Latest

በመተማ መሬት አጼ ዮሐንስ- ሕይወቱን፣ አቶ ደመቀ- ማንነቱን… (አሳዬ ደርቤ)

በመተማ መሬት አጼ ዮሐንስ- ሕይወቱን፣ አቶ ደመቀ- ማንነቱን… (አሳዬ ደርቤ)

የመተማ መሬት ሲነሳ ከሁሉም አስቀድሞ ወደ ጭንቅላታችን የሚመጣው ስም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን ነው፡፡ ምክንያቱም ከረዥም ዓመታት ጀምሮ የመተማን መሬት ከሱዳኖች ጋር ተፈራርሞ ‹ሽጦታል› እየተባለ ይወራ ነበር፡፡  

ወሬው ደግሞ በአሉባልታ መልክ ሲናፈስ የነበረ ሳይሆን በእርግጠኝነት ሲሰራጭ የኖረ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአቶ ደመቀ ስም ጥላሸት የደፈደፈበት ሊሆን ችሏል፡፡ በተለይ አማራ ክልል ላይ ሰውዬውን እንደ መሪ ቀርቶ እንደ ሰው የሚቆጥረው አልነበረም፡፡ ከዚህም አልፎ የአቶ ደመቀ የጠለሸ ስም በብአዴንም ላይ ሲያንዣብብ ኑሯል፡፡

ይሄም ሆኖ ግን… የስም ማጥፋት ዘመቻው በአፈ-ታሪክ እንጂ በሰነድ የታገዘ አልነበረም፡፡ መሬቱ ‹ለሱዳኖች ተሰጠ› በተባለበት ዓመተ-ምህረት አቶ ደመቀ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡ ይሄውም ስልጣናቸው የአገራችንን መሬት በፊርማቸው ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የሚያበቃ ባይሆንም… እንደ ዜጋ አሉባልታውን ለማስፋፋት እንጂ ለማጣራት የሞከረ አልነበረም፡፡  

ጆርጅ ኦርዌል መጽሐፍ ላይ እንዳሉት እንስሶች ‹‹ኢህአዴግ አስማሚ፣ ደመቀ ፈራሚ›› የሚል መዝሙር ሸምድደን ስናቀነቅን ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ አቶ ደመቀ ለባለፉት ዓመታት በተነዛባቸው ‹‹የበሬ ወለደ›› አሉባልታ ተቀባይነታቸውን ብቻ ሳይሆን ነጻነታቸውንም አጥተው ኖረዋል፡፡

ለምሳሌ ያህል- ባንድ ወቅት ከእነ ካሳ ተክለብርሐንና ከእነ ህላዌ ዮሴፍ ጋር ዲያስፖራውን ሊሰበስቡ ውጭ አገር በሄዱበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ‹ውርደት› ማንሳት ይቻላል፡፡ በወቅቱ አዳራሹ ውስጥ የተገኙት ዲያስፖራዎች አቶ ደመቀን ‹‹የመተማን መሬት የሸጥክ ሌባ እኛን ለመሰብሰብ ወደ ካናዳ ስትመጣ አለማፈርህ›› እያሉ ሲሞልጩት የሚያሳይ ቪዲዮ ዪ-ቲዩብ ላይ ተጭኖልን ነበር፡፡

እናም በጊዜው አገራችን ላይ በነበረው አፈና የተነሳ የልባችንን መናገር የማንችል ‹ጭቁን ዜጎች› አቶ ደመቀና ጓዶቹ የተሸማቀቁበትን ቪዲዮ በብሉ-ቱዝ እየተቀባበልን በማየት የተቃጠለ አንጄታችንን ቅቤ ለማጠጣት ሞክረናል፡፡
ከዚህ ባለፈ ደግሞ ሰውዬው ከክልሉ ተነስቶ በትምህርት ሚኒስቴርነት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ… በአገር ሻጭነቱ እንጂ በብቃቱ ወደ ፌደራል እንደመጣ የሚያስብ አልነበረም፡፡ ሁላችንም ደምድመን የነበርነው በፊርማው መሬቱን ለሱዳኖች አሳልፎ በመስጠቱ እድገት እንደተሰጠው ነው፡፡

ከአምስት ወር በፊትም ለአገራችን ጠቅላይ ሚኒስቴርነት እጩ ሆኖ ሲቀርብ የተሳለቀበት እንጂ የተስማማበት አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን የሰውዬውን ንጹሕነት የሚያውቀው ድርጅቱ እጩ አድርጎ ቢያቀርበውም የክልሉ ህዝብ ግን ‹‹መተማን ሽጦ የሄደ ሰው ለአገር መሪነት ሲወዳደር ትንሽ እንኳን ሼም አይዘውም?›› እያለ ሲነጋገር ነበር፡፡

ደግነቱ አቶ ደመቀም እራሱን ከምርጫው በማግለል ለዶክተር አቢይ መመረጥ ታላቅ አስተዋጽኦ አደረገ፡፡
በማስከተልም….. አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በቆሙበት መድረክ ላይ ሁሉ ‹‹ከጀርባ ሆኖ ለውጡን የሚሾፍር ታላቅ ሰው›› እያሉ ምክትላቸውን ሲያወድሱት፣ የጠለሸ ስሙን ለማንጻት የሚጣጣሩ እንጂ እውነቱን የሚናገሩ አይመስለንም ነበር፡፡
.
አሁን ግን ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል›› እንደሚባለው በያዝነው ሳምንት ‹ኢሳት› ይፋ ያደረገው ሰነድ ‹ደመቀ ሌላ፣ መታወቂያው ሌላ› መሆኑን በግልጽ ያወጣ ሁኗል፡፡ ይሄውም ለባለፉት አስር ዓመታት አቶ ደመቀ ባልፈረመውና በማያውቀው ሰነድ ስሙ ሲጠፋ መኖሩን የገለጸ ነው፡፡

እኛም ስሙን ስናብጠለጥል የኖርን ዜጎች አጼ ዮሐንስ ሕይወታቸውን ባጡበት የመተማ መሬት ላይ አቶ ደመቀ ማንነቱን አጥቶበት እንደኖረ ባወቅን ጊዜ በእጅጉ አፍረናል፡፡ ሰነዱ የአቶ ደመቀን አንገት ቀና ሲያስደርግ… የእኛን አንገት አስደፍቷል፡፡

ጭራሽ ባሳለፍናቸው በአፈና የተሞሉ ዓመታት…. እኛ አቶ ደመቀን የምንሳደብበት መድረክ እንዳጣነው ሁሉ… እሳቸውም ያለስራቸው የሚሰደቡበትን ጥፋት የሚያስተባብሉበት መድረክ ተነፍገው መኖራቸውን ስንገነዘብ… እፍረት ብቻ ሳይሆን እዝነትም ተሰምቶናል፡፡

ለነገሩስ ‹‹የጸረ-ሽብር ግብረ-ሐይሉን›› የሚመራ ሹም በአሸባሪነት ተሰማርቶ በሚገኝባት አገር ላይ… ንጹህ ሰዎች የሌላውን እድፍ ተሸክመው መኖራቸው የሚገርም አይደለም፡፡ በእንዲህ ያለ ዘግናኝ ስርዓት ውስጥ የገባ ሰው… ያለግብሩ የሚደረብበትን ካባ ለማስተባበል ቢሞክር… የአቶ ታምራት ላይኔን እጣ-ፈንታ ከመጋት የዘለለ ፋይዳ አያመጣም፡፡  

ስለሆነም ለባለፉት ዓመታት አቶ ደመቀ በግዳጅ ከተሰጣቸው ስም ጋር ተስማምተው መኖራቸው ከንጹሕነታቸው ባለፈ ጥንካሬያቸውንም የሚገልጽ ሲሆን ይሄም ሁኔታ በንቄት ፈንታ አድናቆታችንን እንድንሰጥ አስገድዶናል፡፡
.
ሃሳቤን ሳጠቃልለው… የተደበቀው እውነት ዘግይቶ ቢወጣም አቶ ደመቀ በሕይወትና በሹመት ላይ ያሉ መሆናቸው እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህም በአባይ ፊርማ አቶ ደመቀን ስናማ መኖራችን የሚያስቆጭ ቢሆንም ከልባችን ይቅርታ ለመጠየቅና የነፈግናቸውን አድናቆት ለመለገስ ግን ጊዜው ይፈቅድልናል፡፡

እናም ይሄን ለመልካም ስራ እንጂ ለመልካም ስም የማይጨነቅ፣ ለድርጊት ካልሆነ በቀር ‹እዩኝ፣ እዩኝ› ለማለት ጠብ-እርግፍ የማይል ‹‹የተግባር ሰው›› ለባለፉት አስርት ዓመታት ስሙን ሳመነዥክ በመኖሬ በግሌ የተሰማኝን ጸጸት እየገለጽኩ ይቅርታ እንዲያደርግልኝ እለምነዋለሁ፡፡ 

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ሌሎቻችሁም ይቅርታ ልትጠይቁት እንደሚገባ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡

No comments