Latest

ከማርሽ ቀያሪው ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጀርባ ያለችው ጠንካራ ሴት! (ጌታቸው ሺፈራው)


ሐምሌ 5/2008 ዓም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከየመን ጠልፎ አመጣው የሚባለው ኮማንደር ኃለፎም የሚመራው አፋኝ ቡድን ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የሚኖርበትን ቤት በኃይል አንኳኳ።  

ሰሞኑን  በባለቤቷ ኮ/ል ደመቀ ላይ ያንዧበበውን አደጋ የምታውቀው ወይዘሮ ዘውድነሽ ማለደ ቀድማ ወጣች። በሩን በኃይል የሚያንኳኩትን ሰዎች ማንነት ጠየቀች። የአፋኝ ቡድኑ አባል የሆነ ሰው የኮ/ል ደመቀ ጓደኛ መሆኑን ገለፀላት። 

"መብራቱ ጌታሁን ነኝ፣ ጓደኛው ነኝ" ብሎ መለሰ። ወይዘሮ ዘውድነሽ መብራቱን ታውቀዋለች። መብራቱ በዚህ ሰዓት ሊመጣ አይችለም። መብራቱ ነኝ ከሚለው ሰው በስተኋላ  ደግሞ ብዙ ኮቴ ይሰማል። "አልነጋም፣ ጠዋት ጠይቀን" ብላው ሮጣ ወደ ውስጥ ገባች።

"መጥተዋል ታጠቅ!" አለች ባለቤቷን ኮ/ል ደመቀ ዘውዱን። አስጠነቀቀችው። "እጅ እንዳትሰጥ!" ብላ። እሱ እንደታጠቀ፣ አፋኞቹም እንደቆረጡ ስታውቅ  ልጆቿን ማህደር (7 አመት)፣ ዳግም ደመቀ (3 አመት)፣ እዮብ ደመቀ (1 አመት)  ባኞ ቤት ውስጥ አስቀምጣ ከጥቃት ትከላከላለች። ፈንጅና ብሬን እየተኮሰ በመሃል ወደ ባለቤቷ እየሄደች "አይዞህ!" እያለች ታበረታታዋለች። ኮ/ል ደመቀ ጥይት ላለመጨረስ ሁኔታውን እያየ መተኮሱን ሲያቆም "ተመታ ይሆን" እያለች ትጎበኘዋለች። ደህና መሆኑን ስታውቅ አበረታትታው ወደ ልጆቿ ትመለሳለች።

አንድ ቀን አለፈ። ሐምሌ 6፣ ሌላ ቀን አለፈ ሐምሌ 7፣ በዚህ ሁሉ የጥይት ውርጅብኝ ባሏን እያበረታታች ልጆቿን ከጥቃት ትከላከላለች። ለልጆቿ ምግብ ማብሰል አልቻለችም። በሶስተኛው ቀን ህፃናቱ ሲርባቸው እንጀራ በስኳር ፈትፍታ ለማብላት ጣረች። ፈንጅ የሚጮህባቸው ህፃናት ለመብላት ፍላጎት አልነበራቸውም። አልበሉም።

ልጆቹ ርሃብ ሲጠናባቸው ሐምሌ 7/2008 ዓም በጠዋት ልጆቿን ይዛ ወጣች። ስትወጣ ግን ኮ/ል ደመቀን አንድ ቃል አስገባችው። "አደራ እጅህን እንዳትሰጥ፣ እጅህን ከምትሰጥ ራስክን አጥፋ" አለችው። ቃል ገባላት።

ባሏን ቃል አስገብታ ከዛ ቤት ስትወጣ፣ በር ላይ አድፍጠው የነበሩት የአፋኞቹ ሰራዊት አባላት ያዟት። የአፋኞቹ  ጊዜያዊ ኃላፊ በትግርኛ ይናገራል። "ልጆቹ ከወጡ ቤቱ በከባድ መሳርያ ይመታ" ይላል እንዳለ የሚገመተው ሰው።
ከዛ በፊት ግን ዘውድነሽን ወደ አንድ ግቢ ወስደው አስፈራሯት። 

"ሄደሽ ባልሽን እጁን እንዲሰጥ አድርጊ፣ ይህን ካላደረግሽ  ከእነ ልጆችሽ እንገልሻለን" አሏት። "ግደሉን" አለች። ባሏን "እጅ እንዳትሰጥ"ያለችው ጠንካራ ሴት ለባሏም፣ ለራሷም ለልጆቿም ህይወት መደራደር አልፈለገችም። "ግደሉን" አለች።

ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስፈራሯት። ስለ እውነት ግደሉን ብላ ስለቆረጠች "አንች አውሬ፣ የአውሬ ሚስት" አሏት። እሷ ግን "ከአማራነታችን ውጭ ምንድን ነው በደላችን?" ብላ ጠየቀች። ባይሰሟትም!

አሁንም የአፋኞቹ ሌላ ኃላፊ ስልክ ደወለ። በትግርኛ ነው! እሷም ትሰማለች። በዛኛው ወገን ያለው ሰው "በከባድ መሳርያ ይመታ!" ይላል! አልፈራችም። አልተደራደረችም።  በሕይወቷም ቢሆን!

በሕዝብ ትግል ግፊት ኮ/ል ደመቀ በከባድ መሳርያ አልተመታም። ከዛ ቤት በፅናት ወጥቷል። ኮ/ል ደመቀን ካፀኑት መካከል አንዷና ዋነኛዋ ባለቤቱ ዘውድነሽ ነች። ከእስር እስኪፈታም ድረስ አፅንታዋለች። 

ፀንታለች! ከኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጀብድ ብቻ አይደለም፣ ለዛሬው ለውጥ ማርሽ ቀያሪነቱ  ጀርባ የነበረችውና ያለችው ብርቱ ሴት ዘውድነሽ ነች! ዘውድነሽ ማለደ!

No comments