Latest

የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች እንዴት ሥራ ያገኛሉ? ቢቢሲ

የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች እንዴት ሥራ ያገኛሉ?

ክረምት አዳዲስ ምሩቃን ከትምህርት ዓለም ወደ ሥራ ፍለጋ የሚሸጋገሩበት ነው።

በርካቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም መመረቅ የሚሰጠውን ደስታ አጣጥመው ሳይጨርሱ ሥራ አገኝ ይሆን? በሚል ስጋት ይዋጣሉ።

ሥራ ማፈላለጊያ የትምህርት ማስረጃ ከማሰናዳት አንስቶ በየማስታወቂያ መለጠፊያው ማማተር፣ እድለኛ ከሆኑ ደግሞ ለሥራ ቅጥር ግምገማ የጽሁፍና የቃል ፈተና መዘጋጀትም ይጠበቅባቸዋል። ምሩቃን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አሟልተውም ሥራ ለማግኘት ሲቸገሩ ይታያል።

ሥራ ፍለጋን ለማቅለል እንዲሁም ቀጣሪና ተቀጣሪን በአንድ መድረክ ለማገናኘት ያለመ መርሀ-ግብር ያሳለፍነው አርብና ቅዳሜ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ ተካሂዶ ነበር። መድረኩ አዳዲስ ምሩቃን የትምህርት ማስረጃቸውን ሊቀጥሯቸው ለሚችሉ ድርጅቶች እንዲሰጡ እድል አመቻችቷል።

የትምህርት ማስረጃቸው በቀጣሪዎች ለማስገምገም በቦታው ከተገኙት መካከል ኬነሳ ሒካ ገምቴሳ እና ፌነት ማስረሻ ይገኙበታል። ኬነሳ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ምሩቅ ፌነት ደግሞ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ተመራቂ ናቸው።

ኬነሳ ከዚህ ቀደም በዋነኛነት ሥራ የሚፈልገው ጋዜጣ ላይ ነበር። ስለ መርሀ-ግብሩ ከሰማ በኋላ በደረጃ ዶት ኮም ድረ ገጽ ተመዝግቦ ተሳታፊ ሆኗል። "ፍላጎቴ የትኛውም ድርጅት ሲቪዬን ተመልክቶ ቢቀጥረኝ ነው" ይላል።

ተመራቂዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ለቀጣሪዎች ሰጥተዋል
ተመራቂዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ለቀጣሪዎች ሰጥተዋል
ፌነት በበኩሏ "መድረኩ አዳዲስ ተመራቂዎች ሥራ እንዲያገኙ ያግዛል" ስትል በመርሀ ግብሩ የተገኙት ተቋሞች የትምህርት ማስረጃዋን ገምግመው ብቁ ከሆነች ሥራ እንደምታገኝ ተስፋዋን ትናገራለች።

መርሀ ግብሩ ቀጣሪዎች በተለያየ መስርያ ቤት ልምድ ላካበቱ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን ለአዳዲስ ምሩቃንም የቅጥር እድል እንዲሰጡ ለማሳሰብ ያለመመም ነበር።

የኢትዮ ጆብስ ወይም ኢንፎ ማይድስን ሶሉሽንስ ሪጅናል ዳይሬክተር ህሊና ለገሰ እንደምትናገረው መሰናዶው ዋነኛ አላማው በተመራቂዎችና ቀጣሪዎች መካከል ድልድይ መፍጠር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ተመራቂዎች የት ተቋም ማመልከት እንዳለባቸው አያውቁም። ቀጣሪዎች በአንጻሩ አዳዲስ ተመራቂዎችን ለመቅጠር ተነሳሽነት አያሳዩም።

ክፍተቱን ለመሙላት በሚል ኢትዮ ጆብስ፤ ደረጃ ዶት ኮም ከተሰኘ ድረ ገጽ እንዲሁም ከትምህርት ሚንስቴር ጋር በመተባበር የሥራ ማፈላለጊያ መድረክ (ጆብ ፌር) አዘጋጅቷል።

በመድረኩ 250 ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከሦስት ሺህ በላይ ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ለተመራቂዎቹ አቅርበዋል። በ2010 ዓ. ም የተመረቁ ተማሪዎች በኢትዮ ጆብስ ድረ ገጽ ካመለከቱ በኋላ የመድረኩ ታሳታፊ ሆነዋል።

ተመራቂዎቹ ስራ የማግኘት ተስፋ ሰንቀዋል
ተመራቂዎቹ ስራ የማግኘት ተስፋ ሰንቀዋል
በዚህ መድረክ ላይ ተሳታፊ ለሆኑት በዳይሬክተሯ አማካይነት ተማሪዎቹ ሥራ ለመፈለግ የትምህርት ማስረጃ (ካሪኩለም ቪቴ ወይም ሲቪ) ስለሚጽፉበት መንገድ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

"ብዙ ድርጅቶች ልምድ ያላቸው ሰራተኞች መቅጠር ይፈልጋሉ። ሆኖም አዳዲስ ምሩቃንም ስልጠና ከተሰጣቸው የመቀጠርና የማደግ አቅም እንዳላቸው ማሳየት እንፈልጋለን" ትላለለች።

በመድረኩ ወደ 20 ሺህ ተማሪዎች ከመሳተፋቸው ባሻገር ሰባት ዩኒቨርስቲዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኙ ተደርጓል።

በየዓመቱ ከ160 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ይመረቃሉ። ተመራቂዎቹ ሥራ በሚፈልጉበት ወቅት ምን እንደሚጠበቅባቸው ስልጠና መውሰድ እንዳለባቸው ህሊና ታምናለች። ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ድርጅት ተቀጥረው የሙከራ ሥራ (ኢንተርንሺፕ) እንዲሰሩ ማድረግም ከተመረቁ በኋላ ለሚጠብቃቸው የሥራ ዓለም ያግዛል ትላለች።

"ተማሪዎች የተሻለ ክህሎትና የመቀጠር ብቃት እንዲኖራቸው ተደርገው መመረቅ አለባቸው" ትላለች።

መርሀ ግብሩን ዓመታዊ የማድረግ እቅድ አለ።

No comments