Latest

የአረናና የህወሃቶች የዘር ቅስቀሳ (ጋዜጠኛ አበበ ገላው)

የአረናና የህወሃቶች የዘር ቅስቀሳ

አረናና ህወሃት ሰሞኑን የተቀነባበረ የዘር ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው። የጣና በለስ ፕሮጄክት ሁለት የትግራይ ተወላጆችና አንድ ኤርትራዊ ላይ ዘርን ያነጣጠረ ግድያ ተፈጸመ ብለው ሃሰተኛ የሆነ ዜናና ምስል በማሰራጨት ብቻ አላበቁም።

የአረናው ሊቀመንበር አብረሃ ደስታ በፌስቡክ ገጹ ላይ “በአማራ ክልል ከተገደሉ ሦስት ተጋሩ አንዱ ኤርትራዊ መሆኑ ተረጋግጣል። ስለዚህ በትግርኛ ተናጋሪዎች ላይ የተቃጣ ጥቃት መሆኑ ግልፅ ነው። “ በማለት ሃላፊነት የጎደለው የዘር ቅስቀሳ አሰራጭቷል።

አብረሃ ጉዳዩን ለጠጥ አርጎ “አንሸወድ! ፀረ ህወሓት ሳይሆን ፀረ ትግራይ ህዝብ የታወጀ ጦርነት ነው።” በማለትም የዘር ግጭት ለመቀስቀስ መሞከሩ አረና ሃላፊነት በጎደለው ግለሰብ መመራት ብቻ ሳይሆን ከህወሃት ወደ ባሰ የጥፋት አቅጣጫ እያመራ መሆኑን ግልጽ ያደርጋል።

የትግራይ ክልል የኮሚውኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ የሚከተለውን የተሳሳተ መግለጫ ሀምሌ 24 በማውጣት በሚዲያ ተቋማት በስፋት እንዲሰራጭ አድርጓል።

“በኣማራ ክልል በጣና በለሰ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ሀምለ 22/ 2010 ዓ/ም ላይ በተፈፀመው ብሔር መሰረት ያደረገ ጥቃት በሁለት የትግራይ ተወላጅ እና ኣንድ ኤርትራዊ ተወላጅ መሞታቸውን ተረጋግጧል፡፡ ሰለሆነም ኣሁን እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት በትግራይ ተወላጅ ብቻ ሳይሆን በትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑ ነው፡፡”

ይሁንና የስኳር ኮርፖሬሽን ዛሬ ለሸገር ሬድዮ በሰጠው መግለጫ ፣ በጣና በለስ ፕሮጀክት በተቀሰቀሰ ግጭት ሶስት ሰዎች ሞተዋል ፣ የተባለው ወሬ ውሸት መሆኑን ዕወቁልኝ ብሏል። በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ፣ ጃዊ ወረዳ ፣ ፈንደቃ ከተማ ፣ በቀብሩ እለት መብራት የጠፋው ሆን ተብሎ ነው በሚል መነሻ በተቀሰቀሰው ረብሻ 3 ሰዎች መሞታቸው የስኳር መሞታቸውን ኮርፕሬሽኑ ገልጿል።

በዘገባው መሰረት ግጭቱ የተነሳውና የሞቱትም ሰዎች የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ናቸው ተብሎ መነገሩ ሀሰት ነው፡፡

“ግጭቱ የተነሳበት ፈንደቃ ከተማ ከፕሮጀክቱ በሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝና የሞቱትም የፕሮጀክቱ ሰራተኞች አለመሆናቸውን የተናገረው ስኳር ኮርፖሬሽን ሰራተኞቼ ፣ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የመጡና ተቻችለው ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩ ናቸው ብሏል፡፡”

በመግለጫው መሰረት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ በነበሩት የአቶ ስመኘው በቀለ ፣ የቀብር ሥነ፡ሥርዓት በተፈፀመበት ቀን መብራት በመጥፋቱ በፈንደቃ ከተማ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር፡፡

እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ አረናና ህወሃት ያለምንም ማጣራት የተራ ግጭት አሳዛኝ ክስተትን ወደ ዘር ግጭት ከፍ ለማድረግ ተቀናጅተው መስራታቸው ዛሬም የዘረኝነትን ካርድ ለፖለቲካ ቁማር ማዋል ለከፋ ኪሳራ መዳረጉን መገንዘብ ይገባቸዋል።

አንድ ሰው ላይ ወንጀል ሲፈጸም መርማሪዎች ለምን እና እንዴት መሆኑን ያጣራሉ እንጂ የፖለቲካ አላማ ያላቸው ቁማርተኞች ከሩቁ ያለምንም ማጣራት ለራሳቸው እኩይ አላማ ከዘር ጋር እያያዙ ከተጠቀሙበት አደጋው የከፋ ነው። ሃላፊነት የሚሰማው አመራር ግጭት ይከላከላል እንጂ ግጭት አይቀሰቅስም። ህወሃቶችና አረናዎች መሪ አልባ በመሆናቸው የያዙት አቅጣጫ የጥፋት ነው።

No comments