Latest

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በመስቀል አደባባይ የቦንብ ፍንዳታ አደጋ ለደረሰባቸው ንጹሃን ዜጎች ደም ለገሱ


የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በመስቀል አደባባይ የቦንብ ፍንዳታ አደጋ ለደረሰባቸው ንጹሃን ዜጎች ደም መለገሳቸው ተገለጸ።

የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን እና የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ አዳነች ሃቢቤ ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት ትናንት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ወጥተው የቦንብ ፍንዳታ አደጋ ለደረሰባቸው ንጹሃን ዜጎች ደም ለግሰዋል።

ባለ ስልጣናቱ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው በቦምብ ፍንዳታው አደጋ ደርሶባቸው የህክምና ክትትል ላይ ያሉትን ተጎጂዎች ከጎበኙ በኋላ በቀይ መስቀል የደም ባንክ በኩል ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የደም ልገሳ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው።

ባለስልጣኑ በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅትም ከተጎጂዎችን ጎን መሆናቸውን በመግለጽ እንዳጽናኗቸውም ነው የተገለጸው።

የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ጠይባ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጸው ጥቃቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ በመሆን በፍቅርና በመተሳሰብ ለሀገሪቱ እድገትና ልማት እያደረገ ካለው ጥረት የማይገታው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትየጵያ ህዝብ በእንደዚህ አይነቱ አጸያፊ ድርጊት ወደ ኋላ ሳይል ለሀገር ልማትና እድገት ቀጣይነት መስራት ይገባዋልም ብለዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሯ ወ/ሮ ጠይባ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን አደጋ አጸያፊ ሲሉም አውግዘውታል።

ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ሰዎች መካከልም የሟቾቹ ቁጥር ሁለት መድረሱም ተመላክቷል።

በታሪክ አዱኛ

No comments