Latest

የሶማሌ (ጅግጅጋ) ጉዳይ - በጌታቸው ሽፈራው

የሶማሌ (ጅግጅጋ) ጉዳይ - በጌታቸው ሽፈራው

ቅዳሜ ሀምሌ28/2010 ዓም ከጠዋት ጀምሮ በጅግጅጋ፣ ቀብሪዳህር፣ ዋርደር፣ ደሃቡር፣ ከተሞች አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ላይ ዘረፋና ደብደባ ተፈፅሟል። በርካታ ቤተ ክርስትያኖች ወድመዋል። ከእነዚህም መካከል፦ 

~ ዋርደር ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል
~ ቀብሪዳሀራ ቅድስት ማርያም
~ ደገሃቡር ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ንብረታቸው ተዘርፏል።

ጅግጅጋ ውስጥ 
ቅዳሜ :

~ የቅድስት ኪዳነ ምህረት ካቴድራል፣ ቅድስት አርሴማ፣ ደብረ ብስራት ጊዮርጊስ ንብረታቸው ተዘርፎ ወድመዋል።
~ የቅድስት አርሴማ አገልጋይ ቄስ አብርሃም ተገድለዋል፣ ከአንገታቸው በላይ ተቃጥለዋል።
~ ቅድስት ኪዳነ ምህረት መነኩሴ አባ ገ/ማርያም ተገድዋል። አባ ገ/ማርያም የ70 አመት መነኩሴ ናቸው።
~ የቅድስት ኪዳነ ምህተት የመፅሃፍ መምህር ቄስ ጌራ ወርቅ በተመሳሳይ ተገድለዋል። ሶስቱም ላይ ብዙ ጭካኔዎች ተፈፅሞባቸዋል።

~ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ በአጠቃላይ ደግሞ ከሶማሊ ውጭ የሆኑ ዜጎች ንብረት ወድሟል። የመኪና መለዋወጫ፣ የልብስ መሸጫ ቡቲኮች፣የኤሌክትሮኒክስ መሸጫ፣ የመዋቢያ ቁሳቁሶች መሸጫ፣ የህንፃ መሳርያ መሸጫ፣ ዳቦ መጋገሪያ፣ቡና ቤቶች፣ ምግሽ ቤቶች፣ ላውንጅች፣ ሆቴሎች፣ ፔልሲዮኖች ተዘርፈው፣ተቃጥለዋል። የፍራፍሬና አርክልት መሸጫ (ጉሊቶች) መጋዘኖች ተዘርፈው። 

~ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ኦሮሚያ ህብረት ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ሌሎች ተቋማት ዘረፋና ጥቃት ደርሶባቸዋል።

~ ባለፉት ሁለት ቀናት ከተገደሉት በተጨማሪ ዛሬ 7 ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል። አራቱ መሰረተ ክርስቶስ የሚባል የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስትያን አካባቢ፣ እንዲሁም 3ቱ ምስራቅ ድል ትምህርት ቤት (በነዋሪዎቹ አጠራር ግራኝ ማህመድ ትምህርት ቤት) አካባቢ ተገድለዋል ተብሏል። አራት ግለሰቦች ቆስለዋል ተብሏል።

~ ቅዳሜ እና እሁድ የአማራ፣ ኦሮሞና ጉራጌ እንዲሁም በሌሎች መኪናዎች ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ታውቋል። በመኪና ሆነው "ሄጎ" እያሉ በመጨፈር፣አብይ አህመድ ይውረድ፣ ለማ መገርሳ ይውረድ፣ ገዱ አንዳርጋቸው ይውረድ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ከሶማሊ ይውጣ የሚል መፈክር ማሰማታቸውም ተገልፆአል። ለአብዲም ድጋፍ እንዳላቸው በመግለፅ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በማውረድ የ"ታላቋ ሶማሊያን") ሰንደቅ አላማ፣ እና የሶማሊያን መዝሙር ሲዘምሩ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። የቀበሌ አመራሮችም ድጋፍ ሲሰጡ እንደነበር ተገልፆአል።

~ ትናንት አብዲ ኤሌ ከቀኑ 7 ሰዓት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስያን ሄዶ ለማነጋገር ሞክሯል። ሕዝብ "ሌባ ሌባ፣ ውሸታም ውሸታም" እያለ ጩኸት ሲያሰማ ተመልሷል። 10 ሰዓት አካባቢ ቀሳውስት አብዲን ማናገር እንዳለባቸው ሲመክሩ ወጣቶ እንዳይሄዱ አስጠንቅቋል። ዛሬ 3 ሰዓት ላይ 45 ደቂቃ ያህል ቀሳውስቱ ጋር ተወያይቷል።

~ አብዲ ለችግሩ ተጠያቂ እንዳልሆነ ተናግሯል። ለዚህምም 1ኛ) "ጅግጅጋ ውስጥ ሰውን የዘረፉ፣ ወንጀል የሰሩርን አስሬ የነበር ቢሆንም በፌደራል መንግስቱ ትዕዛዝ የፖለቲካ እስረኛ ተብለው ተፈትተዋል፣ እነሱ ናቸው የሚበጠብጡት" ብሏል

~ ቤተ ክርስትያን የሚያቃጥሉት አክራሪዎች እና የኦብነግ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው" በሚል በድርጊቱ እንደሌለበት ገልፆአል ተብሏል። ቤተ ክርስትያን ተጠልለውና ለሶስት ቀን ምግብ ሳይቀምስ ፆሙን ለሚገኘው ሕዝብም "ምግብ ይመጣላችኋል" ብሎ ተመልሷል። ሆኖም ምግብ እንዳልሄደላቸው ተገልፆአል።

~ ሕዝቡ ቅዱስ ሚካኤል እና የፕሮታንቶቹ መሰረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስትያን ተጠልሎ የሚገኝ ሲሆን ሶማሊ ያልሆኑ ሙስሊሞች ቤተ ክርስትያን ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

~ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቅዳሜ 5፣30 እና ወደማታ አካባቢ ሰኢድ መሃመድ ሀውልት አካባቢ ታይተው እንደነበር ተገልፆአል። አብዲ ኤሊ ዛሬ ለቀሳውስት ባደረገው ንግግር ቅዳሜ ዕለት መከላከያ ሰራዊት ስለገባ ነው ችግሩ የተባባሰው ማለቱ ተገልፆአል።

(ጥንቅሩ ጅግጅጋ ከሚገኙ ዜጎች በስልክ የተገኘ ነው)

No comments