Latest

ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ፦ አፓርታይድ ሲኖር ጭቆና ይፈፅማል፣ ሲወድቅ ግጭት ይቀሰቅሳል! ከስዩም ተሾመ


ከአስር ወራት በፊት “አዎ…ኢትዮጲያ እርስ-በእርስ ግጭትና ዕልቂት እያመራች ነው” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። ይህ ፅሁፍ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ቅጭትና አለመረጋጋት የተቀሰቀሰበትን ምክንያት አስመልክቶ ትንታኔ የሚሰጥ ነው። በተመሳሳይ ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ግጭትና ሁከት ተቀስቅሷል። በዚህም በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። “ለዚህ መነሻ ምክንያቱ ምንድነው?” በሚል አንድ ፅሁፍ ለመፃፍ ስዘጋጅ ከአስር ወራት በፊት የፃፍኩት ፅሁፍ ትዝ አለኝ።

ይህን ፅሁፍ ከፍቼ ሳነበው ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት መሰረታዊ መንስዔው ምንና ማን እንደሆነ በዝርዝር ያስረዳል። ስለዚህ ከመንስዔው ይልቅ መፍትሄው ላይ ባተኩር የተሻለ እንደሆነ አመንኩ። ሆኖም ግን፣ ሰሞኑን በሀገራችን ለሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት መንስዔ ምንና ማን እንደሆነ እንድታውቁት በሚል መስከረም ላይ ያወጣሁትን ፅሁፍ አሳጥሬና ርዕሱን ቀይሬ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ። ሙሉ ፅሁፉን ደግሞ ይህን ሊንክ በመጫን ማንበብ ትችላላችሁ።

የሰቆቃ ልጆች እና የብሔር አፓርታይድ በሚል ርዕስ ባወጣኋቸው ተከታታይ ፅሁፎች በዝርዝር ለመግለፅ እንደሞከርኩት አሁን በሀገራችን ያለው መንግስታዊ ስርዓት እ.አ.አ. ከ1948 – 1994 ዓ.ም ድረስ በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ጋር ከአመሰራረቱ እስከ ውድቀቱ ድረስ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ብዙዎች በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በዘር ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን፣ ለአፓርታይድ ስርዓት መመስረት ዋና ምክንያቱ ዘረኝነት አይደለም። የአፓርታይድ መነሻ ምክንያቱ እ.አ.አ. ከ1899 – 1902 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በእንግሊዞች መካከል የተካሄደው ¨The Second Boers War” ነው። ይህ ጦርነት በነጮች መካከል የተካሄደ ጦርነት እንጂ በጥቁሮችና ነጮች መካከል የተካሄደ አልነበረም።

የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ በዘር ሀረግና በቆዳ ቀለም ነጮች፥ ጥቁሮች፥ ሕንዶችና ቅይጦች (colored) በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። ሆኖም ግን፣ የፀረ-አፓርታይድ ትግሉ ሲካሄድ የነበረው በዋናነት በጥቁሮችና በነጮች መካከል ነው። የአፓርታይድ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነጮችን የፖለቲካ የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ 70% የሚሆኑትን ጥቁሮች በጎሳና ብሔር መከፋፈል አለበት።

በዚህ መሰረት፣ የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብን በጎሳና ብሔር ለአስር ክልሎች ከፋፍሏቸዋል። እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን አለው። ነገር ግን፣ የአንዱ ክልል ነዋሪ በሌላኛው ክልል ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሕግ የተከለከለ ነበር። ይህ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አጀንዳና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳይኖራቸው የታለመ ነው።

የአፓርታይድ ስርዓት የአነስተኛ ብሔርን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ሕዝቦች በጎሳና ብሔር በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው። አሁን በኢትዮጲያ ያለው ፖለቲካዊ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ከነበረው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። የህወሓት/ትግራይ የበላይነትን ለማስቀጠል በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች በመለያየት ላይ የተመሰረተ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እ.አ.አ. ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደጎን በመተው የመብትና ነፃነት ጥያቄያቸውን በጋራ መጠየቅ ሲጀምሩ የአፓርታይድ መንግስት የወሰደው እርምጃ አሁን በሀገራችን ለሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት መንስዔን፣ እንዲሁም በሁለቱ ስርዓቶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በግልፅ ይጠቁማል።

እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ አመፅና ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ልክ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች እንደታየው እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ አመፅና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች የመንግስት እርምጃ አንድና ተመሳሳይ ነበር። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ያለማቋረጥ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ምክንያት፣ የሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እያመራ ሄደ። ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መሪ የነበሩት “Pieter Willem Botha” ልክ እንደ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ቃል ገቡ። የጠ/ሚ ኃይለማሪያም ንግግር ለሁላችንም የቅርብ ግዜ ትዝታ ስለሆነ እዚህ መድገም አያስፈልግም። የአፓርታይዱ መሪ ንግግርና የተሃድሶ እንቅስቃሴ ግን “Stephen Ellis” የተባለው የዘርፉ ምሁር ባቀረበው በጥናታዊ ፅሁፍ እንዲህ ገልፆታል፡-
“…in a series of speeches, Botha seemed to try to direct the country into reformist paths and away from the racial “Apartheid”…. What is certain is that his idea of ‘healthy power sharing’ meant he would cling to ‘group rights’ as a means of maintaining White control, which he claimed was still in the best interests of South Africa….A changing and increasingly volatile South African society led to the civil insurrection of 1984 and its repercussions around the country. Botha’s response was the repression of activists and liberation movements under a state of emergency. The reform policy stagnated.…” The Historical Significance of South Africa’s Third Force STOR Stephen Ellis Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299.
ይሁን እንጂ የሁለቱም ሀገራት መንግስታት ስር ነቀል ተሃድሶ ማምጣት ተሳናቸው። ከዚያ ይልቅ፣ የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ማድረግ ቀጠሉ። ሆኖም ግን፣ የሁለቱም መንግስታት እርምጃ የሕዝቡን ቁጣና ተቃውሞን ይበልጥ እንዲባባስ አደረገው። በዚህ ምክንያት፣ እ.አ.አ. በ1986 በደቡብ አፍሪካ፣ ባለፈው የ2009 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጲያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ።

በሌላ በኩል የአፓርታይድ ስርዓት የመከላከያና ድህንነት ኃላፊዎች በሕቡዕ ሦስተኛው ኃይል (The third Force) የተባለ ፀረ-አብዮታዊ ቡድን አቋቋሙ። ይህ ከክልል ሚሊሺያዎችና ልዩ ፖሊስ ኃይል የተወጣጣው ቡድን እንደ ዝምባብዌና ሞዛምቢክ ባሉ ጎረቤት ሀገራት የነበረውን የአማፂያን እንቅስቃሴ እንዲያውኩ የተቋቋሙ ነበሩ። የአሰቸኳይ ግዜው ከታወጀ በኋላ ግን በደቡብ አፍሪካ ጦር ወታደራዊ ስልጠና እና ትጥቅ ተሰጥቷቸው የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን በማጨናገፍ ተግባር እንዲሰማሩ ተደረገ። የአፓርታይድ ስርዓት በተለይ በደቡብ አፍሪካ “KwaZulu Natal” በሚባለው ክልል የታየውና ዛሬ በሶማሊ ክልል እየታየ ያለው ፍፁም ተመሳሳይ ነው።
“In April 1986, the State Security Council had endorsed guidelines for a strategy for counter-revolutionary war which, among other things, emphasised that the forces of revolution should not be combatted by the security forces alone, but also by ‘anti-revolutionary groups such as Inkatha … as well as the ethnic factor in South African society’. In the following months, specifically ethnic organisations were armed and trained in KwaZulu and Ciskei, while anti-ANC groups in other places were encouraged and armed in the form of kitskonstabels or special policemen and vigilantes…. In effect, military units, which had carried out the destabilisation of neighbouring countries, were now implementing similar strategies at home, on the instructions of the State President, the State Security Council and the head of the [South Africa Defense Force]”Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299
በአጠቃላይ፣ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ዛሬ በአንዳንድ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊና ደቡብ ክልሎች እየታየ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮች መካከል የአርስ-በእርስ ግጭት በመፍጠር የነጮች የበላይነትን ለማስቀጠል ካደረገው ጥረትና ካስከተለው ውጤት በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደየት እየሄደች እንደሆነ መገመት ይቻላል።

በደቡብ አፍሪካ በተለይ እ.አ.አ. ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የጥቁር ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር በሕቡዕ የተሰራው ስራ እ.አ.አ. ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ፍሬ አፈራ። በእርግጥ ከመርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅም። በእነዚህ አራት አመታት ውስጥ ብቻ በተነሳ ሁከትና ብጥብጥ 14,000 ደቡብ አፍሪካዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። 

እ.አ.አ. ከ1948 ዓ.ም የአፓርታይድ ስርዓትን ለመጣል በተደረገው ትግል ከተገደሉት ሰዎች ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ብቻ የተገደሉት ይበልጣል። ሀገራችን ወደየት እያመራች እንደሆነ ለማወቅ የሚሻ ከዚህ በላይ ጠቋሚ ማስረጃ የለም። [በደቡብ አፍሪካ ሆነ በኢትዮጵያ አፓርታይድ ሲኖር በደልና ጭቆና ይፈፅማል፣ ሲወድቅ ደግሞ ግጭትና ሁከት ይቀሰቅሳል]።

No comments