በሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዛሬም እየተሰቃዩ ነው - ቢቢሲ
ህልሟ ባህር አቆራርጦ ጣልያን መግባት ነበር። ከወራት በፊት ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አበባ አቀናች። አስከትላም ወደ መተማ አቅንታ ሱዳን ወስጥ አራት ወራትን አሳለፈች።
እንደሷው ያሉ ስደተኞች በሰሀራ በረሀ ለሚያዘዋውር ግለሰብ ገንዘብ ከፍላ በረሀውን በመኪና አቋረጠች። ሊቢያ አንደደረሰች ደላላ ተቀበላት። ተቀብሎም ለሌላ ደላላ ሸጣት።
ሊቢያ ውስጥ ኢምወሊድ የሚባል አካባቢ እሷና ሌሎችም ስደተኞች ታሰሩ። "ገንዘብ ክፈሉ" እየተባሉ ይደበደቡ እንደነበረ ትናገራለች።
ከእስር ቤቱ ለመውጣት ከኢትዮጵያ ወይም ከሌላ ሀገርም ገንዘብ እንዲያስልኩ በማስገደድ ያሰቃዩዋቸው እንደነበረም ታክላለች።
ወጣቷን በስልክ ያነጋገርናት ሊቢያ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሳለች ነው። ከእስር ቤቱ ኢንዛራ ወደሚባል ቦታ ከተወሰዱ በኃላም እንግልቱ እንደቀጠለ ለቢቢሲ ገልፃለች።
"ከተደፈሩ ሴቶች አንዷ እኔ ነኝ" ትላለች ከደረሰባት ሁሉ የከፋውን ስትናገር።
በርካታ ሴቶች እንደሷ ተደፍረዋል፤ ተደብድበዋል። የተገደሉ እንዳሉም ትናገራለች። ካሉበት መጠለያ ለማምለጥ የሚሞክሩ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰው ድብደባ የከፋ ነው።
"እንድንፈራ እኛ ፊት ነው እንዳይሞቱም እንዳይድኑ አድርገው ነው የሚቀጠቅጧቸው" ትላለች። ያሉበትን ሁኔታ የሚነግሩት አንዳችም አካል እንደሌለ ገልጻ፤ እንደ ሱዳን ያሉ ሀገሮች ዜጎቻቸውን መታደግ እንደቻሉ በንጽጽር ትናገራለች።
ከምትገኝበት መጠለያ ከሶስት ቃለ መጠይቅ በኋላ መውጣት እንደምትችል ቢነገራትም ለስምንት ወር ያህል ከቦታው መውጣት እንዳልቻለች ትገልጻለች።
"ሁለት ጊዜ ቃለ መጠይቅ አድርጌ ሶስተኛ ነው የቀረሽ ተብዬ ስምንት ወር ሆነኝ" ትላለች።
ጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚደርስባቸው እንግልት የከፋ መሆኑን የምትናገረው እሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም በስልክ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ሌሎች ዜጎች ከማቆያው ወደ ኒጀር እንደተሰደዱና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ከማቆያው እንዲወስዳቸው በሚጠባበቁበት ወቅት ምግብና መጠጥ ማግኘት እንደሚቸገሩም ይናገራሉ።
ያላቸውን ገንዘብ በፖሊሶች እንደተዘረፉ ያገጋገረችን ወጣት ትገልጻለች። "ስልካችንን ወስደውብናል፤ ከሶማሌዎች ተውሰን ነው እናንተንም ማናገር የቻልነው" ትላለች።
በተመሳሳይ መጠለያ ውስጥ የሚገኘው ሌላ ኢትዮጵያዊ "አሁን ራሱ አንዱን ሌላ ቦታ ወስደው እየደበደቡት ነው" ይላል በፍርሀትና በስጋት ተሸብቦ።
እሱም ተመሳሳይ የመደብደብ እጣ እንዳይገጥመው ይሰጋል።
እሱና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ድብደባና ስቃይ እንደበረታባቸው "ያለሁበት ቦታ ለህይወቴ አስጊ ነው" በማለት ይናገራል።
የሚገኙት በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ቢሆንም ከሊቢያ ፖሊሶች ድብደባ እንዳልዳኑ ይናገራል። ሴቶች ይደፈራሉ።
በድብደባው ምክንያት አርግዘው ያስወረዳቸውም አሉ።
ይህኛው ወጣት የተያዘው ከስምንት ወር በፊት ባህር ለማቋረጥ ሲሞክር ነበር። እሱና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ሊቢያ፣ ትሪፖሊ ውስጥ ኢንዛራ የሚባል ቦታ ይገኛሉ።
ሌላ ቢቢሲ ያናገራት ኢትዮጵያዊት ለወራት በመጠለያው ሲቆዩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን መውጣት እንዳልቻሉ ትናገራለች። አንዳንድ ቀን ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው ይቀመጣሉ።
"ወንዶቹን 'ስራ አለ' ብለው ወስደው ይገርፏቸዋል፤ አንዱን ደግሞ የት እንዳደረሱት አናውቅም" ስትል መጠለያው ውስጥ ፖሊሶች መስለው የሚገቡ ደላሎች የሚያደርሱባቸውን ትናገራለች።
ጨምራም"ሊደፍሩን ሲመጡ እየጮህን ከራሳችን ላይ እያስወረድን ነው እንጂ እነሱ በኛ መጫወት ነው የሚፈልጉት" ትላለች።
ደላሎቹ ስደተኞችን ከመጠለያው እያስወጡ ይሸጧቸዋል። ከሊቢያ ወጥተው ባህር ለመሻገር ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅም ያንገላቷቸዋል።
ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከሚገኙበት መጠለያ ሶማሌዎች እየተለዩ ወደ ኒጀር ይወሰዳሉ። ኢትዮጵያውያን ወይም ኤርትራውያን ጥያቄ ሲያቀርቡ ግን ቤት ውስጥ ይቆለፍባቸዋል።
ስደተኞቹ ኒጀር ውስጥ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው በኃላ ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች እንዲሻገሩ ይደረጋል።
የአውሮፓ ሀገራት አምባሳደሮች ወደ ጊዜያዊ መጠለያው ሲሄዱ ስደተኞቹን እንዳያናግሩ እንደሚደረጉ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያኑ "እንድትደርሱልን እንለምናለን" የሚሉትም ለዚሁ ነው።
ስለሁኔታው የጠየቅናቸው ተሰናባቹ የግብጽ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በሊቢያ እየተንገላቱ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለማውጣት መጓጓዣ ሰነድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ሰነዱን ለመዘጋጀት የሚያስፈልግ መረጃ ከቦታው የሚልክ ተወካይ ወይም አስተዳዳሪ አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ።
"ማንነታቸውን የሚገልጽ ዝርዝር ማስረጃ ስለሌላቸው አንጠይቅም። ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ብቻ በቂ ነው" የሚሉት አምባሳደሩ፤ ስደተኞቹ ካሉበት ሆነው ፎቷቸውንና ስማቸውን ከላኩ መጓጓዣ ሰነድ እንደሚያዘጋጁላቸው ተናግረዋል።
"በቦታው ሁነኛ ሰው ስለሌለን በቀጥታ ማግኘት አንችልም፤ የበረሀ ጩኸት ነው የሚሆነው፤ ልንደርሳቸው የምንችለው በምናውቃቸው ሰዎች ወይም ተቋሞች አማካይነት ብቻ ነው" ይላሉ።

No comments