Latest

ይድረስ ለሕወሐት (TPLF) አመራርር ክፍል (ይፍሩ ኃይሉ)


በባሕላችንም በልማዳችንም ሰላምታን ማስቀደም ተገቢ ስለሆነ የአክብሮት ሰላምታዬን አስቀድማለሁ።ወቅቱ የሰላምና የፍቅር፤የደስታና የመደመር ወቅት በመሆኑ፤በኢትዮጵያና በመላዉ የአገሪቷ ሕዝብ ልብ ዉስጥ የሰፈነዉ ደስታ በናንተም በወንድሞቻችን ልብ ዉስጥ እንዳለ አልጠራጠርም።አገር ሰላም ሲሆን፤ሕዝብ ሲደስት ማነዉ አብሮ ደስ የማይለዉ?

ከዛሬ ሦስት ወራት ጀምሮ እስከ ዛሬዉ ዕለት ድረስ በአገራችን ዉስጥ፣ በሚያስደንቅ ፍጥነት በመካሄድ ላይ ያለዉን፣ የዕርቅ፤ የሰላም፤ የመደመርና የአንድነት ግስጋሴ እኛን ቀርቶ መላዉን ዓለምን ጭምር እያስደነቀዉና እያስደመመዉ ይገኛል። ከሃያ ዓመታት በላይ፤በኢትዮጵያና በኤርትራ፣በሁለት እህትማማች አገሮች መሃል ተፈጥሮ በነበረዉ አለመግባባት፤ከሁለቱም ወገን የብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደም በከንቱ ከፈሰሰ በኋላ፣ጦርነቱ ቢቆምም ላለፉት ሃያ ዓመታት ያህል ሁለቱም አገራት፤ሰላም አይሉት ጦርነት፤ሠራዊቶቻቸውን በድንበራቸዉ አስፍረዉ፣የሁለቱም ወታደሮች፣በቀን ሐሩር በሌት ቁር ሲጠበሱ ሁለት አሥርት ዓመታት አለፉ።

የማያልፍ ቀን የለምና ያም ቀን አለፈና፤ዛሬ፤እግዚአብሔር በላከልን በኢትዮጵያ ሙሴ፣በጠቅላይ ምኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሊ የሰላም እጃቸዉን በመዝርጋት የማንንም አስታራቂነት ሳይጠይቁ፣ ለፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ያቀረቡትን የሰላም ጥያቄ፤ክቡር ፕሮእዚደንት ኢሳያስም የተውደደዉም የኤርትራ ሕዝብ በደስታ ተቀብሎ የተደረገላቸዉን አቀባበልና ሕዝቡ ያስያቸዉን ፍቅር እዚህ ላይ ማብራራት አያሻም።”ሲያዘንብ ያጎርፈዋል” እንደሚሉ፣ዛሬ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራያ ያለውን ደስታና ፈንጠዝያ ለመግለጽ ያዳግታል። ጨዋዉና ጀግናው መላዉ የትግራይ ሕዝብና እናንተም በሕወሐት አመራር ዉስጥ ያላችሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም በዚህ ድንቅ እርምጃ ደስ እንደሚላችሁ አንጠራጠርም።

“ለጋስነት(ቸርነት)ከቤት ይጀምራል” እንደሚሉ፣ክቡር ጠቅላይ ምኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ሰላሙን የጀመሩት ከሀገራቸዉ፤ከኢትዮጵያ ነዉ።ወዲያዉ ሥልጣናቸውን እንደተረከቡ፣የእግዚአብሔርን ትልቅነትና፤የናት አገራቸዉን የኢትዮጵያን የአገር ዕንቁ እንደሆነች በአደባባይ ቆመዉ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አውጁ።ያን ዕለትም በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ዉስጥ ገቡ።

ሳይዉሉ ሳያድሩ የሕዝባቸዉን የልብ ትርታ፣ ብሶትና ስጋቱን፣ጥያቄዉንም ለመመለስ፤በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር መወያየት ጀመሩ።መቀሌም ከነዚህ መሃል አንዷ ነበረች።በዚህም አላቆሙም የኢትዮጵያን ሕዝብ ጩኸት እያዳመጡ፣በሃያ ሰባት ዓመታት፣በሆነ ባልሆነዉ በአሰቃቂዉ ወሕኒ ቤቶቻችሁ አጉራችሁ በስቃይ ላይ የሚገኙ የፖሊቲካ እሰረኞችን፣ እነአዳርጋቸው ጽጌን፤እነእስክንድር ነጋን እነ አዱዓለም አራጌን እነበቀለ ገርባንና ስፍር ቁጥር የሌላቸዉን ወገኖች አስፈቱ።

የኢትዮጵያን ሕዝብ አንደበቱን ለመዝጋት፤እንቅስቃሴዉን ለመገታት ብላችሁ፤የጣላችሁበትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንዲነሳ፤አደረጉ።ከሃያ ሰባት ረዥም የስቃይ ዓመታት በኋላ፣ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ “እፎይ”ማለት ጀመረ። የሰላም ጭላጭሉ ቦግ እያለ ሲሄድና ጨለማዉ ወደ ብርሃን ሲለወጥ፤በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ዉስጥ ያለዉ ደስታና ተስፋ ቦግ ብሎ እየታየ፣እናንተን ምነንዳሰቀየማችሁ፤ስናዉቅ ፊታችሁን አዞራችሁብን።አሁንም የተንኮልና የሸር ዘውዴያችሁን፣ ያንኑ ”የከፋፍለህ ግዛ ወይም ከፋፍለህ አሸንፍ” ተንኮል በመጠቀም፤ወደ ደቡብና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ጎራ አላችሁና ሱማሌዉን ከኦሮሞዉ፣ቤኒሻንጉል ጉምዙን በአማራዉ፣ወላይታዉንም ሲዳማዉንም ማተረማመስ ጀመራችሁ።

ዕቅዳችሁ”ይህ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የምትሉት ጠቅላይ ምኒስቴራችሁ አገሪቷን ማስተዳደር አልቻለም፤ ሕዝቡ በየአለበት አምጾ እርስበርሱ እየተፋጀ ነዉ፤ ብላችሁ እንደገና አስቸኳይ አዋጅ አዉጃችሁ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዳችሁ ዶከተር ዐቢይን ፈንቅሎ ከፖሊቲካዉ ጨዋታ ዉጪ ለማድረግ በናተዉ ጓዳ ዉስጥ የተጠነሰሰች የተንኮል መርዝ ስለነበረች፤ ሕዝቡ ከናንተ ቀድሞ ነቃብችሁ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ፤ዛሬ ባገኘዉ ድንቅ መሪ በፍቅሩ ተንድፏል።ይህ መሪ ከሰማይ እንደ መና የወረደለት የኢትዮጵያ ሙሴ ነዉ ብሎ ያምናል። ይህን ሕዝብ አሁን ካለበት የደስታ መንፈስ ነጥሎ ተመልሰህ ወደ ዘመነ ወያኔ ግባና ተሰቃይ ማለት እብደት ይባላል። 

አይታለምም። እጅግ በጣም የሚያሳዝነዉ፤ ይህ ንጹህ ሕዝብ ዛሬ ደስታና የመኖር ተስፋ ላጎናጸፈዉ የሰላምና ባለራዕይ መሪዉ ላይ ያለዉን ፍቅርና አክብሮት በአንድ ቦታ ተሰብስቦ ምስጋናዉን በመግለጽ ላይ እንዳለ፤የመሪዉን ሕይውት ባጭር ለመቅጨት ያደረጋችሁት አሳፋሪና አሳዛኝ እርምጃ፤እኛም ታሪክም ስናስታዉሰዉ እንኖራለን። 

የሚገርመዉ ዛሬ በጠቅላላ በኢትዮጵያ ዉስጥ ስለእናንተ ሰላምን እየሰበከ፤አብሮ መኖርን እያረመደ፤”ያለፈዉን እረስተን ይቅር ተባብለን ወደፊት እንገስግስ” የሚልን መሪ እንዴት ጦር ይሰበቅበታል? እንዴትስ መርዝ ይጠነሰስለታል?ስለ እናንተ በጎነትና ደህንነት የሚያስብ አንድ ሰዉ ቢኖር ከክቡር ጠቅላይ ምኒስቴሩ በስተቀር ሌላ አንድ አይገኝም። ታድያ ጎበዝ በመላ ኢትዮጵያን

አንድ ወዳጅ ዶከተር ዐቢይ ቢኖራችሁ እንዴት “ዓይንህን ላፈር”ትላላችሁ? ዕዉነቱ ግን ልፉ፣ ድከሙ ቢላችሁ እንጂ ይህን የተቀደሰ ዓላማና እርምጃ አሰናክሎ ወደኋላ መመለስ በጭራሽ አይታለምም። ይህ ያለቀለት ጉዳይ ነዉና እሱን እረስታችሁ ወደሚያዋጣውና ለናንተም በሰላም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመኖር የሚያስችላችሁን መንገድ ዛሬዉኑ መምረጥ ነዉ። እሱም የይቅርታና የንስሐ መንገድ ብቻ ነዉ።

ዕርግጥ ነው፤የኢትዮጵያን ሠራዊት ወግታችሁ ኤርትራን አስግንጥላችኋል።አግሪቷን ወደብ አልባ አድርጋችኋል።የኢትዮጵያን ለም መሬት ለአረብና፤ለሕንድ ሸጣችኋል፤የተረፈውንም ከድሃዉ ሕዝብ ዘርፋችሁ የግል ንበረት አድርጋችሁታል።ኢትዮጵያን ሃብቷን መዝረፍና ለም መሬቷን መሸጥ ብቻ ሳይሆን፣በሕዝቧ ላይ የፈጸማችሁት በደል ተዘርዝሮ አያልቅም።ገድላችሁናል።አስራችሁ አሰቃይታችሁናል።በቁማችን ሰልባችሁ አካለጎደሎዎች አድርጋችሁናል። እህቶቻችንን ወልደዉ ዘር እንዳይተኩ መርፌ እየወጋችሁ መሃን አድርጋችኋል።በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እየለመናችሁ ከዓለም ዙሪያ የቃረማችሁትን ለግል ጥቅማችሁ አዉላችሁ እራሳችሁን አበልጽጋችኋል። 

በአገራችንና በኛ ላይ የፈጸማችሁትኝን ግፍ ለታሪ መተዉ እንጂ እኛ ዘርዝረን አንዘልቀዉም። ዕድሜ ለዶክተር ዐቢይ ዛሬ ሁላችንም እንድሳቸዉ ይቅር ባይነትን፣ ፍቅርና፣መደመርን እየተማርን ስለሆነ፤እኛም ተለዉጠናል።በናት አገራችንም ላይ ሆነ በኛ ላይ የፈጸማችሁት በደል፤ከይቅርታ በላይ ነዉ ብለን አንገምትም። ሁሉም ይቻላል። ከናንተ የሚጠበቀዉ በንጹሕ ልብ ንስሐ ገብታችሁ እግዚአብሔርንም፤የኢትዮጵያንም ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅና የተበላሸዉን ማስተካከል፣የተጣመመዉን ማቃናት፤በግፍ ከድሃ ጉሮሮ አዉጥታችሁ የእዘረፋችሁትንና በዉጭ አገእ ባንኮች ያስቀማጣችሁትን የሕዝብ ሁብት ከመለሳችሁ፤እርገጠኛ ነኝ፣ እግዚአብሔርም ደጉና ይቅር ባዩ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይቅር እንድሚላችሁ አልጠራጠርም።

“ያዳቆነ ሠይጣን ሳያቄስ አይለቅም ነውና”በተንኮልና በሸር፣በኔ እበልጥ፣እኔ እበልጥና በስግብግብነት የተመረዘው አስተሳሰባችሁ አሁንም ወደ ጥፋት ጎዳና ጎትቶ፤”ጋሻ አንስተን ጦር ሰብቀን፣የኢትዮጵያን ሕዝብ በኃይል አንበርክከን እንድገና እንደፈረስ እንጋልበዋለን፣በራሱም ላይ ጮቤ እንረግጣለን” ብላችሁ ማሰቡ ይቅርና በሕልማችሁም እንዳይመጣባችሁ። 

እናንተ ጥጋብ በፈነቀላችሁ ቁጥር ጠመንጃ እያነሳነሳችሁ ሰላማዊዉን የትግራይንም ሕዝብ አትበጥብጡት።ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ እናንተ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ቂጥጥ ብላችሁ፣የኢትዮጵያን ንብረትና ሃብት የዘረፋችሁ፤ቤት ሙሉ እየደገሳችሁ፤በዉስኪና በቮድካ፣በሻምፓኛ በዋይን እየተራጫችሁ፤ጮማ ስትቆርጡ፣ዳንኪራ ስትረግጡ፤ያልጋበዛችሁትን፣ትዝ ያላላችሁን የትግራይን ለፍቶ አደር ሕዝብ ዛሬ ሙትልን ስትሉት ትንሽም ቅር እንኳ ሃፍረት አይሰማችሁም?ለመሆኑ ይህ የፈረደበት የትግራይ ሕዝብ ለናንተና፣የናንተን ጥቅም ለማስከበርና የታወረ ጭፍን ምኞት ለማሟላት ሲል ስንት ጊዜ ልጆቹን ይገብር?ስንትስ ጊዜ ለናንተ እየተጋፈጠ የጥይት እራት ይሁን?ባልበላ ጎኑ ባልተበደረዉ ዕዳ እንዴት ይህንን ሕዝብ የቁም ስቃዩን ታሳዩታላችሁ?ኧረ ግፉ በዛበት!!

ደግሞሣ ጦርነት ለማን ጠቅሞ ነዉ እናንተ እንደዚህ ጧትታ የምሸልሉበት?በጦርነት እኮ የብዙ ሕዝብ ሕይወት በከንቱ ያጠፋል፤ቤተሰብ ያፈናቅላል፡፡ስንቱ ሸበበላ ጉብል አካለ ስንኩል ሆኖ ይቀራል፣የሃገር ሃብትና ንብረት በሣት ጋይቶ ይወድማል፡፡እጅግ በጣም ለሚያስፈልጉ፤ለሀገር የሚጠቅሙ፣ለሕዝብ አግልግሎት የሚዉሉ፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ አካባቢዉን በቀላሉ የሚያገናኙ መንገዶች፣ ሌላም ሌላም ብዙ አግልግሎት የሚስጡና ህብረተሰቡን ጥቅምና ኑሮዉን የሚያሻሽሉ ላይ የሚዉለዉን የሃገር ሃብት ለምን ለጠመንጃና ለጥይት፤ ለመድፍና ለመትረየስ፣ ለአድፍኔና ለመድፍ፣ ለታንክና ለጦር አዉሮፕላንና ሄሉኮፕተር መግዣ ይባክናል? ጠመንጃና መትረየሱን አቅልጠን ማረሻና ዶማ፣ማአጭድና መጥረቢያ ብንሠራበት የተሻለ ጥቅም ላይ እንደምናዉለዉ ጠፍቶን ነዉ? ታንኩንና መድፉንስ አቅልጠን ትራክተርና ቡልዶዘር መሥራት ተስኖን ነዉ?  ለመሆኑ፡በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የሚደፍር፣ፀጥታውን የሚያደፈርስ የትኛው አገር ጠላት ነዉ? ዕድሜና ጤና ከሰላም ጋር ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ለዶከተር ዐቢይ ይሁን እንጂ፤ከኤርትራም ጋራ የነበረን ቅራኔ በሰላም መፍትሔዉን አግኝቷል።ሌሎቹም ጎረቤቶቻችን እራሱን የቻለ የየራሳቸዉ ጣጣ በየጉዳቸዉ ስለአለ”ኢትዮጵያ ድረሽልን” እያሉ ይጮህሉ እንጂ ኢትዮጵያን ለመጻረር እንኳን አቅሙ ሊኖራቸዉ፣ አያልሙትም፣አይቃቱትምም።

ጎበዝ ቀዝቀዝ፣ሰከን ብትሉ ይሻላል።ጀግንነቱንም ክነአፄ ቴዎድርስም፣ከናባኮስትር በላይም፣ከነራስ አበበና ከነኃይለ ማርያም ማሞም፣ከነ ገረሱ ዲኪም፣ከነ ዑመርሰመተርም፣ከነ አሊ ሚራ አገር ሙልጭ አድርጋችሁ ወስዳችሁ፣ከናንተዉ ከወያኔ እራስ ራስ ላይ ቆለላችሁት። ትግራይ የጀግና አገር አይደለም ማለቴ አይደለም።የነአሉላ አባ ነጋና የአፄ ዮሐንስ አገር መሆኗን እያወቅሁ እንደዚህ ዓይነቱን ድፍረት አልቃጣዉም። ግን አንድ ግራ የሚያጋባኝ ነገር ቢኖር ጦርነት፣ጦርነት እያላችሁ ስታቅራሩ ግርም ይለኛል።ለመሆኑ ዛሬ እናንተ “ሠራዊት ክተት! ምታ ነጋሪት!”እያላችሁ የምትጮሁት ያንን ጦርነት ማን ሊዋጋዉ ነዉ?ዛሬ እኮ እያንዳንዳችሁ በዕድሜያችሁ ላይ 27 ዓመት መጨመራችሁን እረሳችሁት እንዴ?በዚህ ላይ ደግሞ በግፍ በሰበሰባችሁት ሃብት ሰዉነታችሁን፣በዉስኪና በቮድካ ጉበታችሁን አቃጥላችሁ፣በሲጋራ ሳንባችሁን አንድዳችሁ፣በጫትና በሃሽሽ አንጀታችሁን

አኮማትራችሁ፤ዛሬም እንደ ቀድሞዉ ታግላችሁ የምትጥሉ፤አባራችሁ የምትይትይዙ፤እሮጣችሁ የምታመልጡ፣ተኩሳችሁ የምትመቱ ይመስላችኋል?ወይስ ያንኑ የፈረደበትን ሮጦ ያልጠገበዉን የትግራይን ወጣት ማግዳችሁ የዕሣት እራት ልታደርጉት አቅዳችኋል? ታዲያ ይኸ የጤንነትነዉ? ምነዉ ጎበዝ ቢበቃችሁ!ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ ሰፊ አገር እንደሆነች እያወቃችሁ እንዴት እኛ ብቻ ግጠናት እንሙት ትላላችሁ? ትንሽ አስቡ።የሰላም እጁን ዘርግቶ ‘ኑ እንደመር” እያለ የሚጮህ ብሩህና አስተዋይ መሪ አላችሁና ጥሪዉን ተቀብላችሁ፣ ዛሬዉኑ ኑ አብረን ተደምረን ለናት አገራችን ለኢትዮጵያና ሳይማር ላስተመረን የኢትዮጵያ ሕዝብ እናገልግለዉ።ዉለታዉን በላብችን እንክፈለዉ፤የናፈቀዉንም ሰላም እንስጠዉና በሰላም ዉሎ በሰላም ይደር።

“እኛ ካልበላነዉ ይደፋ!” የምትሉ ከሆነ ግን ምርጫዉ የናንተ ነዉ።ግን የትግራይን ሕዝብ ከናንተ ጋር መደመር፣ እኛ በበላን አንተም በእሣት አሎሎ ተጨፍለቅ ነዉና ይህ ደግሞ በኛ በኩልም ሆነ በንፁሑ የትግራይ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረዉም። ትግራይ የኢትዮጵያ አካል፣የትግራይም ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነውና ትግራይንም፣ሕዝቧንም ለቀቅ፣ለናተም የሚያዋጣችሁን ጠበቅ ማድረግ ነዉ።

ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ዘርፈን ያከማቸነዉን ኢሮ፣ ዶላርና ፓዉንድ ይዘን አገር ለቀን እንጠፋለን የሚለዉን ሕልማችሁን ቅዠት ስለሆነ ብትረሱት ይሻላል።እስከ ዓለም ዳርቻ እርቃችሁ፣ተደበቀን በሰላም እንኖራለን የሚለዉንም ሕልም እርሱት።ያ! ሃ ሰባት ዓመት ሙሉ፣በናት አገሩ ሠርቶ እንዳይኖር ቁም ስቅሉን እያሳጣችሁ፤ለቁም ስቃይና መከራ የዳረጋችሁት፣ከሞት የተረፈዉም ስፍር ቁጥር የሌለዉ የኢትዮጵያ ወጣት እንደ ጨዉ ዘር በዓለም ዙሪያ ስለበተነ እሱ የማይኖርበት አገር ዛሬ አንድ አይገኝም።ያ! የትላንቱ የናንተ ወንጀለኛና እስርኛ፣ ያ የትላናዉ ስደተኛ! ዛሬ እራሱን የቻለ ጌታ ሆኗል። 

ቁስሉም ድኖ፣ጠባሳዉም ሽሮ አምላኩን እያመሰገነ ከናንተ ጋራ የሚፋረድበትን ቀን ብቻ በጉጉት እየጠበቀ ነዉ።ታዲያ ይኸ ለናንተ የሚያጽናና ዜና ነዉ ብላችሁ ታምናላችሁ?የቆሰለ ነብርና የቆሰለ አንበሣ ያቆሰላቸዉን ጉሮሮዉን አንቀዉ ከገደሉት በኋላ እንደሚሞቱ አታዉቁም? የኢትዮጵያም ጀኛ እንኳን የራሱን ደም፣እንኳን የወድሙን ደም ይቅርና የባልጀራዉንም ደም ሳይከፍል እንቅልፍ አይወስደዉም። እንግዲህ ይህ ማለት እናንተ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ አምልጣችሁ የትም በሰላም ልትኖሩ አትችሉም።እንዳልኳችሁ የገደላችሁበትና ያቆሰላችሁት ጀግናዉ የኢትዮጵያ ወጣት ከተሸጎጣችሁበት ጉድጓድ ዉስጥ እንደ እሪያ (ከርከሮ) ግልገል፤ አንገታችሁን እየጠመዘዘ አዉጥቶ ነገ ለፍርድ ያቀርባችኋል።ስለሚረዳችሁ ስለ አዶልፍ ኤክማን የተባለ የጦር ወንጀለኛ (War Criminal) አንብቡ፣ የናንተም ዕጣ ፈንታ ያ እንደ ኤዶልፍ ኤክማን ነዉና፡፡

ግን ለምን ያ ይሆናል? ቀላሉ የሰላም መንገድ እያለ?”ሲስሟት እምቢ ብላ ሲስቧት”እንዳሆንባችሁ ዛሬ የቀረበላችሁን የሰላምና የመደመር ጥሪ ተቀብላችሁ፣እግዚአብHኤርንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቃችሁ፣የዘረቻችሁትን የሕዝብ ሃብት መልሳችሁ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በሰላም ከኛ ከወንዶምቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር እንደ ቀድሞዉ በፍቅርና በሰላም መኖር ትችላላችሁ፡፡ምስጋና ለጠቅላይ ምኒስቴራችን ይሁንና እንኳን ደጉ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና፣መቼም ቢሆን ለናንተ ይቅር የሚል ልብ አይኖረኝም የምለዉ ሰዉዬ ዛሬ ተቀይሬ በናንተ ላይየመዘዝኩትን ሠይፌን ወደ አፎቱ መልሼዋለሁ፡፡እርቅ፣ሰላምና መድመር ይቻላል፡፡ሌላዉ አማራጭ “የንጨት ምንቸት”መሆንን ያስከትላል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
ሰላም፣ ፍቅርና መደመር ከኛ ጋራ ይሁኑ!!
ይፍሩ ኃይሉ
Yifruhailu5@gmail.com

No comments