Latest

ኦህዴድ እና ብአዴን፤ አቅማቸዉን ያባከኑ ታላላቅ ሃይሎች! (ታዬ ደንደኣ)

ኦህዴድ እና ብአዴን፤ አቅማቸዉን ያባከኑ ታላላቅ ሃይሎች! (ታዬ ደንደኣ)

የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያንስ 70% ይሆናል። በኢትዮጵያ ፓርላማ ኦህዴድ 190 አባላት አሉት። ብአዴን ደግሞ 150 የሚጠጋ አባላት አሉት። በድምሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ተወካዮች 340 አከባቢ ናቸዉ። ይህ በፓርላማዉ እጅግ በጣም ወሳኝ ድምፅ ነወ።  


ብአዴን እና ኦህዴድ ቢተባበሩ ፓርላማዉ የሚያወጣዉን ህግ መቆጣጠር ይችላሉ። ሁለቱ ድርጅቶች ያልደገፉት ረቂቅ አዋጅ ሊፀድቅ አይችልም። ሁለቱ የፈለጉትን ረቂቅ አዋጅ ደግሞ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቅ ይችላሉ። ስለዚህ ለኢትዮጵያ የዴሞኪራሲ መቀጨጭ ተጠያቂ መሆን ያለበት ሌላ አካል ሳይሆን ኦህዴድ እና ብአዴን ናቸዉ። ሁለቱ ሀይሎች ተባብረዉ ለኢትዮጵያ ዴሞኪራሲ እና ልማት ከመሥራት ይልቅ እርስ-በእርስ በመፈራራት አምባገንነት እና ድህነት በኢትዮጵያ ምድር እንድሰነብት አድርጓል።

በእርግጥ በአማራ እና በኦሮሞ ህዝቦች መሃከል ከፍተኛ ሴራ ተሸርቧል። የሁለቱ ህዝቦች ጠላት አማራ እና ኦሮሞ መቼም ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ እንደላቸዉ አድርጎ በመሳል በሁለቱ መሀከል መፈራራት እንድነግስ አድርጓል። ኦሮሞ ጠባብ ሲባል አማራ ደግሞ ትምክህተኛ ተብሎ ተፈርጇል። 

የሁለቱ ህዝቦች የጋራ ባላንጣ ሁለቱን በማጋጨት ቁማር ሲጫወት ኖሯል። “እኛ ባንኖር አማራ ከምድረ-ገፅ ያጠፋችሁ ነበር” ያሉኝ ወገኖች አሉ። እነዚሁ ወገኖች “ኦሮሞ እንዳይፈጃችሁ ያደረግነዉ እኛ ነን” ብለዉ እንደነገሩት አንድ አማራ ጓደኛዬ ነግሮኛል።

አማራ ያለፈዉን ሥርዓት ይፈልጋል ተብሎ ለኦሮሞ ይነገራል። ነገር ግን ይህ ፈፅሞ ሊታሰብ የማይችል ሃሰት ነዉ። የፊዉደል ሥርዓት ዳግም ላይመለስ ሞቶ ተቀብሯል። ስለዚህ የአማራ ልሂቃን በ21ኛ ክፍለ ዘመን በራሱ ጊዜ አርጅቶ የሞተዉን የፊዉዳል ሥርአት የመመለስ ህልም አላቸው ማለት በራሱ ከባድ ስድብ ነዉ። ጤነኛ አዕምሮ ያለዉ አማራ ይህን ሊያስብ አይችልም። ያንን የሚፈልግ ሞኝ እንኳን ቢኖር አሁን ባለንበት ሁኔታ ፍላጎቱ የቀን ቅዠት ነዉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞ ሀገር ለመገንጠል እና አማራን ሊበቀል ይፈልጋል በማለት ለአማራ ይተረካል። ይህም እዉነት አይደለም። ከግፍ ብዛት መገንጠልን እንደ አማራጭ የሚያስቡ ወገኖች ቢኖሩም መብቱ እና ጥቅሙ በአግባቡ የተከበረለት ኦሮሞ መገንጠል አይፈልግም። እንኳን ኢትዮጵያ አፍሪካ በሙሉ አንድ ሀገር ቢሆን ኦሮሞ ይፈልጋል። 

ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት ወቅት መለያየት ለማንም አይበጅም። ስለዚህ “ኦሮሞ ሀገር ሊገነጥል ነዉ” የሚለዉ ማስፈራሪያ ህዝቦች እንዳይተማመኑ ለማድረግ የተሸረቤ ሴራ ነዉ። ከስንት ዘመን በፊት ለተከሰተ በደልም ዛሬ ላይ ስለበቀል ማሰብም ኋላቀርነት ነዉ። አማራም ሆነ ሌላ ብሔር በዚህ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሊሰጋ አይገባም። በሆነ ተዓምር ኦሮሚያ ብትገነጠል እንኳን የሚፈጠር ችግር የለም።  

መገንጠል ማለት የአስተዳደር ድንበር መለየት እንጂ መሬቱን ነቅሎ ወደ ኤሲያ ወይም አዉሮፓ መዉሰድ አይደለም። ጀርመን እና ፈረንሳይ የተለያዪ ሀገሮች ቢሆኑም በአንድነት መኖር አላቃታቸዉም። ዋናዉ ጉዳይ ከተንኮል እና ከሸፍጥ በፀዳ መልኩ ለጋራ ጥቅም በቅንነት መሥራት ነዉ።

ባለፉት ዘመናት በአማራ እና በኦሮሞ መሃከል ግጭቶች ነበሩ። በግጭቱ ወቅት በደሎች ተፈፅሟል። ይህ እዉነት ነዉ። ይህ እዉነት በራሱ ችግር አይደለም። ችግሩ በዚያ ዙሪያ የተፈጠረዉ የተዛባ አመለካከት ነዉ። አንዳንዶች ታሪካዊ ክስተቶችን በማጋነን አማራ እና ኦሮሞ ሊታረቁ የማይችሉ የዘላለም ጠላቶች እንደሆኑ ይሟርታሉ። ያልነቁ ወገኖች ደግሞ ይህን ሟርት በማመን የጠላት መጠቀሚያ ይሆናሉ።  

ባለፉት ዘመናት የተፈፀሙ ግፎችን የሚክዱ የአማራ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ የተፈፀመዉን ግፍ ወደ ጫፍ በመዉሰድ ሁለቱ ህዝቦች አንዳይተማመኑ የሚለፉ የኦሮሞ ወገኖች አሉ። ሁለቱም ወገኖች እንወክላለን የሚሉትን ህዝብ የጠቀሙ መስሏቸዉ የህዝባቸዉን የሰቆቃ ዘመን እያራዘሙ ነዉ። መፍትሄዉ በታሪክ እዉነታዎች ላይ መነታረክ ትቶ የወደፊቱን በማየት በሃቅ እና በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ አንድነት መገንባት ነዉ።  

ከ150 ዓመት በፊት በነበሩ ሟች እና ገዳይ ላይ ስንከራከር ዛሬ ላይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የበረሃ እና የባህር አዉሬ ቀለብ እየሆኑ ነዉ። ወደፊት ደግሞ እጅግ የባሰ ችግር ሊመጣብን ይችላል። ስለሆነም አማራ እና ኦሮሞ በአጠቃላይ ፥ ኦህዴድ እና ብአዴን ደግሞ በተለይ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተባብረዉ መሥራት አለባቸዉ።

ኢትዮጵያን ለመቀየር ብአዴን እና ኦህዴድ ትልቅ ህጋዊ አቅም አላቸዉ። ይህ አቅም ግን ለ26 ዓመታት በከንቱ ባክኗል። ላለፈዉ አሁን ማልቀስ ጥቅም የለዉም። ዋናዉ ነገር ከዚህ ጀምሮ በትክክል አቅሙን በመገንዘብ መጠቀም ነዉ። ከምንም በላይ መከባበር የችግሮች መፍትሔ ነዉ። ብንከባበር እና ለጋራ ጥቅም ከሠራን የሚያጣላን ምድራዊ ሀይል የለም። ኦሮሞ እንደ ህዝብ የራሱ ፍላጎቶች እና ጥቅሞች አሉት።  

የአማራ ህዝብ ይህን ማመን እና ማክበር አለበት። አማራም በዝያዉ ልክ የራሱ ፍተሃዊ ፍላጎቶች አሉት። የኦሮሞ ህዝብ ያንን አዉቆ ማክበር አለበት። ከሁሉም በላይ ደግሞ “እኔ አዉቅልሀለሁ” የሚል ፈሊጥ መቆም አለበት። በደፈናዉ “አንድ ነን” ማለትም አይሰራም። በቅንነት መነጋገር ያስፈልጋል። 

ይህ ከሆነ አማራ እና ኦሮሞ የማይተባበሩበት ምንም ምክንያት የለም። ሁለቱ ታላላቅ የኢትዮጽያ ህዝቦች ከተባበሩ ደግሞ የማይፈቱት ችግር አይኖርም። ብአዴን እና ኦህዴድ በቅንነት እና በብስለት የሚመሩትን ህዝቦች በማስተባበር ዘርፈ ብዙ የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት መሥራት አለባቸዉ። ይህ የሁለቱ ድርጅቶች ታሪካዊ ሀላፊነት ነዉ። የራስን መብት መጠየቅ የሌላዉን መብት መድፈር አይደለም። የህዝቦች ትብብር ይጠንክር!

ማስታወሻ

ይህ ፅሑፍ በዚህ “የኦሮማራ” ትብብር መድረክ ባህርዳር ላይ ከመጀመሩ በፊት የተፃፈ ነው፡፡ የፅሁፉ ዓላማ በሀገራችን የዴሞክረሲ፣ የልማት እና የሠላም ምኞት ያልተሳካዉ በአማራ እና በኦሮሞ መሃከል በተሸረበዉ ሴራ ምክንያት መሆኑን ለማሳየት እንጂ የሌሎች ብሔረ-ሰቦችን ሚና ለማሳነስ አይደለም። 

በሀገራችን እኩልነት፣ ነፃነት፣ የህግ የበላይነት እና ፍተሃዊ ተጠቃሚነት እንድረጋገጥ የሁላችን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አምናለሁ። አመሰግናለሁ!

No comments