Latest

ተቃውሟችን ምክንያታዊ ነበር ውሳኔአችንም ምክንያታዊ ነው – በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የስፖርትና የባህል ዝግጅት ኮሚቴ


በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የስፖርትና የባህል ዝግጅት ኮሚቴ
  • ለመላው የሽቱትጋርትና አካባቢው ማሕበረሰብ እንዲሁም በመላው አውሮፓ የምትገኙ ደጋፊዎችና ተከታዮች
  • ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን
ሽቱትጋርት፣ 26/06/2018
እንደሚታወቀው በየዓመቱ የሚደረገው የኢትዮጵያዊያን የስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ከኦገስ 01 እስከ ኦገስት 04. 2018ዓ.ም በአባይ ስፖርት ክለብ አዘጋጅነት በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ ሊካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል።
ይህን ፌስቲቫል አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያዊያን የስፖርትና ባሕል ፌዴሬሽን በአውሮፓ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት እወክለዋለሁ የሚለውን፣ ሰፊውን በአውሮፓ የሚኖር፡
  1. ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በማያማክል መልኩ ሲሰራ በመቆየቱ
  2. የፌስቲቫል ዝግጅቱ ኢትዮጵያዊያንን በእኩል መልኩ ማሳተፍ ባለመቻሉ
  3. የወያኔ እረጅም እጅ እንደፈለገ ሲያሽከረክረው የነበረ በመሆኑ
  4. በየዓመቱ የፌስቲቫሉ ካዝና ተዘረፈ፣ ከሰረ በሚሉ ሰበብ አስባቦች ከልካይና ጠያቂ በሌለባቸው የአመራሩና የእነርሱ ደጋፊዎች የግል ኪስ ማደለቢያ በመሆኑ
  5. ፌዴሬሽኑ በአውሮፓ የሚኖሩ ሰደተኞች ሆኖ ሳለ አግባብ ባልሆነ መልኩ ከኢትዮጵያ የአበበ ቢቂላ ክለብ በሚል ስያሜ የተለያዩ ተጨዋቾችን ማስመጣት ትክክለኛ ባለመሆኑ
  6. ሐላፊነት በጎደለው መልኩ ኢትዮጵያዊ ባሕልና ልምዱን ተምሮና ተዝናንቶ ወደመጣበት እንዲመለስ የሚገባውን ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወጣት በአልኮሆል መጠጦችና የሺሻ ጭሶች በመጋበዝ የግል ኪሳቸውን ለመሙላት መትጋታቸው ከብዙው በትንሹ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
እነዚህን እና ሌሎችም በፌዴሬሽኑ ውስጥ ሊፈፀሙ የማይገባቸው ጉዳዮችን በመቃወም በሽቱትጋርትና አካባቢው ያሉ ከተለያዩ ድርጅቶች የተውጣጡ ስብስቦች እነዚህ ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች አንክሮ በመስጠት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው የዘንድሮው ፌስቲቫልን ለማካሄድ ሃላፊነቱን ከወሰደው የጥቁር አባይ ስፖርት ክለብ በሽቱትጋርት አንዴ በአካል ተገናኝተው የመጀመሪያ ውይይት ከማድረግና አንዴ ደግሞ በፅሁፍ መልክ ሐሳብ ከመለዋወጣቸ ውጪ ይዘው የመጡትን የማስተካከያ ሐሳብ በተደጋጋሚ ለመወያየት ጥሪ ቢያደርጉም ከፌዴሬሽኑ ጭምር ማንኛቸውም ለመስማት ፍላጎት አልነበራቸውም።

በዚህም የተነሳ እነዚህ ስብስቦች ይዘታቸውን በማጠናከርና በማስፋት ከሽቱትጋርትና አካባቢው አልፎ በጀርመን ከዛም ከፍ ብሎ በአውሮፓ የተቀናጀ ግብረሐይል ተደራጅቶ ከኦገስት 02 እስከ ኦገስት 04 2018 ተመሳሳይ ፌስቲቫል ለማድረግ ዝግጅቱን ወደ ሰማንያ በመቶ አጠናቅቋል።
  
እነዚህንም በዝርዝር ለማስቀመጥ: 
  1. አዳራሽ ማግኘታችን 
  2. ሙዚቀኞችና የኪነጥበብ ሰዎችን ተነጋግሮ መጨረሱን 
  3. የጨዋታ ሜዳ መገኘቱ 
  4. ለሚመጡ እንግዶች የሚያስፈልጉ ሆቴሎችን አዘጋጅቶ መጨረሱና 
  5. እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ የሚጋበዙ የክብር እንግዶችን በማነጋገር ላይ ነበረ 
ይሁን እንጂ የፌስቲቫሉ ዝግጅት ወደማይቀለበስበት ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስተር የወያኔን የዘረኝነት፣ የመከፋፈል፣ የጥላቻ መረብ በጣጥሰው ወጥተው በአገራችን የተስፋ፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የይቅር ባይነትና የአንድነት መንፈስ በመላ አገራችን እና በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ  ሰርጸዋል።
  

በመሆኑም እ.ኢ.አ ስኔ 16. 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ አሕመድን የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ጉዞ የድጋፍ መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ጠ|ሚ ባደረጉት ንግግር ላይ ‹እናንተ ይቅር ስትባባሉ፣ እናንተ አንድ ስትሆኑ.....› እኔን እንደደገፋችሁኝ እቆጥረዋለሁ የሚለው አባባላቸው ማንኛውንም ለአገሩ ለወገኑ ሐላፊነት የሚሰማው ዜጋ ለእንደዚ አይነቱ የጠ|ሚ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ተገቢ መሆኑን ተገንዝበን ከአውሮፓው ግብረሃይል ጋር የተጣመረው ከሽቱትጋርትና አካባቢው የተውጣጣው ስብስብ ምንግዜም ቢሆን ለአገሩና ለወገኑ ቀና አመለካከት ያለውና ሐላፊነት የሚሰማው በመሆኑ የጠ|ሚ ዶ.ር አብይ አሕመድን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና ይቅርባይነት እንዲሁም ከመከፋፈል የመደመርን ጥሪ ተቀብሎ በተጨማሪም የአገራችን መጪ ብሩህ ተስፋን እሳቤ በማድረግ ከኦገስት 02 እስከ ኦገስት 04. 2018 በሽቱትጋርት ከተማ ሊያደርግ የነበረውን ዝግጅት ማቋረጡን በይፋ ያሳውቃል።
 

ይህ ውሳኔ ዝግጅቱ አለቀ በሚባልበት ሰአት ብዛት ያለው የገንዘብ ወጪ ከማስወጣቱም ባሻገር ይህንን ጉዳይ ሲያካሂዱ በነበሩት ኢትዮጵያዊያኖች ላይ የተለያዩ የውሸት ስም የማጥፋት ዘመቻ እንዲሁ በገቢያችን መጣችሁ በሚል የከንቱ ማስፈራሪያ ዛቻዎች ሲካሄዱ ብዙ ዋጋ አስከፈሎ የነበረ ቢሆንም ዝግጅቱ እንዲቋረጥ መደረጉ የስብስቡ እና ግብረሃይሉ ምን ያህል ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለፍቅር እና ይቅር ባይነት ዋጋ እንደሚሰጡ ከማሳየቱም ባሻገር ለግል ጥቅም ነው የሚሯራጡት ለሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ከበቂ በላይ መልስ ነው ብለው ያምናሉ።
 

በተጨማሪም የስፖርትና ባሕል ፌዴሬሽን በአውሮፓም ሆነ ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ ይህ የተቃውሞ ጉዞ እንዲገታ የተደረገው ጥያቄዎቻችን ተመልሰው ሳይሆን ከላይ እንደተጠቀሰው ለወቅታዊው የአገራችን ጉዳይና ለጠቅላይ ሚንስትሩ መልስ ለመስጠት መሆኑን ተገንዝባችሁ በሚቀጥለው ዓመት ዝግጅታችሁ ቀና እንዲሆን የዛሬውን በትክክል እንድትሰሩ ወንድማዊ ምክራቸውን ከመለገስ ባሻገር ጥያቄዎቹ እልባት ካላገኙ ሰፊው የኢትዮጵያ በአውሮፓ ነዋሪ ማሕበረሰብ ሊጠይቃችሁ እንደሚችል ግንዛቤ ቢወሰድበት ጥሩ ነው እንላለን። 

በማከልም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ የራሴ ነው በማለት የሚቀጥሉትን ዝግጅቶች በአንክሮ እንዲከታተለውና እንከን አልባ ዝግጅት እንዲሆን ጥረት ቢያደርጉ መልካም ነው እንላለን። በተረፈ የዚህ ዓመት ዝግጅት የተሳካ ዝግጅት እንዲሆን ልባዊ ምኞታቸውን እየለገስን በሽቱትጋርትና አካባቢው እንዲሁም በመላው ጀርመንና ብሎም አውሮፓ የምትገኙ ደጋፊዎችና ተከታዮች ይህንን ውሳኔ እናንተም በበጎ እንደምትመለከቱት በመተማመን ዝግጅቱ መቋረጡን ተገንዝባችሁ ለኢትዮጵያ አንድነትና፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርባይነትና መቻቻል የበኩላችሁን እንድታደርጉ በማሳሰብ
 

እስከዚህ ሰአት ድረስ አይዞአችሁ በርቱ ስትሉ ለነበራችሁ፣ እርዳታችሁን በተለያየ መልኩ ስትለግሱ ለነበራችሁ ባጠቃላይ አብራችሁን ከአጠገባች ለቆማችሁ በሙሉ ልዩ የአክብሮት ምስጋናችንን እያቀረብን ለወደፊትም እራዳታችሁ እንዳይቋረጥ በመማፀን እንሰናበታለን። 

የሽቱትጋርትና አካባቢው ስብስብ ከአውሮፓው ግብረሃይል ጋር በመተባበር።  

ፍቅር ያሸንፋል 
26.06.2018 በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የስፖርትና የባህል ዝግጅት ኮሚቴ

No comments