን እንዳደረገ ለአውሮፕላን ልዩ ፍቅር እንዳለው ፣ እንዲሁም የባለ ምናምን ሞተርና የባለምንትስ ክንፍ አውሮፕላን አንድነትና ልዩነት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጠኝ !

እኔ አሁን በዚች ቅጽበት የፈለኩት ሰለኢትዮጲያ ምንም ነገር የሚያወራኝ ሰው ነው !! አየር መንገዳችን በአፍሪካ አንደኛ በአለምም አንደኛ ከማርስም አንደኛ መሆኑን፣ ባንዲራችን አረንጓዴው ልምላሜ፣ ቢጫው ተስፋ ቀዩ ደም . . . ወዘተ የሚለኝ ፣ ቢፈልግ እንደአዲስ የመለስን ሞት የሚያረዳኝ ፣ የቆሸን ቆሻሻ መደርመስ ፣ ኤርትራ ኢትዮጲያን መውረሯን ፣ ወላ ዚያድ ባሬ በምሰራቅ እንደወረረን ብቻ ሰለኢትዮጲያ ማንኛውንም ነገር ! ብቻ ሰለአገሬ ሰለኢትዮጲያዊነት፣ ሰለበርበሬ፣ ሰለቡና፣ ሰለታክሲ ሰልፍ ። ሰለመብራት መጥፋትና መምጣት፣ የሚያወራኝ ሰው ነው የምፈልገው !  

<<ወደኢትዮጲያ በረህ ታውቃለህ ?>> አልኩት
<<ይቅርታ ኢትዮጲያ የት ነች?>>
<<ብሽቅ !ኢትዮጲያን ካላወክ ታዲያ ወደየትስ ብትበር ምናገባኝ >> ብለው ደስታየ !

ከምር ተከዝኩ፣ ያ አውሮፕላን ዝቅ ብሎ ምናይነት ቦምብ ነው እኔ ላይ ብቻ ጥሎብኝ የሄደው ? ከፊቴ የተጋደመውን ውሃ በትካዜ አየሁት ተመኘሁ . . .ይሄ ውሃ ያዲሳባ መንገዶችን የሞላ የዝናብ ወሃ በሆነ ብየ . . .ተመኘሁ ይሄ ቤት አራዳ ህንጻ ማንኪራ ኮፊ፣ ብሔራዊ ሃሮ ኮፊ በሆነ ብየ . . . ተመኘሁ ውሃው ላይ የማያቸው ቅንጡ ጀልባዎች ካራዳ ህንጻ ስር ውር ውር የሚሉ ሚኒባሶች በሆኑ ብየ . . .  

ፍልቅልቅ የምትል የእንግሊዞች አክሰንት ያላት ቆንጆ ሴት በትልቅ የጠርሙስ ጆግ ቡና ይዛ ከመወልወያ ፎጣ ጋር <<አዝናለሁ ሰለቡናህ ሌላ ልቅዳልህ?>> አለችኝ 

ተመኘሁ ይች ረጃጅም እግሮቿን ያጋለጠ አጭር ቀሚስ የለበሰች እስከጆሮ ክንዷ ውብ ከንፈሯን ለጥጣ የምትስቅ ሴት ኮንጎ ጫማ አድርጋ ከነንቅሳቷ አዲስ አበባ መንገዶች ላይ የጀበና ቡና በጤናዳም የምትሸጥ ሴት ብትሆን ብየ . . . ተመኘሁ ያለፈው አውሮፕላን ተመልሶ ይዞኝ ወደኢትዮጲያ በከነፈ ብየ !!

No comments