Latest

የለውጥ ግስጋሴው ግቡን ይመታ ዘንድ… (ጠገናው ጎሹ)


ከሁሉም በፊት የርዕሰ ጉዳዬን ኀይለ ቃሎች ግልፅ ላድርግ ።

የለውጥ ግሥጋሴ ስል ዶ/ር አብይንና መሰል ጓዶቻቸውን በውዴታ ግዴታ ከለውጥ ደጋፊነት (አራማጅነት) አሁን ወደ አሉበት ከፍተኛው የሥልጣን ደረጃ ላይ ያደረሳቸውን የህዝብ የነፃነት ፣የፍትህ ፣ የሰብአዊ መበት (ክብር) ፣ የእኩልነት ፣ የዘላቂ ሰላም እና የብልፅግና ተጋድሎ ማለቴ እንጅ የገዥው ቡድን ፖለቲከኞች በራሳቸው ተነሳሽነትና አነሳሽነት ከህዝቡ ቀድመው ፣ ፈጥረውና አመቻችተው ለመሪነት የበቁበት የለውጥ ሂደት ነው ማለቴ አይደለም።

የሩብ ምዕተ ዓመቱ የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት በለመደው መንገድ ጨርሶ መቀጠል እንደማይችል ቁርጡን ሲያውቅ ከእራሱ የወጡ ፖለቲከኞች ለውጡን ከመደገፍ አልፈው መሪዎቹ የመሆናቸው አጋጣሚ ከፈጠረብን ልጓም አልባ ስሜታዊነትወጥተን ገንቢ በሆነ ሂሳዊ አመለካከት ( critical and constructive way of thinking) የመነሻችን፣ የሂደታችንና የመዳረሻችን ምንነትና እንዴትነት በአግባቡ ለመረዳት ካልተሳነን በስተቀር እውነቱ ይኸው ነው።

በሌላ አገላለፅ የአያሌ ዘመናት የነፃነትና የፍትህ እጦት ሰለባ ሆኖ የዘለቀው እና በተለይ ደግሞ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በዘር አጥንት ቆጠራና በቋንቋ ልዩነት ላይ በተመሠረተ የፖለቲካ እብደት ምክንያት መግለፅ የሚያስቸግር የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸክሞ የኖረው የዋህና ምስኪን የአገሬ ህዝብ ዶ/ር አብይንና መሰሎቻቸውን በውዴታ ግዴታ (willingly or otherwise) ከለውጥ ደጋፊነት ወደ የፊት ለፊት መሪነት እንዲወጡ አደረገ እንጅ ከእነሱ ተጠንስሶና ተወልዶ ወደ ህዝቡ የሰረፀ የለውጥ ሂደት አለመሆኑን በአግባቡ መረዳት ቀላል የሚመስል ግን ቀላል ያልሆነ ጠቀሜታ ያለው (የሚኖረው) ስለመሆኑ የሚያጠያይቀን አይመስለኝም ። 

 ወደ ኋላው ይበልጥ ግልፅ የማደርገው ቢሆንም ከጠቀሜታዎቹ አንዱ ክፉ ሥርዓቶች (አገዛዞች) ከሚያደርሱብን እጅግ የከፋ በደልና ግፍ የተነሳ ከዚህ ለመውጣት በምናደርገው ግብ ግብ (ተጋድሎ) ሂደት ውስጥ የምናገኛቸውን መሪዎች እንደ እኛ ሊያለሙና ሊያጠፉ የሚችሉ ሰብአዊ ፍጡሮች እስከማይመስሉን ድረስ አምልኮ (cult) በመፍጠር “እኛ ከሌለን የሚፈታ ፈተና የለም” የሚል የፖለቲካ ሰብእና ሰለባ እንዳይሆኑ ለማገዝና ለመቆጣጠር የሚያስችለን መሆኑ ነው።

ይህ ፈፅሞ አይሆንም የሚል አስተያየት እንደሚኖር እገምታለሁ ። መኖሩም የሚገርም አይደለም ። ነገር ግን የሰው ልጅ እጅግ ውስብስብ ባህሪና ከቶውንም ወሰን የሌለው ዝና ፈላጊነቱ (excessive self-importance /self-aggrandizment ) እንኳንስ እንደ እኛ ባለ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እጅግ በተሻለ ደረጃ ላይ በሚገኝ ማህበረሰብ ውስጥም ሊያጋጥም የሚችል አስቀያሚ እውነታ ነው ። 

በማይናወጥ መርህና ህግ በሚመራ ሥርዓት ተገቢውን የመቆጣጠሪያ መካኒዝም (ስልት/ዘዴ) ካላበጀንለት በስተቀር አይሆንም ብሎ ማሰብ የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ እውነታ ነፀብራቅ አይደለም ።

በሌላ በኩል ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩና በህዝባዊ የለውጥ መስመር ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ጓዶቻቸው ለሩብ ምዕተ ዓመት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ንቁ ተሳታፊዎች ሆነው ከዘለቁበት የመከራና የውርደት ሥርዓት በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ተፀፅተውና የተፈፀመውን ግፍና በደል “ከእንግዴህ ይበቃል” በማለት የለውጡን ግሥጋሴ በመሪነት ደረጃ ለማስተባበር ያሳዩት የፖለቲካና የሞራል ድፍረት (ወኔ) ለዛሬው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ስኬታማነት ብቻ ሳይሆን ከፊት ለፊታችን ለሚጠብቀን አዲስና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም የሚኖረው አወንታዊ አስተዋፅኦ (ተፅዕኖ) እጅግ ከፍተኛ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም ።

ስህተት ወይም ችግር የሚሆነው የለውጡን አቅጣጫ ትክክለኛነት ወይም መሳሳት እና የግቡን እውን መሆን ወይም አለመሆን ለአንድ መሪ ጠቅልለን ስናሸክመው (ስናሸክማት) እና ከገሃዱ ዓለም (ከውስብስቡና ፈታኙ እኛነታችን) ውጭ በእነዚሁ መሪዎች አማካኝነት የሚመጣ ውጤት ይኖራል እስከሚልና መሪዎችን ጨምሮ የልዩ ፍጡርነት ስሜት (false or wrong self-perception) ሰለባ እንዲሆኑ ስናደርግ ነው ። 

የአሁኑ የፖለቲካ እውነታና “የለውጥ አራማጅ” መሪዎች ሁኔታ የተለየ እንደሆነ በሚገባ ብገነዘብም የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ወደንም ሆነ ፈርተን “ያመለክናቸውና የምናመልካቸው” መሪዎች ደሃ አይደለም። ለዚህ ነው በህዝባዊው የለውጥ ሂደት ውስጥ የተካተቱን ተዋንያን (መሪዎችን ጨምሮ) በሩብ ምዕተ ዓመቱ የመስዋዕትነት ትግል በጎመራውና ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ በፍጥነትና በከፍተኛ ስሜት በመንፈስ ላይ ካለው የለውጥ ነፋስ ጋር በሰከነ መንፈስና አእምሮ መከታተልና ተገቢውን ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው ።

ሁለተኛው የርዕሰ ጉዳዬ ኅይለ ቃል ወይም ፅንሰ ሃሳብ ግብ (goal) የሚለው ነው። ከረጅሙ የዴሞክራሲዊና የሰብአዊ መብት አልባ የፖለቲካ ታሪካችንና እና በተለይ ደግሞ ከሩብ ምዕተ ዓመቱ የማንነት አጥንት ቆጠራንና የቋንቋ ልዩነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ካስከተለው መከራና ውርደት ለመውጣት የተከፈለውና እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት ግቡ (እጣ ፈንታው) በማያወላዳ አኳኋን ግልፅና ግልፅ መሆን አለበት። 

ከዘመናት የመከራና የውርደት የፖለቲካ ሥርዓት ለመውጣት በእውን የምንፈልግ ከሆነ የዚህ ህዝባዊ የለውጥ ግሥጋሴ ግቡ (መዳረሻው) በዴሞክራሲያዊ ሽግግር መሸጋገሪያነት አዲስና አስተማማኝ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትና ማጎልበት እንጅ በህወሃት/ኢህአዴግ የለውጥ “ምቹ ሁኔታ ፈጣሪነት” በሚካሄድ የምርጫ ቁማር ለመጫወት አለመሆኑን ከምር አለመረዳትና ለዚሁም በሰለጠነና በማይናወጥ መርህ ላይ የተመሠረተ ትግል አለማድረግ የሚያስከትለውን ውጤት አስከፊነት አለመረዳት ወይም ምን አገባኝ ባይነት ነው ።

ከእነዚህ እንደ መግቢያ ካነሰኋቸው ጉዳዮች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተያያዥ የሆኑ አንዳድ ጉዳዮችን እንደሚከተለው ልጨምር ፦
ከዓመታት የግፍ እሥረኛነት በቅርቡ የተፈቱትና በባህርዳሩ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ (ሰኔ 24/2010) ላይ ተናጋሪ ከነበሩት አንዷ ወ/ሮ እማዋይሽ እንዳሉት የለውጡን ሂደት ድል አድራጊነት የሚወስነው ወደ እውነተኛ ሽግግር መግባት ወይንስ የተቀደደ ቦይን ተከትሎ መፍሰስ?” የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ በጊዜውና በአግባቡ ለመመለስ ሙሉ ፈቃደኛና ከምር ዝግጁ ሆነን የመገኘታችን ወይም ያለመገኘታችን ጉዳይ ነው ። የወ/ሮ እማዋይሽ ጥያቂያዊ አስተያየት የሚነግረን የለውጡ ሂደት የታለመለትን ግብ መምታት ካለበት እያንዳንዱ ( መሪዎችን ጨምሮ) ነፃነት ፣ ፍትህ፣ እኩልነት ፣ ሰላምና ብልፅግና ናፋቂ ኢትዮጵያዊ በስሜታዊነት ከሚጋልብ ፖለቲካ ወጥቶ እና ከድጋፍ ሰጭነትና ከምሥጋና አቅራቢነት አልፎ ንቁና ወሳኝ ሚናውን መጫወት እንዳለበት ነው ። የወይዘሮ እማዋይሽን ጥያቂያዊ አስተያት ሥርዓታቸውን እንደ ሥርዓት ማፍረስ ሳያስፈልጋቸው ሰፊ፣ ጥልቅና አሳታፊ በሚሉት ጥገናዊ ለውጥ (reformism)አማካኝነት የህዝብን መሠረታዊና የትየለሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ጥያቄ መመለስ ይቻላል የሚሉ “የለውጥ አራማጅ መሪዎች” ማዳመጥ ቀርቶ መስማት የሚፈልጉት አይመስለኝም ።

ምክንያቱም የዕውነተኛው ለውጥ ግብ (goal) እውን የሚሆነው የሁሉ አቀፍ ብሔራዊ ውይይትን (inclusive national dialogue ) ፣ የጋራ መግባባትን (mutual understanding ) እና ይቅር መባባልንና እርቅን (apology and reconciliation )መሠረት አድርጎ በሚፈጠር የመሸጋገሪያ መንግሥት አማካኝነት ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዕትን እውን በማድረግ እንጅ ፖለቲከኞች (መሪዎች) በሚቀዱልን የፖለቲካ ትኩሳት ማስተንፈሻ መንገድ (ቦይ) በመፍሰስ አይደለም ።

የህን መሠረታዊ ጥያቄ እየሸሹ ከእርሱ መለስ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ የመመላለስ የፖለቲካ ባህልና አስተሳሰበ በአጠቃላይ ላለንበት ዘመንና በተለይ ደግሞ አሁን ለምንገኝበት መሪርና ወሳኝ የለውጥ ሂደት ጨርሶ አይመጥንም ። እናም ከገዥው ቡድን እኩይ ፍልስፍና እና የማስፈፀሚያ ፖሊሲ(አጀንዳ) ተለይተው በለውጡ ሂደት መሪነት ላይ የተሰለፉትን ፖለቲከኞች ስንደግፍ ዋናው ማመሳከሪያችን ( reference point) በምንም አይነት ሌላ አማራጭ (መተኪያ) የሌለውን የሽግግር ሥርዓት መዘርጋትና ወደ አዲስና መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ የመሻገር ጥያቄ መሆኑን ከምር መረዳትንና ለተግባራዊነቱም በፅናት መቆምን ግድ ይላል።

ቀድሞውንም ቢሆን ለአፈና እና ለነፃ እርምጃ የታወጀን አዋጅ የማንሳት ፣ ቀድሞውንም መታሰር የሌለባቸውን ንፁሃን ዜጎችን የመፍታት ፣ ቀድመውንም ቢሆን ለፖለቲካ ጨዋታ ሲባል የአገር ማፈሪያ በሆነው ፓርላማ ፀደቀ በተባለው የሽብርተኝነት ፍረጃ ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶችን ከፍረጃው ነፃ የማድረግ ፣ ባለስልጣናትን ወይም የሥራ ሃላፊዎችን ጦረታ የማስወጣት/ከቦታቸው የማንሳት ወይም የማሰናበት እና በሌሎች የመተካት ፣ የገዥውን ቡድን የአፈና ህጎችን ለመከለስ ኮሚቴዎችን ወይም ኮሚሽኖችን የማቋቋም ፣ ለተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በደምሳሳውም ቢሆን ጥሪ የማቅረብ ፣ ወዘተ እርምጃዎች ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ የሚወስደውን መንገድ ለማመቻቸት የሚያግዙ ሁኔታዎች እንጅ በፍፁም በራሳቸው ግቦች አይደሉም።

ሊሆኑም አይችሉም ። እየሰማንና እያየን ያለነው መጠን የሌለው የደስታና የድጋፍ ግለት ግን በመሬት ላይ ያለውንና ሊኖር የሚችለውን እጅግ ፈታኝ ሁኔታ በቅጡ ተረድቶና ተገቢውን ዝግጅት አድርጎ የተጀመረውን የለውጥ ግስጋሴ ከታለመለት ግብ ለማድረስ የሚያስችል አቅምና ጥበብ ለማጎልበት ፋታ የሰጠን አይመስልም ። በዚህ አይነቱ ልጓም የሌለው ስሜታዊ የፖለቲካ ፈረስ መጋለብ የትየለሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የለውጥ ግብ (goal) እውን ለማድረግ በምናደርገው ጥረት ላይ የተሳሳተ አመለካከት ( illusion or false belief) በመፍጠር ብርቱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አለመስጋት የፖለቲካ ጥበብ ድህነት ነው ። ለዚህ ደግሞ በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ የመጣንበት የፖለቲካ ተሞክሯችን ከበቂ በላይ አስተማሪ ነው ። ለመማር ፈቃደኞች ፣ ዝግጁዎችና ቁረጠኞች ከሆን ።እዚህ ላይ ” የአሁኑ ሁኔታና የአሁኑ መሪዎች እኮ የተለዩ ናቸው” የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ እንደሚኖር እረዳለሁ ። አንድ ወይም ተመሳሳይ አለመሆናቸው የሚያከራክረን አይመስለኝም ። በአንድ እውነታ ግን የምንስማማ ይመስለኛል ።

ዘመናት ካስቆጠርንበት ዛሬን ከልክ ባለፈ የደስታና የተስፋ ሲቃ ተቀበለን ነገ ወደ ሃዘንና ወደ ተስፋ ቢስነት የምንመለስበት የፖለቲካ ማንነት ቢቻል ጨርሶ መቆም አለበት ፣ ካልተቻለ ግን ቢያንስ በቅጡ መሆን አለበት ። ይህን ሆኖና አድርጎ ለመገኘት ደግሞ ከበሰበስና ከከረፋ የህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካል ኢኮኖሚና ማህበራዊ ሥርዓት ጨርሶ መውጣት የግድ ነው ። እንደ እኔ ግንዛቤና አረዳድ ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት አብቅቶለት ፣ ወደ ታሪክ ሙዚየም ገብቶና ተገቢውን የታሪክ ገፅታ እንዲይዝ ተደርጎ በሽግግር ሂደት ወደ አዲስና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ ካልገባን በስተቀር እንኳን አንድ ዶ/ር አብይ አህመድና የተወሰኑ ጓዶቻቸው ብዙ ዶ/ር አብዮችና ጓዶቻቸው ወደመሪነት የመምጣታቸው አጋጣሚ ከጥገናዊነት (reformism)ያለፈ የለውጥ ውጤት አያስገኝልንም ።

የአሁኖች “የለውጥ ደጋፊ መሪዎች” በጋራ ጥረት በሚፈጠረው መሸጋገሪያ መንግሥት እና በሚመሠረተው አዲስና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደማነኛውም ባለድርሻ ተሳታፊ ለመሆን እንጅ አሁን ባሉበትና በሚመሩት ድርጅትና መንግሥት ለውጡን በበላይነት እንመራለን ከሚል ቅዠት ለመላቀቅ ብርቱ ፈተና አለባቸው። አንፃራዊ ጥንካሬና ተቀባይነት ያላቸው ተቀዋሚ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅቶችም ከቅዠትና ልፍስፍስ የፖለቲካ አካሄድ ወጥተው የራሳቸውን ሃላፊነትና ግዴታ ለመወጣት ይህን በየትየለሌ መስዋዕትነት ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የተከፈተውን የለውጥ በር ተጠቅመው የሚቀጥለውን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በር የአገርና የወገን ጉዳይያገባኛል የሚለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሚያስተናግድ አኳኋን መክፈት (ማስከፈት) ይኖርባቸዋል ።

ይህ ሥርዓት እንደሥርዓት እንዲፈርስ ካልተገደደ በስተቀር “በቅዱሳን” መሪዎች መሪነት እንኳ ቢሆን በምንም አይነት የሚፈለገውን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ሊያደርግ አይቻለውም። እናም አገርና ህዝብ ያወቀውና ወደፊትም አደጋ ሊያስከትል የሚችል የለየለት ወንጀል የፈፀመ አካል ካልሆነ በስተቀር ከአሁን በኋላ አንዱ ሰጭ ሌላው ተቀባይ ፣ አንዱ ፈቃድ ጠያቂ ሌላው ፈቃድ ሰጭ ወይም ከልካይ ፣ አንዱ ምህረት ሰጭ ሌላው ምህረት ተቀባይ ፣ አንዱ ደግሶ ጠሪ ሌላው የቀረበለትን ተቋድሶ ወይም ቀላውጦና አመስግኖ ሂያጅ ፣ አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ ፣ አንዱ ተናጋሪ ሌላው አድማጭ ፣ወዘተ ሆነን የኖርንበት እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ባህልና አስተሳሰብ ተለውጦ ሁሉም እንደየአቅሙና እንደየድርሻው በነፃነትና በራስ መተማመን ስሜት የሚሳተፍበትን የመጫወቻ ሜዳ ጊዜ ሳያባክኑ ማመቻቸትን የግድ ይላል።

ከዚህ ያነሰን የለውጥ መዳረሻ (ግብ) ለመቀበል ቀርቶ ለማሰብም የሚዳዳን ከሆነ የትየለሌ መስዋትነት ለምን ተከፈለ ? ብለን የየራሳችን ህሊና (የውስጥ ነፍስ) ጠይቀን መልስ ማግኘት ይኖርብናል ። ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ያነሰ ግብ (goal) ለመቀበል የሚያስችል አጥጋቢ መልስ ግን የምናገኝ አይመስለኝም ። “ይኸስ ምን አነሰን” የምንል ከሆነ ደግሞ እራሳችን ብቻ ሳይሆን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ በምንም አይነት ዋጋ የማይታመን መስዋዕትነት የከፈሉ እልፍ አእላፍ የነፃነትና የፍትህ ሰማዕታትን ታሪካዊ ተልእኮ በጭቃ መጎተትና ለትውልድም ልፍስፍስ ማንነትን ማስተማር ነው የሚሆነው።

ገና ብርቱ ሥራ በሚጠይቀን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ በአለንበት በአሁኑ ወቅት ምክንያታዊ በሆነ አኳኋን ለግለሰቦች ወይም ለመሪዎች ወይም ለቡድኖች ተገቢውን አድናቆት ከሂሳዊ ድጋፍ ጋር ከማድረግ አልፎ “ክንፍ ማውጣት የቀራቸው ሙሴዎች ናቸው” የሚል አይነት በእጅጉ የተለጠጠና ስሜታዊነት የተጫነው “አስተምህሮት” በምንም አይነት መመዘኛ (በሃይማኖ እምነትም ሆነ በማህበራዊ ሳይንሱ ) አሳማኝ አይደለም ። በመርህና በምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተ እውቀትና በፈጣሪው (በእግዚአብሔር) ድጋፍ የራሱን የወደፊት እጣ ፈንታ በራሱ ተጋድሎ የተሻለ ብቻ ሳይሆን የላቀ ማድረግ አለበት ለምንለው ትውልድ እንዲህ አይነት የታሪክን ምንነትንና እንዴትነትን (context) ባላገናዘበ አኳኋን የሚቀርብ የጅምላ (ደምሳሳ) “አስተምህሮት” እውነትነት ብቻ ሳይሆን ሃላፊነትም የጎደለው ነው ።

ለብዙ ዘመናት በመከራና በውርደት ውስጥ የኖርነው ፈጣሪ ሊቀጣን ፈልጎ ሳይሆን እርሱ በነፃ በሰጠን አእምሮና አካል ተጠቅመን እራሳችንን ነፃ ለመውጣት ባለመቻላችን ብቻ ነው ። ፈጣሪ እነ ዶ/ር አብይን እየጥበቀ ስለነበርም በፍፁም አይደለም ። ሊሆን አይችልም ። እነ ዶ/ር አብይን ወደ አሁኑ ህዝባዊ መስመር ያመጣቸው ህዝብ በራሱ ድክመት የራሱን መከራና ውርደት እያራዘመ እግዚኦ ከማለት አባዜ በመውጣት የድርሻውን እየተወጣና በእርሱ (በፈጣሪ) እርዳታ እየታገዘ እውን ያደረገው የለውጥ ፈላጊነት ተጋድሎ ነው ።

አንዳንድ ወገኖች ሙሴንና ዶ/ር አብይን ለማመሳሰል የዕድሜ አቻነትን (40 ዓመት) ሳይቀር ለማገጣጠም የዘመነ ኦሪት ሃይማኖታዊ ታሪክ ፍለጋ የሄዱበት እርቀት በእጅጉ የተለጠጠ ፣ ስሜታዊነት የተጫነውና በእጅጉ አሳሳች ነው ። መሪዎችን ያልሆኑትን ናችሁ ማለት ያባልግ እንደሆን እንጅ ልዕልናን አይጨምርም ።

በህዝብ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ተገደውም ቢሆን ለአገርም ሆነ ለራሳቸው የሚበጀውን ለማድረግ የመረጡትን መሪዎች በአግባቡ እውቅና እና አድናቆት መስጠት ተገቢ ነው ።በህዝብ ተጋድሎና በፈጣሪ እርዳታ የሆነውን መልካም ነገር (የለውጥ ጅማሮ) ከመሪዎች ጋር ተባብሮ በማስተዋልና በጥበብ ከዳር ማድረስ ያስፈልጋል ከማለት አልፎ እነዚህ መሪዎች “ከፈጣሪ የተላኩልህ ናቸው” ብሎ ለህዝብ መንገርን ወይም መስበክን ግን እራሱ ፈጣሪም አሜን ብሎ የሚቀበለው አይመስለኝም ።

ከፍጥረታት ሁሉ ለይቶ የሰጠንን አቅምና ችሎታ ራሳችንን ከራሳችን ክፉ ወገኖች ነፃ ለማድረግ ያልቻልን ደካሞች ወይም ፈሪዎች በመሆናችን ለአያሌ ዓመታት እራሳችን ክፉኛ ቀጣነው እንጅ እኛን ቀጥቶ በእኛ መከራ የሚደሰት ጨካኝ ፈጣሪ በፍፁም የለም ። አይኖርምም ። አሁንም እዚህ ተስፋ ሰጭ የለውጥ ጅማሮ እንድንደርስ ፈጣሪ ሊረዳን የፈቀደው የሰጠንን አቅምና ችሎታ ተጠቅመንና ፍርሃትን በጣም ቀንሰን ከምር መነሳታችን በማወቁ ነው ። መሪዎችም በዚህ እውነታ ውስጥ እራሳቸውን በማየት የለውጡን ጅማሮ ለታለመለት እውነተኛ (አዲስ) የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ እንዲበቃ ማስቻል ይኖርባቸዋል እንጅ የለውጥ ነፋስን አቅጣጫና ብርታት እየለኩ “የአዳኝነት ገድል”ካልነገርንላችሁ ወይም ካልተቀኘንላችሁና ካልዘመርንላችሁ የሚሉ የድንቁርና ወይም የግብዝነት ወይም አስመስሎ የመኖር ወይም የአድርባይነት ልክፍተኞች ሰለባ ላለመሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ።

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያለባቸው ሃላፊነትና ተግባር ቀላል አይደለም (አይሆንምም) ። እንኳን በአገር ደረጃ በአንድ በተወሰነ ድርጅት ደረጃም የመሪነትን ሥልጣንና ተግባር አጠቃቀም ተከትለው የሚመጡ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ለማወቅ የሥራ አመራር ወይም የተመሳሳይ ሙያ ባለቤት መሆንን አይጠይቅም ። እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መካከል እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሶስት ወራት የሥራ ሂደት ከታዩትና እስከአሁንም በመቀጠላቸው ልብ ሳንላቸው እንደ ጥሩ (ጤናማ) የአመራር አካሄድ እየተቀበልናቸው እንዳንቀጥል ሊያሳስቡን ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ ሃላፊነትንና ሥልጣንን በየደረጃው ለሚገኙ የበታች ባለሥልጣናትና የሥራ ሃላፊዎች የማካፈል (delegate) የማድረግ ጉዳይ ነው ።

በርግጥ ከውስብስቡ የፖለቲካ ሁኔታችን አንፃር እና ባልተጠበቀ መጠንና ፍጥነት በተከሰተው የለውጥ ግፊት ምክንያት ይህን በጣም አስፈላጊ መርህና አሠራር በተሟላ አኳኋን እንዲተገበር መጠበቅ ትክክል አይሆንም ። ከተጨባጩ እውነታ ጋር በሚራመድ (በሚሄድ) እና በሚመጥን አኳኋን ተግባራዊ አለማድረግ ግን በምንም አይነት ተገቢና አሳማኝ አይሆንም ። እንደእኔ ግንዛቤና አረዳድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉን ነገር የመጠቅለል ፍላጎት ( excessive ambition) ቢኖራቸው ነው ከሚል እጅግ ስሜታዊና ደምሳሳ አስተያየት ላይ መድረስ ስህተት መሆኑን ብረዳም ችግሩ መኖሩን በግልፅና በቀጥታ አለመነጋገር ደግሞ የባሰ ስህተት ነው ባይ ነኝ ።

ለማጋነን ሳይሆን እውነቱ ለመናገር ባለፉት ሶስት ወራትና እስከአሁንም ድረስ በተለያዩ የአገር ውስጥ ጉዳዮችም ሆነ በውጭ ግንኙነት መስክ ከዶ/ር አብይ አህመድ ሌላ ወይም ጎን ለጎን ጆሮን ለሚስብ ዜና እንኳ የሚበቃ የሌላ ባለሥልጣን ወይም የሥራ ሃላፊ ተሳትፎ (presence and participation) አለማየት በምንም አይነት ምክንያት ጥሩ ነገር አይደለም ። የካቢኔ አባላት ተራ ልዩ ባለሞያዎች (experts/speccialists) ሆኑ እንዴ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብ መገረም ወይም ጥያቄውን ስላልወደድነው ማጣጣል ያለብን አይመስለኝም ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅታቸውና መንግሥታቸው የሚከተሉትን የፖለቲካ መስመር ፣ የሚመሩባቸውን ፖሊሲዎችና አሠራሮች በተመለከተ ለህዝብና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በልዩ ልዩ መድረኮችና የመገናኛ ዘዴዎች የማሳወቅና እንደ አስፈላጊነቱም ሥልጠና እና አውደ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታች እንዲምቻቹ ማስደረግ እና እራስም እንደአስፈላጊነቱ በቀጥታ መሳተፍ እጅግ በጣም ተገቢና ጠቃሚም ነው።

ከዚህ አልፎ ግን ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ ለኪነጥብ ባለሙያ ሥልጠና እስከመስጠትና እንደመደበኛ አስታራቂ ሽማግሌ ሆኖ እስመሥራት ሲኬድ ምነው በአገሩ እንደዚህ አይነቶችንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንኳ በሃላፊነትና በተመጣጣኝ እውቀት የሚመራ (የሚያስተባብር) እና መልክ የሚያስዝ ባለሥልጣን ወይም የሥራ ሃላፊ ወይም ባለሙያ በአገር ታጣ እንዴ ? ቢያሰኝ ሊገርመን ይገባም።

ታዲያ በዚህ አካሄድ የአገሬ ህዝብ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሌሉበት መድረክና ያልተናገሩበት ጉዳይ ጨርሶ አይጥመኝም” የሚል አጉልና የድንቁርና ልማድ እየተጠናወተው ቢመጣ ምን ይገርማል ? እናም የለውጡ ግስጋሴ የታለመለትን ግብ ይመታ ዘንድ እንዲህ አይነት አካሄዶች ሥር ሰደው ሳያስቸግሩ በጊዜና በአግባቡ እርምት ሊደረግባቸው ይገባል ።

ከሰሞኑ የሚታዩ ፣ የሚደመጡ ፣ የሚነበቡና የሚዜሙ መልእክቶች በአብዛኛው ከምንጠብቀው የለውጡ ግስጋሴ ግብና እጣ ፈንታ( goal and destiny) እና ይህንም እውን ለማድረግ ከሚጠብቀን እልህ አስጨራሽ ተግባርና ሃላፊነት አንፃር የተቃኙ አይመስለኝም ። የግስጋሴውን ፍጥነትና ስኬታማነት በየደረጃው በመረዳትና በመገምገም ተገቢውን ተሳትፎ ከማድረግና ሂሳዊ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ድሉ የተጠናቀቀና አገርም አገረ ዴሞክራሲ ፣አገረ ነፃነት ፣ አገረ ብልፅግና ፣ አገረ ፍትህ ፣አገረመብት ፣ ወዘተ የሆነች በሚመስል አኳኋን የሚቀርቡ ሃሳቦች ፣ የሚፃፉ ፅሁፎች፣ አደባባዮችን ቀውጢ የሚያደርጉ የሰልፍ ትዕይንቶች ፣ ለመሪ (ዎች) የሚዜሙ ውዳሴዎች ፣ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች ፣ አንጋፋዎችን ጨምሮ ፊደል በቆጠረው ( በተማረው ) የህብረተሰብ ክፍል የሚስተጋቡ የእልልል !እንበል አይነት “ትንታኔዎች” ፣ በድል አጥቢያ አርበኞች (በአድር ባዮች)የሚተወኑ ጭራ የመቁላት ተውኔቶች ፣ በቁጥር ቀላል ከማይባሉ የህብረተሰብና የሙያ መስክ አባላት የሚስተዋሉ የፖለቲካ ሽርሙጥናዎች (politicalprostitutions) ፣ ወዘተ አስፈላጊው ትኩረት ካልተሰጣቸውና ገንቢ እርማት ካልተደረገባቸው ልማድ ይሆኑና የለውጡን ግስጋሴ ወደ ግቡ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለመመሥረትና ለመገንባት በምናስበው አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይም የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም ።

ልብ ብለን ከሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከህዝባዊ ለውጡ ጋር ተደምረዋል (መደመር የሚለውን ደምሳሳ ቃል ከሂሳብ ቀመርነቱ አልፎ ውስብስብ ለሆነው ፖለቲካችን እንደ መሪ ቃል መጠቀሙ ብዙም የሚስብ አይመስለኝም ) የሚባሉት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች ለተቀዋሚ ድርጅቶች በደምሳሳው ጥሪ ከማቅረብ ባለፈ ወደ የትኛው የለውጥ ግብ መድረስ እንደሚፈልጉና እንደተዘጋጁ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግልፅ ያደረጉት ነገር የለም። በየስብሰባውና በየድጋፍ ሰልፉም ስሜታዊነትን በቅጡ ተቆጣጥሮ ይህን ጥያቄ ከምር የሚያስተጋባ ድምፅ አይሰማም ማለት ይቻላል ። ተሰምቶም ከሆነ ላለንበት እጅግ ፈታኝና ወሳኝ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚመጥን አይሆንም ። በየዘመናቱ በተፈራረቁብን ገዥዎች ሲዘወር የኖረው የፖለቲካ ባህላችንና ሥነ-ልቦናችን ባሳደረብን ብርቱ ተፅዕኖ ምክንያት “አዬ ! ይህች ለእኛ ምን አነሰችን” እንዳንል ስጋት ቢኖር የሚገርም አይደለም ።

በባህዳሩ ትዕይንተ ህዝብ ላይ ከስብሰባው አዘጋጅ እስከ ተጋባዥ እንግዶች ጨርሶ ያልደፈሩትን የሽግግር መሰናዶ አስፈላጊነት ወ/ሮ እማዋይሽ “ለለውጥ አራማጅ” የክልሉ መሪዎች ሲሰነዝሩ አደባባዩ በጭብጨባ ተናወጠ። ያን ያህል እጅግ በሚገርም የለውጥ ጥማትና የአገር ፍቅር ስሜት አደባባይ የወጣ ወጣት “የለውጥ አራማጅ መሪዎችን” መደገፉና ማሞገሱ እንዳለ ሆኖ ለምን እንደዚያ በሚገርም አድናቆት የተቀበለውን የወ/ሮ እማዋይሽን እጅግ መሠረታዊ ጥያቄ እንደ አንድ መሪ መፈክር አንግቦ አልወጣም ? ለምንስ አስቦበትና ተዘጋጅቶበት መሪዎችን አልጠየቀም ? ለምን ፎቶ ግራፋቸውን ደረቱ ላይ የለጠፈላቸውን “የለውጥ አራማጅ መሪዎቹን” በጥያቄ አላፋጠጠም? ለውጥን (መለወጥን) ለሚያነቃቁ ዲስኩሮችና እየተወሰዱ ላሉ አወንታዊ እርምጃዎች ተገቢውን እውቅና እና አድናቆት መስጠት እንደተጠበቀ ሆኖ የለውጡ ሂደት ዋና ግብ (the ultimate gaol) የት ነው? ምንድነው ? መድረሻውስ መቼና እንዴት ነው ? ብሎ ለምን በቀጥታ ወይም በአዘጋጁ (በወኪሉ) አማካኝነት ከምር አልጠያቀም ? ምነው በሙገሳ እና በማውገዝ ፖለቲካ ብቻ ተጠመድን ? በወ/ሮ እማዋይሽ ጥያቄ መነሻነት ባህርዳርን ጠቀስኩ እንጅ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችና ከተሞች የተካሄዱት ትዕይንተ ህዝቦችም በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው ።
የለውጡ ግሥጋሴ ስኬት የሚወሰነው የሂደቱ ባለቤትና የውጤቱ ተጠቃሚ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ክፉ ገዥዎቹ ተለያይቶ እንዲያስብና ተግባብቶ እንዳይኖር በተረጎሙለት የህዝቦች/ብሔሮች/ ብሔረሰቦች ትርጓሜ ሳይሆን እንደ አንድ አገር (ኢትዮጵያ) ህዝብ በሚያደርገው የጋራ ተጋድሎ ብቻ ነው።

ለሩብ ምእተ ዓመት ከዘለቅንበት እጅግ አስቀያሚ የማንነት (በኢትዮጵያዊነት እያፈሩ በብሔረሰብ ወይም በጎሳ ከመኩራራት) ቀውስ የሚገላግለን ለሁላችን (እንደዜጋ) የሚበጀውን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ የሚያግዙ ሁኔታዎችን እያየን መሆኑ እውነት ነው ። በኦሮሞና በአማራ ወጣቶች “የእርሱ (የእረሷ) ደም የእኔ(የእኛ) ደም ነው” በሚል የተላለፈውን ጥልቅ መልእክት ጨምሮ በአብዛኛው የአገራችን ክፍሉችና ከተሞች የተስተዋለው የአብሮነት እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ላለው የለውጥ ግስጋሴ ስኬታማነት የሚኖረው በጎ ተፅዕኖ ጉልህ ነው ።

 ይህ ግን በሰከነ፣ በመከባበር ላይ በተመሠረተ ፣ ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ ፣ አርቆ አስተዋይነትንና ገንቢነትን በተላበሰ የሃሳብ ልውውጥ ዳብሮ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ዘላቂነት ያለው አገራዊ የምክክርና የትብብር መድረክ (ድርጅታዊ ቅርፅ) እንዲይዝ ካልተደረገ የለውጥ ሂደቱ የታለመለትን (አዲስ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) ግብ ይመታ ዘንድ የሚጠበቅበትን ያህል ሚና ለመጫወት የሚችል አይመስለኝም ።

መለስተኛ የሆኑ ወይም ብዙም የሚያሳስቡ የማይመስሉ ጉዳዮችን እንኳ በሰለጠነ ፣ ቅንነትን በተላበሰ ፣ በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከተሳነን በዚህ አይነት የፖለቲካ ጨዋታ የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ለሚሉ አንዳንድ “ልሂቃንና” ፖለቲከኞች እድል ሰጥተን ወደ ኋላ እንዳይጎትቱን መሥጋት ተገቢ ነው ።

ከሰንደቅ ዓላማ ምንነትና እና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከሚሉ የስያሜ ቃላት ጋር በተያያዘ የምንሰማውና የምናየው እሰጥ አገባ ከቶውንም ችላ መባል ያለበት አይመስለኝም ።በእንዲህ አይነት ጉዳዮች ላይ የሚያጋጥሙትን ብዥታዎች ከተቻለ አሁንኑ በሰለጠነ መንገድ ተከራክሮ መተማመን ፣ ካልሆነ ግን የሚበጀውን ሥርዓት እውን አድርጎ ያ ሥርዓት በሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ለመተማመን ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን የግድ ነው ። የምንመኘው አዲስ ሥርዓት ለሁላችን የሚበጅ መሆን ካለበት የሚያዋጣው መንገድ ይኸው ብቻ ነው ። ለመሆኑ እንደዚህ አይነቶቹን ጉዳዮች ከማንነት ጋር እያያዝንና የፖለቲካ ገመድ ጉተታ ጨዋታ ውስጥ እየዳከርን በህወሃት ተጫነብን የምንለውን የጎሳና የዘር ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ አስወግደን ለሁላችን የሚበጅ ሥርዓት እንመሠርታለንና እንገነባለን ስንል ምን ማለታችን ነው ?

ለብዙ ዓመታት በህወሃት/ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ጫፍ በረገጡ ፖለቲከኞችና “ልሂቃን” አጥብቆ ሲጦዝ የነበረው በአንድ በኩል በብሔረሰብና የዘር አጥንት ቆጠራ ላይ የተመሠረተው እና በሌላ በኩል ደግሞ ያለምንም ጥያቄ (ቅድመ ሁኔታ) አንድነት የሚለው የፖለቲካ አመለካከት አሁንም የፖለቲካችን አስቀያሚ ገፅታዎች ናቸውና ከለውጡ ሂደቱ ጋር በተገዘናበ አኳኋን መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮቻችን ናቸው ።

ዘላቂ መፍትሄን ማረጋገጥ የሚቻለው ግን ህዝብ የእኛ ነው የሚለውን ሥርዓት ፖለቲከኞች በመጡና በሄዱ ቁጥር በማይናወጥ መርህና አሠራር ላይ መመሥረትና መገንባት ሲቻል ብቻ ነው ። ይህ ነው ህዝብ ብሔረሰብና ቋንቋ እየለየ በተናቆረ ቁጥር የፖለቲካ ትርፍ ያገኙ እየመሰላቸው የሚቅበዘበዙ ልሂቃንና ፖለቲከኞችን ጨርሶ ባያስቆማቸውም አንፃራዊ አደብ የሚያስገዛቸው ።

ሃሳቤን እንደሚከተለው ላጠቃል

የለውጡ ግስጋሴ ፖለቲከኞች በሚመጥኑለት ሳይሆን የትግሉ ባለቤትና የውጤቱ ተጠቃሚ በሆነው ህዝብ ፍላጎትና ወሳኝነት በሚመራ አመራር እውነተኛ ግቡን መምታት ይችል ዘንድ ከስሜታዊነት በመውጣት የምር ጥያቄዎችን ከምር መጠየቅ የግድ ይላል ።

ጎበዝ! የአደባባይ ትዕይንቶችና ንግግሮች አያሌ መስዋትነት የተከፈለበትን የለውጥ ግብ በርግጠኝነት ለማሳካት በሚያችሉ ስትራቴጅካዊ ሃሳቦችና ተግባራዊ እርምጃዎች ካልታገዙ ጊዜያዊ የስሜት ትኩሳትን ከማስታገስ አያልፉም። እንዲህ ሲሆን ደግሞ መሪዎችን ጨምሮ ያዘናጋል (ያበላሻል)። የሚወዱትን በማሞገስ እና የሚጠሉትን በማውገዝ ላይ በመጠመድ የሚፈታ የፖለቲካ ቀውስ የለም። የምንወደውን በምክንያታዊነት፣ በገንቢ ሂሳዊ አቀራረብና በመፍትሄ ጠቋሚነት መደገፍ እንዳለብን ሁሉ የማንወደውንም ቢቻል ወደ እምንወደው እንዲመጣ ካልተቻለ ደግሞ ከአሻፈረኝ ባይነትና ከአፈርኩ አይመልሰኝ ልክፍት እንዲታቀብ ለማድረግ እልህ አስጨራሽ ጥረት ማድረግ ተመራጭ አካሄድ ነው ። ይህ ግን ራሱን የቻለ ትዕግሥትን ፣ አስተዋይነትን ፣ አርቆ አሳቢነትን (ትውልድ ተሻጋሪነትን) እና በምናባዊ አመለካከት ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ላይ አለመድረስን ይጠይቃል ።

ከስሜታዊነት እየወጣንና እየተረጋጋን ፣ አስተዋይነትን እየተላበሰን ፣ የዕለት የዕለቱን ወይም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የነገውንና የትውልደ ትውልድን እጣ ፈንታ አርቀን እያየን ፣ መሪዎችን ከማምለክ (cult) ሰለባነት እየተጠነቀቅን፣ የመደመርን ፖለቲካዊና ማህበራዊ እሴትን በደምሳሳው ሳይሆን ምን? እነማን? መቼ ? የት ? ለምን? እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡ እየመለስን፣ ሁሉንም የድክመትና የውድቀት ምክንያት ከራሳችን እያራቅን በሌሎች ላይ ብቻ የመዘፍዘፍን የፖለቲካ ጨዋታ (political blame game)እየተውን (እየቀነስን) ፣ ወዘተ በሄድን ቁጥር ወደ እውነተኛውና ታሪካዊው የዴሞክራሲ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ የመድረሳችን እድል በእጅጉ ሰፊና አስተማማኝ ያደርገዋል ።

ይህን እውን ለማድረግ በሚደረግ የትግል ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙን ፈታኝ ሁኔታዎች (challenges) የምንለውንና የምንመኘውን ያህል ከቶም ቀላል አይደሉም ። ሌላ የተሻለ አማራጭ የሌለው መንገድ አብሮ የመዳን ብቻ ሳይሆን አብሮ የመሰልጠንና የመበልፀግ መንገድ ነው ። ይህ ወርቃማ መንገድ (እድል) ደግሞ ይህን እጃችን ላይ ያለው የለውጥ ሂደት የታለመለትን ግብ (የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ፣ ምሥረታና ግንባታ) እንዲመታ ማድረግ ነው ።

በእኛ ጥረት እና በፈጣሪ እገዛ ሁሉም ነገር ለሁላችነም በሚበጅ አኳኋን ይፈፀም ዘንድ እየተመኘሁ አበቃሁ !!!

No comments