"ሞት ሳይቀድመኝ" ~ ሐብታሙ መብራቱ (በያሬድ ሹመቴ)
ሐብታሙ መብራቱ እጅግ ደግ ሙያውን በነጻ ለጀማሪዎች በማስተማር የሚታወቅ የተባረከ ልጅ ነበር። በፊልም ስራ ውስጥ ከገጠሙኝ ሙያተኞች ውስጥ በቴክኒክ እና በፈጠራ ብቃት እኩል አቅም ያለው ፊልም ባለሙያ ነበር። ከጉዲፈቻ ፊልም ጀምሮ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በርካታ የፊልም ሙከራዊ ስራዎችን ያቀረበ ሰው ነበር።
በህይወት የተለዩትን አባቱን ለማስታወስ ድንቅ የሆነ ፊልም በማዘጋጀት፤ በመልክ ከአባቱ ጋር የሚመሳሰለውን ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስን መሪ ገፀባህሪ እንዲጫወት አድርጎ "ትዝታህ" የተሰኘ ፊልም አዘጋጅቷል። በቀድሞው የሲዳሞ ግዛት የደስታ በሽታ የተባለውን ወረርሽን ለማጥፋት በጤና ባለሙያነት ዘምተው የነበሩት አባቱን መሳጭ ታሪክ የሚያስቃኝ ፊልም በመስራቱ፤ አባቱን ህያው የማድረጉን ያህል በዚህ የጥበብ ስራው ራሱም ህያው ሆኗል።
ከአንድ ወር በፊት 22 አካባቢ በድንገት ተገናኘንና እንዲህ አለኝ። "የኢትዮጵያ አይረሴ መሪዎች ኮከባቸው ሊዮ ነው። አፄ ኃይለሥላሴ፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ በጣም የሚገርመው ደግሞ የአሁኑ ጠ/ሚንስትር ዐብይ አህመድ ሳይቀሩ ኮከባቸው ሊዮ ነው። በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ስለ እነዚህ መሪዎች የኮከብ አንድ መሆን አጭር ቪዲዮ ለመስራት አስባለሁ። ሞት ካልቀደመኝ" አለኝ።
የምን ማሟረት ነው። ብዬ ተቆጣሁትና ሀሳቡን አድንቄለት የማግዘው ነገር ካለ ጠየቅኩት። "እንዴ በደንብ ነው እንጂ የምታግዘኝ። አንተም እኮ ኮከብህ ሊዮ ነው" ብሎኝ ከት ብሎ ሳቀ። እኔም አብሬው ሳቅኩኝ።
በሳቃችን መሀል ቀድሞ ያላትን ቃል ደገማትና ሳቁን ቆም አደረገ። "ሞት ካልቀደመኝ"
እንዲህ አይነት ቃላት በድንገት ከአፍ ሲወጡ ቢያስደነግጡም፤ እውነት ነው ብሎ ማመን አይቻልምና ብዙም ትኩረት አላደረግኩም ነበር።
ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን የህልፈቱን ዜና ጽፎ ባየሁ ግዜ ድንጋጤዬን መቆጣጠር አቃተኝ። በደረቅ እንባ አለቀስኩ። ደግሜ ደጋግሜ ውሸት በሆነ ስል ተመኘሁ።
እሱስ በለጋ እድሜው ሞት ሳይቀድመው የአባቱን ታሪክ ፊልም ሰርቷል። ምትንም ቀድሞታል ብዬ አምናለሁ።
ሁል ግዜም አንረሳህም ወንድምዬ!
ለልጆቹና ቤተሰቦቹ መጽናናት እመኛለሁ
No comments