Latest

ሕዝብ ከስሜትና ከተራ ብሽሽቅ በመራቅ በያለበት የአገሩ ዘበኛ ይሁን! ~ ጎልጉል


ቀደም ሲል በሃዋሳ፣ ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በተቀነባበረ ሁኔታ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ፣ በቤኒሻንጉል በተለያዩ ቦታዎችና በተለይም በአሶሳ የደረሰንና እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥራት ጭፍጨፋ፣ ሕዝብ ወደ ምሬት እንዲሄድ ሆን ተብሎ የሚደረግ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ በጥሞና ለምትከታተሉ ሁሉ፤

በባህር ዳር ለጠቅከላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ቀና ተግባርና የለውጥ ሩጫ እውቅና ለመስጠት የተጠራውን ሰልፍ ለማወክ ከወዲሁ ቦንብ ሲያዘዋውሩ መያዛቸውን ለሰማችሁ፣ የደኅንነት ኃይሉን ትብትብ በወጉ ለምትረዱና ለምትገነዘቡ፤ በተለያዩ የአገሪቱ የልማት ተቋማት ላይ የሚፈጸመውን የኢኮኖሚ አሻጥር በውል ለምትከታተሉ፤ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሸረቡ ተንኮሎችን ለምታጤኑ፤ለውጡ እንዲኮላሽና አገሪቱ ወደ ትርምስ ውስጥ እንድትገባ በተሸናፊነት ውስጥ ሆነው ለጥፋት የሚመደበውን በጀት ለምትሰሙ …. በጥቅሉ አሁን እየሆነ ያለውን ለምታስተውሉ አገር ወዳድ ዜጎች የጎልጉል ዝግጅት ክፍል አጭር መልዕክት አለው።

እየሆነ ባለው የለውጥ ሂደት ቀልብን ሰብስቦ በማሰብ፣ ልብን በመጠበቅ፣ በየመኖሪያና በየሥራው ቦታ፣ በአለፍንበትና ባገደምነበት ሁሉ የአገራችን ዘበኛ ልንሆን ይገባል። በተራ ብሽⶥቅና እንካ ሰላንቲያ የሚገኝ ትርፍ የለምና እንዲህ ያለውን የሰንፎች መንገድ ካልተውን ተሸናፊዎች አጀንዳና እጅ ተመልሰን እንወድቃለን።

አሁን ጊዜው ዋጋ የሚከፈልበት ነው። አሁን ጊዜው ከቀድሞው መስዋዕትነት በላይ ዋጋ ለመክፈል የምንምልበት ነው። ፍቅር ያሸንፋል ሲባል፣ ከክፉ መንገዳቸው የተመለሱትን ከነጸጸታቸው መቀብል እንጂ መግፋት አይደለምና በአገር ደረጃ ለታወጀው የሰላም መንገድ፣ የድል መንገድ፣ የዕርቅ መንገድ ክፉዎች የሚወድቁበት ወጥመድ ይህ የፍቅር መንገድ ብቻ በመሆኑ በማስተዋል እንራመድ።

በየድረገጹና በየማኅበራዊ ሚዲያ የሚታየው፣ የሚነበበው ተራ የብሽሽቅ ፖለቲካ ብስጭት ውስጥ ያሉትን የበለጠ እንዲያመርሩ፤ ያልገቡትን ደግሞ ወደዚያው እንዲገቡ የሚገፋፋ ነው ሰከን እንበል። ያለንበት ሁኔታ “ተራው የኔ ነው” የሚያስብል ሳይሆን አገር ለማዳን የምንጨነቅበት፤ የምንችለውን ሁሉ ቀንና ሌሊት የምሠራበት ነው። በርግጥ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለአገራችን ስንለፋ ከነበርን ይህ የታየው ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ ይበልጡኑ የምንተጋበት ጊዜ አሁን ነው።

በስሜት እየተንቦጫረቅን ከተቀመጠው ዋንኛ የድል መንገድ የምንወጣ ከሆነ መፈረካከስ ይሆናልና በጥሞና ወደ ድልና መደመር የሚወስደንን ጎዳና አንልቀቅ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለለውጡ መቀጠል ሁላችንም በተግባር የሚጠበቅብንን እንወጣ። አሁን የጥፋት ኃይሎች ሆነው ብቅ ያሉት ያለ ከልካይ እንደመዥገር ተጣበቀው ሲጠቧት የነበረችውን አገር እንዲለቅቁ እየተደረጉ ነውና በቀላሉ ለመልቀቅ ፈቃደኞች ይሆናሉ ብሎ መገመት የዋህነት ነው።

ይህ ለውጥ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመኖርን ትርጉም ፍንትው አድርጎ ያሳየ የመሆኑን ያህል ለነዚህ ኃይሎች ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው የሆነባቸው። ስለዚህ በለውጡ ሒደት በፍጥነት ወደፊት ከምንገሰግስ ይልቅ እሣት ወደ ማጥፋት እንድንሄድና በሒደትም መንገዳችንን እንድንስት እንደሚያደርጉን ጠንቅን ልንገነዘብ ያስፈልጋል።

እነዚህ የተቀናጁ፣ የተደራጁ፣ ለዘመናት ሲዘርፉት በነበረው በርካታ የገንዘብ ኃይል የሚደገፉ፣ ለአገር ደኅንነት ቅንጣት ያህል የማይጨንቃቸው ኃይሎችን በስሜት፣ በግብታዊነት፣ በበቀል፣ በእልህና በንዴት ሳይሆን አካሄዳቸውን በማጥናት፣ በብልሃትና በትጋት ነቅተን የምንታገልበት ወሳኝ ሰዓት ላይ ነን። የተጀመረው የለውጥና የተሃድሶ ጉዞ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑን በመገንዘብ ለድል እናምርር።

ስለዚህ ባለሙያዎችም አገራችሁን የምትረዱበት ወቅት አሁን ነውና ኢትዮጵያን በማዳኑ የቀና መንገድ ያለ አንዳች ይጥቅም የበኩላችሁን ተወጡ። አገራችሁ ትፈልጋችኋለች፤ የትኛውም ዓይነት የሙያ ልምድ ይሆን ትምህርት በአሁኔ ጊዜ ያስፈልጋልና በሁሉም መስክ ተደመሩ። በሚዲያ ላይ ያላችሁ በማኅበራዊ ድረገጾችም ይሁን በድረገጾችና በመካነ ጦማሮች ላይ የምትሳተፉ፣ አስተያየት የምትሰጡ የብሽሽቅ ፖለቲካውን ባካችሁን አርግቡት፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚበልጠውና ይቅርባችሁ። 

የዓመታት ግፍ በርግጥ ብዙ እንዲባል ያስገድዳል ግን ደግሞ ውጤቱ መልሶ እኛኑ የሚጎዳ ከሆነ መተዉ የተሻለ ይሆናል። አሁን እየጎላ የመጣውን የለውጥና የመኖር ተስፋ፣ ተመልሶ ኢትዮጵያዊ የመሆን ታላቅ ዕድል ለማፈራረስ የማይማስ ጉድጓድ የለምና ሁሉም ዘብ ይቁም!!

No comments